ግብጠባቂዎቹ ከሚናቸው ውጭ ይጫወታሉ

አብዛኛው ተጫዋቾቹ በኮሮና ቫይረስ የተመቱበት ወላይታ ድቻ ባልተለመደ ሁኔታ ግብጠባቂዎቹ ከሚናቸው ውጭ እንደሚጫወቱ ታውቋል።

ከአስራ አምስት በላይ ተጫዋቾቹ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን ተከትሎ ምሽት ላይ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ጨዋታውን የሚያደርጉት ድቻዎች ሦስት ግብጠባቂዎችን ስምንት ተጫዋቾችን ብቻ በመያዝ በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው እየተመሩ ወደ ሜዳ ይገባሉ። ታዲያ ካሏቸው አጠቃላይ አስራ አንድ ተጫዋቾች መካከል በአስገዳጅ ሁኔታ ሁለቱን ግብጠባቂዎችን ከሚታወቁበት ሚና ውጭ በተጫዋችነት የምንመለከታቸው ይሆናል።

በአመዛኙ የውድድር ዘመን ጨዋታዎች በቋሚ ግብጠባቂነት ድቻን ሲያገለግል የምናውቀው መክብብ ደገፉ በዛሬው ጨዋታ በአጥቂነት ወደ ሜዳ እንደሚገባ ሲጠበቅ ሌላኛው ከተስፋ ቡድን ያደገው ግብጠባቂ አብነት ይስሐቅም በተመሳሳይ በአጥቂ ቦታ እንደሚሰለፉ ታውቋል።

በእግርኳሳችን ብዙ ባልተለመደው በዚህ አስገራሚ ሁኔታ በጨዋታው ላይ ምን ዓይነት ድራማዊ ትዕይንት ሊከሰት እንደሚችል ብዙዎች በጉጉት የሚጠብቁት ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ