የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የዓርብ ጨዋታዎች ውሎ

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ በሦስቱም ምድቦች ጨዋታዎች ተደርገዋል።

በምድብ ሀ 3፡00 ላይ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመግባት ከመከላከያ ጋር እየተፎካከረ የሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወልዲያን 2-0 አሸንፏል፡፡ተመጣጣኝነት ያለው የጨዋታ እንቅስቃሴን ማስተዋል በቻልንበት የመጀመሪያው አጋማሽ በርካታ ሙከራዎችን ለማየት ባንታደለም ለዕይታ የሚማርክ የጨዋታ አቀራረብን አሳይተውናል፡፡ ወልዲያዎች ኳስን ተቆጣጥሮ በአንድ ሁለት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉ ቢሆንም ያገኙትን ጥቂት ዕድሎች በአግባቡ በመጠቀሙ ረገድ ግን ኢትዮ ኤሌክትሪክ የበላይነት ነበረው፡፡

16ኛው ደቂቃ ላይ ሚካኤል ለማ እጅግ በግሩም መልኩ የግል ብልጠቱን ተጠቅሞ የሰጠውን ኳስ አማካዩ ሀብታሙ ጥላሁን ወደ ጎልነት ለውጦት ክለቡን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ በተሻለ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ከወልድያ የተሻሉ ሆነው የታዩት የአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ልጆች 26ኛው ደቂቃ ኤርሚያስ ሀይሉ ከመስመር የተሰጠውን ኳስ በቀላሉ ከመረብ አዋህዶ በኢትዮ ኤሌክትሪክ 2ለ0 መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ አብዛኛዎቹን የማጥቃት አማራጭ በቀኝ በኩል በተሰለፈው ሰለሞን ጌታቸው ላይ አድርገው ለመንቀሳቀስ የሞከሩት ወልድያ ከተማዎች ምንም እንኳን የበላይነትን ያሳዩ የነበረ ቢሆንም በተጫዋቹ ላይ ጥገኛ መሆናቸውን ወደ ጨዋታ እንዳይመለሱ ዳርጓቸዋል፡፡ በአንፃሩ ወጣቱ የመስመር ተጫዋች ፀጋ ደርቤን ከ70 ደቂቃ በኃላ ለውጠው ካስገቡ በኃላ አልፎ አልፎ ተጨማሪ ጎል ማከል የሚያስችላቸውን አጋጣሚ ኤሌክትሪኮች ማግኘት ችለዋል፡፡ 78ኛው ደቂቃ ፀጋ ደርቤ በአንድ ሁለት ቅብብል ከአቤል ያገኘውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ መቶ የግቡ ቋሚ የመለሰበት እና አሁንም ፀጋ ከግብ ጠባቂ ጋር ከአምስት ደቂቃዎች በኃላ ፊት ለፊት ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረበት የሚጠቁ ሙከራዎች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩ ሁለት ጎሎች ኤሌክቶሪክ አሸንፎ ወጥቷል፡፡

ከሰአትም በሁለተኛ የምድቡ መርሀግብር ጨዋታ ተከናውኗል፡፡ በጣለው ዝናብ የተነሳ ልክ እንደ አየሩ ቀዝቃዛ አጨዋወትን ማየት በቻልንበት የደሴ ከተማ እና ለገጣፎ ለገዳዲ ጨዋታ ብዙዎቹን ደቂቃዎች ኳሶች መሬት ላይ አርፈው በአንድ ሁለት ቅብብል ከመታየት ይልቅ ቡድኖቹ በመረጡት አሰልቺ የጨዋታ መንገድ ሳቢነታቸው እጅጉን እምብዛም የሆኑበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ 20ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር በኩል ሀብታሙ ፍቃዱ ያሻገረለትን ኳስ ፋሲል አስማማው በግንባር በመግጨት ግብ አስቆጥሮ ለገጣፎን መሪ አድርጋለች፡፡ ከርቀት ከሚሞከሩ ሙከራዎች ውጪ እንደ ቡድን በቅንጅት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቡድኖቹ በደንብ ሲቸገሩ ማየት ችለናል፡፡የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ ሲቀረው አማኑኤል ግዛቸው ከሳጥን ውጪ ድንቅ የሆነች ግብ በማስቆጠር ደሴ ከተማን 1ለ1 ማድረግ ችሏል፡፡

ከመጀመሪያው አጋማሽ በባሰ መልኩ ተዳክሞ የቀጠለው ሁለተኛው አጋማሽ ከርቀት ወደ ጎል ለመሞከር ከሚደረጉ ጥረቶች ውጪ ብዙም የጠሩ አጋጣሚዎች ሳንመለከት ጨዋታው 1ለ1 ተጠናቋል፡፡

የምድብ ለ 15ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ሻሸመኔ ከተማ ከአቃቂ ቃሊቲ አንድ አቻ ተለያይተዋል። ሻሸመኔዎች አዝማች ወ/ገብርኤል በራሱ ጎል ላይ አስቆጥሮ መሪ ቢሆኑም 79ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ ሰሙ ግርጌ ላይ የሚገኘው አቃቂን አቻ አድርጓል።

ነቀምቴ ላይ እየተካሄደ የሚገኘው ምድብ ሐ ላይ ሦስት ጨዋታዎች ዛሬ ተከናውነዋል። አሰልጣኝ ከለወጠ በኃላ መሻሻል የሚታይበት ሺንሺቾ ከተማ ባቱ ከተማን ብሩክ ዳንኤል ከእረፍት በፊት ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል ማሸነፍ ሲችል በተመሳሳይ አርሲ ነገሌ ቡታጅራ ከተማን በፀጋው ታዬ ጎል 1-0 አሸንፏል። የጌዲኦ ዲላ እና ደቡብ ፖሊስ ጨዋታ በአንፃሩ 0ለ0 ተጠናቋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ