የምሽቱ ጨዋታ ተጋጣሚዎች በኮሮና ተመትተዋል

ምሽት አንድ ሰዓት ላይ ወላይታ ድቻ ከ ሀዋሳ ከተማ ከሚያደርጉት ጨዋታ በፊት በርካታ የሁለቱ ቡድን አባላት በቫይረሱ መያዛቸው ታውቋል።

በተለይም ከትናንት በስትያ በድሬዳዋ የምርመራ ማዕከል የተመረመሩት ድቻዎች ከአስራ አምስት በላይ ተጫዋቾቻቸው በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን የሚገልፅ ውጤት የደረሳቸው ሲሆን ይህንን ውጤት በመጠራጠር ትናንት ወደ ሀረማያ ዩኒቨርስቲ በማቅናት ዳግመኛ ምርመራ አድርገው ነበር። ውጤቱም አሁን ጨዋታውን ሊያደርጉ አራት ሰዓት ሲቀረው የደረሳቸው ሲሆን ለቡድኑ አስደንጋጭ ዜና ሆኖ ተሰምቷል። አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች እና ምክትል አሰልጣኙ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል። በዚህም ምክንያት ስምንት ተጫዋቾች እና ሦስት ግብጠባቂዎች ብቻ ለጨዋታው ብቁ መሆናቸው ተነግሯል።

በሀዋሳ ከተማም በኩል ወደ አዲስ አበባ የላከው የኮሮና ምርመራ ውጤት ከዚህ ዘገባ ደቁቃዎች በፊት ውጤቱ እንደደረሳቸው ሰምተናል። በዚህም ከሙሉ የቡድን አባላት 13 ተጫዋቾች ብቻ ነፃ መሆናቸው የደረሳቸው ውጤት አሳይቷል።

በጉዳዩ ዙርያ የሚኖሩ አዳዲስ ጉዳዮችን ተከታትለን የምናቀርብ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ