በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 19ኛ ሳምንት የመክፈቻ ጨዋታ ሰበታ ከተማ ከመመራት ተነስቶ ጅማ አባጅፋርን ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዮን ሀሳብ ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።
አብርሃም መብራቱ – ሰበታ ከተማ
ስለድሉ ትርጉም
“ለእኛ የዛሬው ጨዋታ ትርጉም አንድ ደረጃችንን የምናሻሽልበት ነው ፤ ሁለተኛ ደግሞ ከአቻ እና መሸነፍ ወጥተን ወደ አሸናፊነት የተመለስበንበት ነው ስለዚህ በቀጣይ በሚኖሩን ጨዋታዎች ላይ በስነልቦናው በኩል ለሁሉም የቡድኑ አባላት ትልቅ አስተዋፅኦ አለው።”
ግብ ስላስተናገዱበት መንገድ
“ግቡ እስኪቆጠርብን ድረስ ጨዋታውን ሙሉ ተቆጣጥረነው ነበር ፤ ግቧ ከተቆጠረችበት በኃላ እልህ ውስጥ የመግባት እና ከምንፈልገው የጨዋታ ሀሳብ የመውጣት ነገር በልጆቻችን ውስጥ ነበር ግን ያንን እረፍት ላይ ነግረናቸው ልክ እንደጀመርንበት መንገድ ጨዋታውን መጨረስ እና ውጤታማ መሆን አለብን ተባብለን ነበር ተመርተን ማሸነፍ መቻላችን በእራሱ አንዱ የስነልቦና ጥንካሬያችን መገለጫ ነው። ስለዚህ እንዛሬው ጨዋታ ብልጫችን ማሸነፍ ይገባናል ብዬ አስባለሁ ጅማም በበኩሉ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነ ቀርቧል ከሌሎች ጨዋታዎች የተሻለውን ጅማ ነበር ዛሬ የተመለከትነው።”
ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ጅማ አባጅፋር
ውጤት ስለማስጠበቅ ድክመት
አዎ በትክክል ድክመት ነው። ተጫዋቾቻችን በውጤት መጥፋት ጫና ውስጥ ናቸው። በዚህም ቀድመን ጎል እናስቆጥራለን፤ ግን የማስጠበቅ ከፍተኛ ችግር አለብን። በግል የሜዳ ውስጥ ታታሪነታቸው ጥሩ ነው። ግን የመከላከል ቅርፃችን ጥሩ አልነበረም። ያን ማስተካከል አለብን። እንደሚታወቀው በየክለቡ ውጤት ቀያሪ ተጫዋቾች አሉ። እኛ ጋር ግን ገና ቡድን እየሰራን ነው ያለነው ከዚህ ጋር በተያያዘ የልምድ እጥረቶችም አለ። ስለዚህ ነጥብ ጥለን ለመውጣት ተገደናል።
በሁለቱ አጋማሾች ወጥ አቋም አለማሳየት
እንደሚታወቀው በተወሰኑ ተጫዋቾች ነው ተከታታይ ጨዋታ እያደረግን የምንገኘው። ስብስባችን በቁጥር ካልሆነ በቀር በጥራት ላይ የተሟላ ነው ማለት አንችልም። ስለዚህ ያ የፈጠረው ጫና ነው። ቀይረን የምናስገባቸው ቋሚዎቹን የሚተኩ ስላልሆኑ ውጤቱን ሊያበላሽብን ችሏል። ዞሮ ዞሮ የመዳከም ብቻ ሳይሆን ልጆቹ ውጤትን ለማስጠበቅ ወደ መከላከል አደረጃጀት የሚገቡበት መንገድ እንደ ድክመት የሚታይ ነው በቀሪ ጨዋታዎች ተስፋ አንቆርጥም። ተሻሽለን ለመቅረብ ጥረት እናደርጋለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ