“ለረጅም ጊዜ ከሜዳ በመራቄ በሂደት እንደምሻሻል ነው የማምነው” ኦሴ ማውሊ

ሰበታ ከተማ ጅማ አባጅፋርን ሲረታ ሁለት ግቦችን ካስቆጠረው ኦሴ ማውሊ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገናል።

ዛሬ ከተደረጉ የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ቀዳሚ የነበረው ጅማ አባ ጅፋርን ከሰበታ ከተማ ያገናኛው ጨዋታ ነበር። በጨዋታው ሰበታ ከተማ በቅድሚያ ግብ ቢቆጠርበትም በጋናዊው አጥቂ ኦሲ ማውሊ ሁለት ግቦች ጨዋታውን አሸንፎ መውጣት ችሏል።

በ2011 የውድድር ዓመት መቐለ 70 እንደርታን በመቀላቀል ወደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ብቅ ያለው ግዙፉ አጥቂ በመጣበት ዓመት ዘጠኝ ጎሎችን በማስቆጠር ከመቐለ ጋር የውድድሩ ቻምፒዮን መሆን ችሎ ነበር። በመቀጠል በተሰረዘው የውድድር ዓመት ወደ ፋሲል ከነማ በማምራት ከተጫወተ በኋላ ከሜዳ ርቆ ቆይቶ በያዝነው የውድድር ዓመት አጋማሽ የሰበታ ከተማ የዓመቱ የመጀመሪያው የውጪ ዜጋ ፈራሚ በመሆን ዳግም ወደ ሊጉ ተመልሷል።

ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች በቡድኑ ቀዳሚ አሰላለፍ ውስጥ መካተት የቻለው ተጫዋቹ ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ ጨዋታ ተመልሶ በፍጥነት የቀደመ ብቃቱን ማግኘት ቀላል እንዳልሆነ ይናገራል። “ወደ ቀድሞው አቋምህ በቶሎ ተመልሰህ መምጣት በጣም ከባድ ነው። ነገር ግን አሰልጣኜ በጣም ጥሩ አሰልጣኝ ነው። በቶሎ ወደ ብቃቴ እንድመለስ ለማድረግ በጥሩ ሁኔታ እያዘጋጀኝ ነው። እኔም በቶሎ ለመመለስ ጥረቴን እቀጥላለሁ።” ይላል። ማውሊ በአዲሱ ክለቡ በቶሎ የተላመደ ይመስላል። “ሰበታ ጥሩ ቡድን ነው ፤ በክለቡ ዙሪያ ያሉ ሰዎችም ለእኔ ጥሩ ናቸው። እስካሁን ሁሉም ነገር መልካም ሆኖልኛል። በዚህ ስብስብ ውስጥ በመካተቴም ደስተኛ ነኝ።” የሚለው አስተያየቱም ከአዲሶቹ የቡድን ጓደኞቹ ጋር ጥሩ እየተግባባ መሆኑን ይጠቁማል።

“ሰበታ ከተማ ከወራጅ ቀጠናው የነበረውን ርቀት ያሰፋበት የዛሬው ጨዋታ እጅግ ወሳኝ ነበር። ጋናዊው አጥቂም በዚህ ሀሳብ ይስማማል። “ለእኔ ትልቅ ጨዋታ ነው። ምክንያቱም ለአንድ ዓመት ያህል ከሜዳ ርቄ ነበር። በመሆኑም ከቡድን ጓደኞቼ ጋር ሆኜ ሁሉንም ነጥቦች ለማሳካት የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ሞክረናል። ግቦቹንም በማስቆጠሬ በጣም ደስ ተሰኝቻለሁ። ”

ባለፉት ጨዋታዎች ከፍፁም ገብረማርያም እና ቡልቻ ሹራ ጋር በመጣመር ከመስመር እየተነሳ ሲያጠቃ የነበረው ማውሊ ዛሬ የፊት መስመር አጥቂነት ሚና ተሰጥቶት መጫወት ችሏል። በቀደሙት ጨዋታዎች ለአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ተስፋ መስጠት ችሎ የነበረው አጥቂው ዛሬ ደግሞ በለስ ቀንቶት ሁለት ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። ከሁለቱ መጫወቻ ቦታዎች የቱ ምርጫው እንደሆነ ስንጠይቀውም እንዲህ ሲል መልሶልናል። “ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቴም አስቀድሞ በፊት አጥቂነት ነው እጫወት የነበረው ፤ እንጂ ከመስመር የሚነሳ አጥቂ አይደለሁም። በፋሲል ከነማም ከቀኝ መስመር እየተነሳው ስጫወት ነገሮች ቀላል አልሆኑልኝም ፤ ከመስመር ተነስቼ ጎሎችን ለማስቆጠርም ተቸግሬያለሁ። በመሆኑም ዛሬ የተጫወትኩበት ቦታ ተስማምቶኛል።”

ከጋናዊው አጥቂ ጋር የነበረንን አጭር ቆይታ ያጠቃለልነው በመጪዎቹ ጨዋታዎች ሰበታ ከእሱ ጎሎችን ያገኝ እንደሆን በመጠየቅ ነበር። የታጫዋቹ ምላሽም እንዲህ የሚል ነበር። “የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ። ለረጅም ጊዜ ከሜዳ በመራቄ በሂደት እንደምሻሻል ነው የማምነው። በመሆኑም ግቦችን በብዛት እንደማስቆጥር በእርግጠኝነት መናገር አልችልም። ያን ለማድረግ ግን የሚቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ