“የዓለም ፍፃሜ፤ የህይወቴ ፍፃሜ አድርጌ ነበር የወሰድኩት” – አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ

በ18ኛው ሳምንት ከባህር ዳር ከተማ ጋር በነበረው ወሳኝ ጨዋታ ቡድናቸውን በኮቪድ ምክንያት ያልመሩት አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ስላሰላፉት አስቸጋሪ ጊዜ እና ስለ ነገው ጨዋታ ይናገራሉ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው ኮቪድ-19 ወረርሺኝ ምክንያት የእግርኳሱን ተለምዷዊ እንቅስቃሴ ባልተለመደ መንገድ ቀይሮት እያስኬደው ይገኛል። በሀገራችን ኢትዮጵያም ውድድር እስከማቋረጥ ያደረሰው ይህ ወረርሽኝ ከወራት የእግርኳስ እንቅስቃሴ መቋረጥ በኃላ ዳግም ወደ ውድድር መመለስ ተችሏል። ታዲያ በየጨዋታዎቹ የኮቪድን ፕሮቶኮልን በጠበቀ ሁኔታ በሚካሄደው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ከጨዋታ በፊት በሚደረጉ የኮቪድ የምርመራዎች ውጤቶች የተለያዩ ያልተጠበቁ ክስተቶችን እያስተናገደ ሊጠናቀቅ የስድስት ሳምንት ጨዋታዎች ዕድሜ ይቀረዋል። እስካሁን በተካሄደው ውድድር አንድም አሰልጣኝ ኮቪድ ተገኝቶበት ቡድኑን ያልመራበት ሁኔታ ሳይፈጠር የቆየ ሲሆን በ18ኛው ሳምንት ግን አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ የመጀመርያው ሰው በመሆን ቡድናቸውን ለቡድን መሪያቸው አስረክበው በስልክ ልውውጥ ለመምራት ተገደዋል። ይህን ያልተጠበቀ ሁኔታን እንዴት አሳለፉት? ነገስ ከሲዳማ ቡና ጋር የሚኖረውን ወሳኝ ጨዋታ ወደተለመደው ሥራቸው ተመልሰው ቡድናቸውን ወደ ዋንጫ የሚያደርገውን ግስጋሴ በፊት አውራሪነት ይመራሉ ወይ? ስንል አጭር ጥያቄ አቅርበንላቸው ተከታዩን ምላሽ ሰጥተውናል።

“ዓምና ነሐሴ ወር ላይ የኮሮና ህመም አጋጥሞኝ ለአስራ ሰባት ቀን በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የህክምና ክትትል ሳደርግ ቆይቻለው። ምስጋና ለጳውሎስ ሆስፒታል ዶክተሮች ይሁን እና ስላወቁኝ በቂ የሆነ ክትትል አድርገውልኝ አገግሜ ወጥቻለሁ። እንዲያውም ሰውነትህ ከዚህ በኃላ በሽታን የመቋቋም አቅም አዳብሯል። መታመምህን አትጥላው እስከማለት ደርሰው ነበር። ስለዚህ በሽታው ምን ዓይነት ምልክቶች እና ህመሙን ደረጃ በሚገባ አውቃለው። ገና ሲጀምረኝ በሦስት ቀን የተሰማኝ ልነግራችሁ አልችልም። በጣም ከባድ ነበር። የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ የምግብ ጣዕም ማጣት ነበር፤ ምንም ነገር አይሸተኝም፤ በጀርባዬ መተኛት አልችልም፤ የእጄ እና የእግሬ መገጣጠሚያዎች ሁሉ ያሙኝ ነበር። አሁን ላይ እዚህ በጣም የሚደንቅ እኮ ነው። ከጤና በላይ ጤና ነኝ፤ ምንም ነገር የለም። ምልክቶቹን እንኳን አላየሁም። እኔ ብቻ አይደለም አብረውኝ ያሉት የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ሳይቀር ጤና ናቸው። አጋጣሚ ሆኖ ያለሁበት ሆቴል ድረስ የድሬዳዋ የጤና ባለሙያዎች መጥተው በድጋሚ ምርመራ አድርጌ ነፃ ነህ ብለውኛል። እንደገና ከሁሉም ከቡድን አባላቶች ጋር ምርመራ አድርገን ውጤት እየጠበቅኩ እገኛለው። ዘጠና ዘጠኝ ፕርሰንት ነፃ እሆናለው ብዬ በማሰብ ነገ ቡድኔን በተለመደው ሥራዬ ለመምራት ዝግጁ ሆኜ እየጠበኩ እገኛለሁ።

“ባለፈው ግን ቡድኔን በተገቢው መንገድ በአካል ተገኝቼ ባለመምራቴ የዓለም ፍፃሜ፤ የህይወቴ ፍፃሜ አድርጌ ነበር የወሰድኩት። በጣም አስጨናቂ ጊዜ ነው። በስልክ አውርተን ከሀብታሙ ጋር ልንገናኝ ሞክረን ነበር። ግን አንተ እንደምትፈልገው በእርሱ ውስጥ ገብቶ ለመተግበር ይከብዳል። በቀጥታ በአካል ተገኝተህ ከልጆችህ ጋር መነጋገር የተሻለ ነው። ከምንም በላይ የእኔ እዛ ጋር መኖር ተፅዕኖው ቀላል አይደለም።

“እኔም ሆንኩ ደጋፊዎቼ ተጫዋቾቼም ፋሲልን ታሪካዊ አድርገን ማለፍ እንፈልጋለን። ስለዚህ እያንዳንዱን ጨዋታ በጉጉት ነው የምንጠብቀው። ያው መቻኮል አይሁን እንጂ ቶሎ አውጀን የሻምፒዮን ክብርን ማግኘት ቀላል እናስባለን። ይሄም ቀላል ስኬት አይደለም። ነገር ግን በእግርኳስ ጨዋታ ላይ ሁሌም መጠንቀቅ ስላለብን። እያንዳንዱን ጨዋታ በትኩረት እናስኬዳለን።”


© ሶከር ኢትዮጵያ