በአስገዳጅ ሁኔታ ከሚናቸው ውጭ ሙሉ ዘጠና ደቂቃ በአጥቂነት ከተጫወቱት ሁለቱ ግብጠባቂዎች መክብብ ደገፋ እና አብነት ይስሐቅ ጋር ቆይታ አድርገናል።
በኢትዮጵያ እግርኳስ ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ በትናንትናው ዕለት የወላይታ ድቻ እና በሀዋሳ ከተማ ጨዋታ አስገራሚ ትዕይንት ለመመልከት ችለናል። ምንአልባትም በሊጋችን በነጥብ ጨዋታ ሁለት ግብጠባቂዎች ከተፈጥሯዊ ሚናቸው ውጭ ሙሉ ዘጠና ደቂቃ በአጥቂ ስፍራ ሲጫወቱ መመልከት ይህ የመጀመርያ ሳይሆን አይቀርም።
በድሬዳዋ እየተካሄደ በሚገኘው አራተኛው ዙር የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ከባለፈው ሦስት ዙሮች በባሰ ሁኔታ የኮቪድ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ የቡድኖቹን ጉዞ በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈታተነ ይገኛል። በዚህ ሂደት ውስጥ እንደ ወላይታ ድቻ በትሩ ያረፈበት ክለብ የለም። ትናንት ከሀዋሳ ጋር ላለበት የምሽት ጨዋታ ካሉት ሠላሳ ተጫዋቾች መካከል አስራ ዘጠኙ በኮሮና ቫይረስ በመያዛቸው ሦስት ግብጠባቂዎች እና ስምንት ተጫዋቾች በጥቅሉ አስራ አንድ ተጫዋቾችን ያለምንም ተጠባባቂ ተጫዋች ለማጫወት ተገዶ ነበር። የዕለቱም አስገራሚ እና መነጋገርያ ዕርስ የነበረው ሁለቱ የቡድኑ ግብጠባቂዎች መክብብ ደገፋ እና አብነት ይሳሀቅ በአጥቂነት የተጫወቱበት ክስተት ነበር። ይህ አስገራሚ ገጠመኝን አስመልክቶ ከሁለቱ ግብጠባቂዎች ጋር ሶከር ኢትዮጵያ አጭር ቆይታ አድርጋ እንዲህ አቅርባዋለች።
መክብብ ደገፋ
ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለ ገጠመኝ አጋጥሞህ ያውቃል?
ይህ የመጀመርያዬ ነው። እርግጥ ነው ፕሮጀክት እያለሁ አልፎ አልፎ በተጫዋችነት ወደ ሜዳ የገባሁባቸው አጋጣሚዎች አሉ። ሆኖም ግብጠባቂነትን በቋሚነት ሥራዬ ካደረኩ ጀምሮ በነጥብ ጨዋታ አጥቂ ሆኜ ስጫወት ይህ የመጀመርያዬ ነው።
አጥቂ ሆኜ እጫወታለው ብለህ አስበህ ታውቃለህ?
ከትናንት ወዲያ በኮሮና ምክንያት የቡድናችን ተጫዋቾች እንደተያዙ ሲሰማ አጥቂ ሆኜ ልጫወት እንደምችል አሰብኩ እንጂ አንድም ቀንም ይህ አጋጣሚ ይፈጠራል ብዬ አስቤ አላውቅም። እኔ ራሴ ኮሮና ተይዘሀል ተብዬ ነበር። እንደ ገና አልተያዝክም ተብዬ ነው የገባሁት። ያው ተጫዋች ወታደር ነው ለሁሉም ነገር ዝግጁ ሆኖ መጠበቅ አለበት። በስተመጨረሻ ተጫወቱ ሲባል ሥራ እስከሆነ ድረስ በየትኛውም ቦታ የሚሰጥህን ሚና በምትችለው መጠን ቡድንህን አገልግለህ ትወጣለህ።
የጨዋታው እንቅስቃሴህ እንዴት ነበር ?
ያው በማጥቃቱም በመከላከሉም እየተመላለስኩ ቡድኔን ለማገዝ ጥረት አድርጌያለሁ። በጣም ከባድ ነው። መጫወት እንደ ግብጠባቂነት ቀላል አይደለም። ከመጫወት ግብጠባቂ መሆን ይሻላል። ትንፋሽ ከየት ላምጣ በጣም ከብዶኝ ነበር።
ግብጠባቂ ነህ። የሆነ ሰዓት በእንቅስቃሴ ተስበህ ኳስ በእጅ ለመንካት አላሰብክም ?
(እየሳቀ) አይ አላሰብኩም። የነጥብ ጨዋታ ስለሆነ በትክክል አስቤ ነበር ተጠንቅቄ እጫወት የነበረው። አንዳንዴ በእጅ ለመያዝ ይነሽጥሀል። ግን እንዳልኩህ ጨዋታው ወሳኝ ስለሆነ በጥንቃቄ ነው የጨረስኩት።
ጎል ብታገባ ሊሆን የሚችለው ምን ነበር?
እንደመጀመርያ አጥቂ ሆኜ በመጫወቴ ጎል ባገባ ከሚባለው በላይ ደስተኛ ነበር የምሆነው። ጎል ባገባ ለታሪክ ለልጄ የማወራው ነገር ይኖረኝ ነበር። አሁንም ደስተኛ ነኝ። የምችለውን ለማድረግ ሞክሬያለው። ብናሸንፍ አልያም አቻ ብንወጣ አስታራቂ ይሆን ነበር። በመጨረሻ ደቂቃ ጎል በመቆጠሩ በጣም አበሳጭቶኛል።
ቋሚ ግብጠባቂ ነበርክ። የውጭ ግብጠባቂ ከመጣ በኃላ ተጠባባቂ ላይ ተቀምጠሀል። ይህ አያሳስብህም ?
አዎ ጥሩ የውድድር ዓመት እያሳለፍኩ መጥቻለው። በተለይ ቡድናችን በተሻሻለበት የባህር ዳር ቆይታ በአምስት ጨዋታ አንድ ጎል ብቻ ነበር የተቆጠረብኝ። አሁን የውጭ ግብጠባቂ መጥቷል። ይህ ጥሩ ነው የፉክክር ስሜት ይፈጥራል። ጠንክሬ እንድሰራ ያደርገኛል። ከዚህ ቀደም በሦስት አጋጣሚ በሌላ ክለብ በነበረኝ ቆይታ ከውጭ ግብጠባቂዎች ጋር ሰርቻለው። ለኔ የነበራቸው እምነት ከውጭ ግብጠባቂው ጋር እኩል አልነበረም። አቅሙ እያለህ እኩል አትታይም። ያ በጣም በስነ ልቦናው ተፅዕኖ አሳድሮብኛል። አሁንም ቢሆን ራሴን በሚገባ በማዘጋጀት ጥሩ ተፎካካሪ ለመሆን ጠንክሬ እሰራለሁ።
አብነት ይስሐቅ
ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለ ገጠመኝ አጋጥሞህ ያውቃል ?
በፍፁም ከልጅነቴም ጀምሮ ፍላጎቴ ግብጠባቂ ሆኖ መጫወት ስለሆነ አጥቂ ሆኖ የመጫወት አጋጣሚ አልነበረኝም። ይህ የመጀመርያዬ ነው። ግብጠባቂ ሆኜ ነው ከፕሮጀክትም ጀምሮ በተስፋ ቡድንም ስጫወት የቆየሁት።
አስበውስ ታውቃለህ አንድ ቀን አጥቂ እሆናለው ብለህ?
በፍፁም አስቤ አላውቅም። ሁሌም ጠንክሬ በመሥራት ጥሩ ግብጠባቂ የምሆንበትን እንጂ በትልቅ ደረጃ ሙሉ ዘጠና ደቂቃ አጥቂ ሆኜ እጫወታለው ብዬ አላሰብኩም። አሰልጣኜ ከተፈጠረው ችግር አንፃር አጥቂ ሆኜ እንደምጫወት ሲነግረኝ ውስጤ ድንጋጤ ፈጠሮብኝ ነበር። ነገር ግን አንዳንዴ እንዲህ ያሉ ነገሮችን በጥሩ መልኩ ተቀብሎ መጋፈጥ ያስፈልጋል።
ጎል ብታስቆጥር…?
ጎል ባስቆጥር በህይወቴ የማረሳው ቀን ይሆን ነበር። በጣም ደስ ይለኝ ነበር። በታሪክ አጋጣሚም ሁሌ የምታወስበት ይሆን ነበር። ትንሽም ቢሆን ጥረት አድርጌ አልተሳካልኝም። ያም ቢሆን ከዚህ ቀደም ያልነበረ ነገር በኔና በመክብብ አማካኝነት ሙሉ ዘጠና ደቂቃ አጥቂ ሆነው የተጫወቱ ግብጠባቂዎች ተብሎ መነሳቱ በሚዲያም መነጋገርያ መሆናችን ለእኛ ጥሩ የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ በማለፉ በራሱ አስደስቶኛል። ይሄ ደግሞ በበሽታው ምክንያት ሊቀጥልም ይችላል። አይታወቅም ዳግመኛ አጥቂ እንሆን ይሆናል።
በእንቅስቃሴ ሜዳ ውስጥ አልተቸገርክም ?
አዲስ ስለሆነብኝ የመጀመርያዎቹ 25 ደቂቃ ትንፋሽ እያጠረኝ በጣም ተቸግሬ ከብዶኝ ነበር። በኃላ ቀስበቀስ አሰልጣኞቼም ረጋ ብለህ ተጫወት ብለውኝ ዘጠና ደቂቃውን ለመጨረስ ችያለሁ።
© ሶከር ኢትዮጵያ