ሪፖርት | ማራኪ የነበረው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

ምሽት ላይ የተጋናኙት ባህር ዳር ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ከከፍተኛ ፍልሚያ በኋላ 1-1 ተለያይተዋል።

ሁለቱም ተጋጣታሚዎች ከመጨረሻ ጨዋታቸው አንፃር ሦስት ለውጦችን አድርገዋል። ባህር ዳሮች መናፍ ዐወልን በሳሙኤል ተስፋዬ ፣ ፍፁም ዓለሙን በአፈወርቅ ኃይሉ እንዲሁም ምንይሉ ወንድሙን በባዬ ገዛኸኝ ቦታ ተጠቅመዋል። ድሬዳዋዎች በበኩላቸው በዐወት ገብረሚካኤል ፣ በረከት ሳሙኤል እና ጁኒያስ ናንጄቦ ምትክ ያሬድ ዘውድነህ ፣ ፍሬዘር ካሣ እና ሪችሞንድ ኦዶንጎን አሰልፈዋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ ከጀመረበት ቅፅበት አንስቶ ለተመልካች ሳቢ የነበረ በሙከራዎች የታጅበ እና ተቀራራቢ ፉክክር የታየበት ነበር። የተሻለ የማጥቃት ምልክትን አሳይተው የጀመሩት ባህር ዳሮች ወደ ፊት ገፍተው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ድሬዳዋ ከተማዎችም በራሳቸው ሜዳ ከመቆየት ይልቅ ፈጥነው ምላሽ መስጠትን መርጠዋል። 12ኛው ደቂቃ ላይ ከኋላ ለምንይሉ ወንድሙ የተላካወን ኳስ ፍሬው ጌታሁን እምብዛም ሳያርቀው አግኝቶ ግርማ ዲሳሳ ወደ ግብ ልኮት ለጥቂት ነበር የወጣው። ከደቂቃዎች በኋላ ድሬዳዋዎች ምላሽ ሲሰጡ ከዘነበ ከበደ የተነሳው ተሻጋሪ ኳስ በተከላካዮች ሲጨረፍ ኢታሙና ኬይሙኒ አግኝቶ በመስ ምት ቢሞክርም ለጥቂት ወደ ላይ ተነስቶበታል።

በጋለ ፉክክር በቀጠለው ጨዋታ ባህር ዳሮች ኳስ ይዘው የፍፁም ዓለሙን እንቅስቃሴ መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሲሞክሩ ድሬዎች ኳሶችን ከጅምሩ በማቋረጥ በፍጥነት ግብ ላይ መድረሳቸው አልቀረም። ባህር ዳሮች የፍቅረሚካኤል የግንባር ኳስ በፍሬው ሲመለስባቸው ሳምሶን ጥላሁንም ከርቀት ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶባቸዋል።

ጨዋታው በሁለቱም የግብ ክልሎች ላይ ተደጋጋሚ የማጥቃት ሙከራዎችን እያሳየን ቀጥሎ ድሬዎች ቀዳሚ የሆኑበትን ጎል በ35ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። ከቀኝ የሜዳ ክፍል የተገኘውን ቅጣት ምት ሄኖክ ኢሳይያስ በቀጥታ ወደ ግብ ልኮት ባልተጠበቀ ሁኔታ ከመረብ አርፏል።

ድሬዎች ከደቂቃዎች በኋላ መሪነታቸውን ዕድል ከቅጣት ምት አግኝተው ዳንኤል ኃይሉ ድንቅ ሙከራ ቢያደርግም በአግዳሚው ተመልሶበታል። በኋላ ግን ቀጣዩ የቅጣት ምት ተራ የባህር ዳር ሆኗል። በአጋማሹ ጭማሪ ደቂቃ ላይም ፍፁም ዓለሙ ባህር ዳሮች ያገኙትን ቅጣት ምት በአስገራሚ ሁኔታ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ በማድረግ ወደ ዕረፍት አምርተዋል።

እንደመጀመርያው ሁሉ በጥሩ ፉክክር በቀጠለው ሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም በኩል ሙከራዎች ተስተናግደዋል። ድሬዎች ከዕረፍት እንደተመለሱ ሁለት ልዩነት ሊፈጥሩ የሚችሉ አጋጣሚዎችን ቢያገኙም ሙኸዲን ሙሳ ወደ ሙከራነት ሳይቀይራቸው ቀርቷል። በ49ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ዓለሙ ከቀኝ የሜዳው ክፍል የተቀበለውን ኳስ በግሩም ቅልጥፍና ከዞረ በኋላ አክርሮ ሲመታ ፍሬው ወደ ውጪ ያወጣበት ደግሞ ባህር ዳርን መሪ ሊያደርግ የሚችል ዕድል ነበር።

በመጀመርያዎቹ የአጋማሹ ደቂቃዎች አንፃራዊ ብልጫ የነበራቸው ድሬዳዋዎች በ54ኛው ደቂቃ በድጋሚ መሪ ሊሆኑበት የሚችሉበት ወርቃማ ዕድል አግኝተው ነበር። የባህር ዳር የግብ ክልል ውስጥ ተከላካዮች ኳሱን በአግባቡ ባለማራቃቸው ምክንያት ሪችሞንድ ያገኘውን ኳስ ከመጠቀሙ በፊት በሰለሞን ወዴሳ ጥፋት ተሰርቶበት ድሬዳዋዎች ፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኙም የቀድሞው የጣና ሞገድ ተጫዋች ዳንኤል ኃይሉ መትቶ በፅዮን መርዕድ በቀላሉ ተይዞበታል።

በሒደት የተሻለ ብልጫ ያሳዩት ባህር ዳሮች በቀሪው ደቂቃ በተደጋጋሚ የድሬዳዋ የጎል ክልል ቢደርሱም የጠራ የጎል ሙከራ ለማድረግ ተቸግረው ታይተዋል። በ69ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻማውን ኳስ ፍሬው ሲያወጣው ሳምሶን አግኝቶ መትቶ ያሬድ በግንባሩ ያወጣበት እና ከአስር ደቂቃዎች በኋላ ፍፁም ዓለሙ ከቅጣት ምት ሞክሮ ወደላይ የወጣበት ሊጠቀሱ የሚችሉ ሙከራዎች ነበሩ። ፍቅረሚካኤል ዓለሙ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ አክርሮ የመታው እጅግ ጠንካራ ኳስም የፍሬው ንክኪ ባይታከልበት ወደ ግብነት መቀየር የሙችል ነበር።

የስታድየሙን ቀዝቅዝ ያለ ነፋሻማ አየር በብርቱ ፉክክር ያደመቀው ጨዋታም በ 1-1 ውጤት ሲጠናቀቅ ባህርዳር በ 31 ነጥቦች ሦስተኛ ደረጃ ላይ ሲቆይ ድሬዳዋ ደግሞ በ 17 ነጥቦች አስረኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ