ነገ ምሽት የሚከናወነውን ጨዋታ የተመለከቱ ነጥቦችን እንዲህ አንስተናል።
ይህ ጨዋታ የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻው እና የአሁኑ አስተናጋጅ ከተማ ክለቦችን ያገናኛል። ሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ባህር ዳር ከሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦችን ማሳካት የቻለ ሲሆን ነገ ውጤት ይዞ ከወጣም ነጥቡን ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የሚያስተካክልበት ዕድል ይፈጠራል። ባሳለፍነው ሳምንት በወላይታ ድቻ ደረሰበት ሽንፈት ሲዳማ ቡናን ተክቶ በወራጅ ቀጠና ውስጥ የተገኘው ድሬዳዋ ከተማም የነጥብ ስብስቡን 19 አድርሶ ከአደጋው ፈቀቅ ለማለት ጨዋታውን ማሸነፍ መቻሉ ትልቅ ዋጋ ይኖረዋል።
ባህር ዳር ከተማ በኋላ መስመሩ ላይ አስገዳጅ ቅያሪዎችን ለማድረግ ቢገደድም ባለፉት አራት ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር መውጣቱ ለነገው ጨዋታ ስንቅ የሚሆነው ነጥብ ነው። በተናጠልም ሆነ እንደ ዲፓርትመንት መልካም ጊዜ እያሳለፉ ያሉት የቡድኑ ተከላካዮች ከአማካይ ክፍላቸው እያገኙት ያሉት ጥሩ ሽፋን ነገም ፈጣኖቹን የድሬዳዋን አጥቂዎች እንቅስቃሴ ለመግታት አስፈላጊያቸው ይሆናል። ቡድኑ ክፍተቶችን በቶሎ በመድፈን ከተጋጣሚ የማጥቃት ሽግግር ቀድሞ እንዲገኝ ከመስመር አጥቂዎቹ ጭምር የሚያሳየው መታተር ሊያስቀጥለው የሚገባው ጠንካራ ጎኑ ነው።
በሌላ በኩል በማጥቃቱ ረገድ በፋሲሉ ጨዋታ ቡድኑ ላይ የታየው ድክመት ነገ ሊሻሻል የሚገባው ነው። በእርግጥ የድሬዳው ጨዋታ ከደርቢው ይልቅ እንደ ወልቂጤው ጨዋታ ከስሜት ነፃ የሆነ ተመጣጣኝ ፉክክር ሊታይበት የሚችል መሆኑ የጣና ሞገዶቹ በተጋጣሚ ሳጥን ዙሪያ በቁጥር በረከት ብለው እና በእርጋታ ውስጥ ሆነው ቅብብሎችን እንዲከውኑ ዕድል ሊሰጣቸው ይችላል። በ18ኛው ሳምንት ላይ በነበሩበት ሁኔታ ግን የተጋጣሚያቸው የኋላ ክፍል ስህተቶች ሲሰራ የሚታይ ቢሆንም ከአደገኛ ሙከራዎች በዘለለ ዕድሎችን ወደ ግብነት ለመቀየር ሊቸገሩ ይችላሉ።
ድሬዳዋ ከተማ በድቻ የተሸነፈበት ጨዋታ እንቅስቃሴ ከእጁ የወጣበት መንገድ ለቡድኑ የሚያስቆጭም ትምህርት የሚሰጥም ነበር። ጥሩ የቡድን መዋቅር እየያዘ የመጣው ድሬዳዋ በተጋጣሚዎቹ ላይ ብልጫ በሚወስድባቸው የጨዋታ ክፍሎች ግቦችን አስቆጥሮ እንቅስቃሴውን ማብረድ አለመቻሉ ከድቻው ጨዋታ በፊት ነጥብ በተጋራባቸው አጋጣሚዎችም ላይ ታይቶበታል። ከዚህ አንፃር የነገ ተጋጣሚው ከፍ ባለ ጉልበት የሚጫወት ከመሆኑ አንፃር የቡድኑ አጥቂዎች ከእስከዛሬው በተሻለ ስልነት ላይ በመገኘት የጨዋታ ብልጫን አግኝተው ዕድሎችን የሚፈጥሩባቸውን ቅፅበቶች ሳያባክኑ መጠቀም ይኖርባቸዋል።
ጅማ አባ ጅፋርን የረታበት ጨዋታ መሀል ላይ ገባ እንጂ በሁለት ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን ያስተናገደው ድሬዳዋ በመከላከሉ ረገድም የቤት ሥራዎች እንዳሉበት ግልፅ ነው። በተለይም ከእንደነገ ዓይነት ብዙ ግብ አግቢዎች ካሉት ቡድን ጋር ሲጫወት ግለሰባዊ ስህተቶችን ፈፅሞ ማስወገድ ይኖርበታል። ከዚህ በተጨማሪ ከፊት አጥቂው ጀርባ የሚጫወቱ የማጥቃት ባህሪ እና ኃላፊነት ያላቸው ተሰላፊዎቹ ከተከላካይ አማካዮቹ በተጨማሪ የቡድኑን የመከላከል ሽግግር እንዲያግዙ ማድረግ ወሳኝነት ይኖረዋል።
ነገ የሚደርሰው የቡድኖቹን የኮቪድ ውጤት ሳያካትት ባህር ዳር ከተማ በስብስቡ ላይ ምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና የሌለበት ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ በጉዳት የሚያጣው ብቸኛው ተጫዋች አስቻለው ግርማ ሆኗል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሦስት የሊግ ጨዋታዎች ሲገናኙ ባህርዳር ሁለቴ ድሬዳዋ ደግሞ አንዴ ድል ቀንቷቸዋል። በእነዚህ አጋጣሚዎች የጣና ሞገዶቹ አራት ብርቱካናዎቹ ደግሞ ሦስት ግቦችን አስመዝግበዋል።
* ወቅታዊው የኮቪድ ወረርሺኝ በቡድኖቹ የስብስብ ምርጫ ላይ እያሳደረ ካለው ተለዋዋጭነት አንፃር ግምታዊ አሰላለፍ ለማውጣት አዳጋች በመሆኑ የወትሮው የአሰላለፍ ትንበያችን በዳሰሳው ያልተካተተ መሆኑን እንገልፃለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ