ቅድመ ዳሰሳ | ሀዲያ ሆሳዕና ከ ወልቂጤ ከተማ

የ19ኛው ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ቀን የሚጀምርበትን ግጥሚያ በዳሰሳችን ተመልክተነዋል።

በድሬዳዋ የመጀመሪያ ሦስት ነጥባቸውን ለማግኘት ከሚፋለሙት ሁለቱ ተጋጣሚዎች የጨዋታው ወሳኝነት ለወልቂጤ ከተማ ያደላል። ከወራጅ ቀጠናው አራት ነጥቦች ርቀት ላይ ብቻ የተቀመጠው ቡድኑ ተጨማሪ ሽንፈት አደጋ ላይ ሊጥለው በመቻሉ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ይገኛል። ከዚህ በተለየ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከመሪው ጋር ያላቸው ልዩነት ወደ 15 ነጥቦች ቢሰፋም ለሁለተኛ ደረጃ ያላቸው ዕድል ሰፊ በመሆኑ ደረጃቸውን ለማሻሻል የጫወታሉ።

ከአዲስ አበባ ተነስተው ድሬዳዋ በደረሱ ሰዓታት ልዩነት ውስጥ አዳማን ገጥመው ነጥብ የተጋሩት ሀዲያ ሆስዕናዎች የወትሮው የአካል ብቃት ዝግጅታቸው አሁንም አብሯቸው እንዳለ አሳይተዋል። በነገውም ጨዋታ ይህ ጥንካሪያቸው በፈጣን ቅብብሎች ወደ ፊት መሄድ የሚያዘወትረው ተጋጣሚያቸውን ለማቆም የሚጠቀሙበት ዋነኛ መሳሪያቸው እንደሆነ ይታመናል። በመሆኑም ከኳሱ ውጪ በንቃት የኋላ ክፍሉን የሚሸፍን እና የወልቂጤን ቁልፍ አማካዮች በቅርብ ርቀት የሚቆጣጠር ታታሪ የአማካይ ክፍል እንደሚያስመለክቱ ይገመታል።

በማጥቃቱ በኩል ከታጋጣሚ የሚቋረጡ እና ከኋላ የሚጀመሩ ካሶችን በተለይም በቀኝ መስመራቸው ባደላ መልኩ ወደ ፊት መጣል የቡድኑ ዋነኛ ስልት ሊሆን ይችላል። በዚህ ረገድ በተናጠል ሲታይ አስፈሪ የሆነው ነገር ግን ተፈላጊው መናበብ ላይ ያልደረሰው የቡድኑ የፊት መስመር ፈጣን ኳሶችን አውርዶ በተጋጣሚ ሳጥን ዙሪያ ተፈላጊዎቹን የተሳኩ ቅብብሎች ማድረግ እንዲሁም አጨራረሱን ማሳመር ይጠበቅበታል።

ወልቂጤ ከተማ ሁለት ተከታታይ ሽንፈት ያስተናገደበት የድሬዳዋ ቆይታውን የሚያቃናበት ሌላ ከባድ ጨዋታ ይጠብቀዋል። የሲዳማው ጨዋታ ፍልሚያው ፍትጊያ ሲበዛው እንደሚቸገር የተመለከትነው ቡድን ነገም ተመሳሳይ ተጋጣሚ ነው የሚጠብቀው። ቡድኑ እስከጨዋታ ፍፃሜ የሚፋለምበት መንገድ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ተመሳሳዩን ጥረት ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ በማድረግ እና ከስህተት በመራቅ ከመጨረሻ ጉልበት ጨራሽ ደቂቃዎች ራሱን መታደግ ይኖርበታል። ነገም የቡድኑ የኳስ ፍሰት ጠንካራውን የሆሳዕናን አማካይ እና የኋላ ክፍል በተደጋጋሚ አልፎ ዕድሎችን መፍጠር ይኖርበታል።

ደካማ ሆኖ የታየው የቡድኑ የፊት መስመር የመጨረስ ብቃትም እንዲሁ በእጅጉ ተስተካክሎ መቅረብ የግድ ይለዋል። ከሁሉም በላይ ግን ቡድኑ የግራ መስመሩን አብዝቶ ለመጣቃት የሚጠቀም መሆኑን ተከትሎ ከኋላ የሚፈጠረውን ክፍተት ለመድፈን ያደረግው ጥረት በመጨረሻው ጨዋታ የተሻለ መልክ መያዙ ነገ ይበልጥ ተሻሽሎ እንዲቀርብ በር የሚከፍትለት ነው። ያም ቢሆን የሆሳዕና የቀኝ መስመር ጥቃት ከባድ መሆኑ እና የቶማስ ስምረቱን ቅጣት ተከትሎ ቡድኑ አዲስ የመሀል ተከላካይ ጥምረት የሚፈጥር መሆኑ ከአደጋው ሙሉ ለሙሉ ነፃ እንዳይሆን ያደርገዋል።

የቡድኖቹን የኮቪድ ምርመራ ውጤት ሳይጨምር ሀዲያ ሆሳዕና ያለጉዳት እና ቅጣት ጨዋታውን ሲጀምር ወልቂጤ ቶማስ ስምረቱን በቅጣት እስራኤል እሸቱን ደግሞ በጉዳት ያጣል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በዚህ ዓመት የመጀመሪያ ዙር ሲገናኙ በሄኖክ አየለ እና ሳሊፉ ፎፋና ጎሎች 1-1 የተለያዩበት ጨዋታ ብቸኛው የሊጉ ግንኙነታቸው ነው።

* ወቅታዊው የኮቪድ ወረርሺኝ በቡድኖቹ የስብስብ ምርጫ ላይ እያሳደረ ካለው ተለዋዋጭነት አንፃር ግምታዊ አሰላለፍ ለማውጣት አዳጋች በመሆኑ የወትሮው የአሰላለፍ ትንበያችን በዳሰሳው ያልተካተተ መሆኑን እንገልፃለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ