ነገ ምሽት የሚደረገውን ተጠባቂው የሸገር ደርቢን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
የውድድር ዓመቱን አራተኛ ሽንፈት በሀዋሳ ከተማ ካስተናገዱ በኋላ ሰበታን በመርታት ዳግም ወደ አሸናፊነት የተመለሱት ኢትዮጵያ ቡናዎች የድል ጉዞዋቸውን ለማስቀጠል፣ ከመሪው ፋሲል ከነማ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ እንዲሁም ተጋጣሚያቸው ቅዱስ ጊዮርጊስን ጨምሮ ከሚከተሏቸው ብድኖች ለመራቅ በነገው ጨዋታ ሦስት ነጥብ ያስፈልጋቸዋል። ድል ካደረጉ አራት የጨዋታ ሳምንታት ያለፋቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች በበኩላቸው ከአስከፊው ውጤት አልባ ጉዞ ለመላቀቅ፣ ከመሪው ፋሲል ከነማ ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ፣ ደረጃቸውን ለማሻሻል እና ከድል ጋር ለመታረቅ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆያሪ ቡድን (36) የሆነው የአሠልጣኝ ካሳዬ አራጌ ኢትዮጰያ ቡና የፊት መስመሩ ስልነት ለተጋጣሚዎች የራስ ምታት ሆኗል። ምንም እንኳን ቡድኑ ኳስን በትዕግሰት ተቆጣጥረው ከሚጫወቱ ቡድኖች መካከል ቀዳሚው ቢሆንም ፊት መስመሩ ትዕግስት እና ርህራሄ የሚባል ነገር አያውቅም። በተለይም የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ አቡበከር ናስር ብቃት ቡድኑ የተሻለ ውጤት እንዲያገኝ እያስቻለው ይገኛል። ነገም በተመሳሳይ ቀልጣፋው አቡበከር ፍጥነቱን እና ቴክኒካዊ ብቃቱን ተጠቅሞ የሚያደርጋቸው የጎል ፊት እንቅስቃሴዎች የጨዋታውን ውጤት እንደሚወስኑ ይገመታል። ከእርሱ በተጨማሪ ከመስመር የሚነሱት የቡድኑ ተጫዋቾች ተጨማሪ የጎል ምንጭ እንደሚሆኑ ይታሰባል።
የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ከኳስ ጋር ጥሩ ቢሆኑም ከኳስ ውጪ የሚያሳልፉት ጊዜ ብዙም የተዋጣለት አይደለም። በተለይ ቡድኑ ከማጥቃት ወደ መከላከል በሚያደርገው ሽግግር ተጋጣሚዎች በጎ ነገሮችን ለራሳቸው እያገኙበት ይገኛል። ከዚህም መነሻነት ነገ በዚህ ክፍተት ፈጣሪ የመከላከል አደረጃጀቱ ፈተና ላይ እንዳይወድቅ ያሰጋል። በተጨማሪም ቡድኑ ኳስ ከኋላ ሲጀምር መጠነኛ የቅብብል ስህተቶችን ሲሰራ ይስተዋላል። በተለይ ተጭኖት የሚጫወት ቡድን ሲገጥም ይህ ችግሩ በጉልህ ይታያል። ስለዚህም ቡና በዚህ ረገድ ነገ ችግር እንዳይገጥመው ያሳስባል።
በቡናማዎቹ በኩል የኮቪድ ውጤታቸው ዘገባውን እስካጠናከርንበት ወቅት ባይደርስም አቤል ከበደ እና ኃይሌ ገብረትንሳኤ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታው ውጪ መሆናቸው ተረጋግጧል።
ከአዲሱ አሠልጣኛቸው ፍራንክ ነታል ጋር ለመሻሻል የሚያልሙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የ17ኛ ሳምንት አራፊ ቡድን በመሆናቸው ከሰበታ ጋር ጨዋታቸውን ካደረጉ በኋላ ወደ ቢሾፍቱ ተጉዘው ነበር። ቡድኑ በቢሾፍቱም ልምምዱን ለሳምንት ሲያደርግ ከቆየ በኋላ ትናንት ከሰዓት ድሬዳዋ ደርሷል። ነታል ሰበታን ሲገጥሙ ቡድኑ ላይ የታየው የእንቅስቃሴ መሻሻል ነገ የቡድኑ ደጋፊዎች ተስፋን እንዲሰንቁ አድርጓል። በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ተጫዋቾቹ ላይ የታየው የማሸነፍ ፍላጎት ከወትሮ ለየት ያለ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ለበርካታ ጊዜያት ቡድኑ አቶት የነበረውም ፍጥነት በተወሰነ መልኩ አግኝቶት ተመልክተናል። ከዚህም መነሻነት ነገም ቡድኑ ኳስ ሲይዝ በፍጥነት ነገሮችን ለመከወን ከሞከረ በጎ ነገሮችን ሊያገኝ እንደሚችል ይታሰባል።
ባለፉት አራት ጨዋታዎች በድምሩ ከሁለት ያልበለጡ ግቦችን ብቻ ተጋጣሚ ላይ ያስቆጠረው ቡድኑ ከነገው ጨዋታ ሦስት ነጥብ ከፈለገ ከመቼውም ጊዜ በላይ ስል ሆኖ መቅረብ አለበት። እርግጥ ቡድኑ ግቦችን ማስቆጠር ብቻ ሳይሆን የግብ ዕድሎችንም በተደጋጋሚ የመፍጠር ችግር አለበት። ከላይ እንደገለፅነው በሰበታው ጨዋታ የታየው ነገር በተወሰነ መልኩ ችግሩ ሊቀረፍ እንደሚችል ፍንጭ የሰጠ ቢሆንም ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ ፊት ላይ አስፈሪ መሆን ይሻዋል። ከዚህ ውጪ መጠነኛ ድክመት የሚታይበት የኋላ መስመሩ በአስተማማኝ ደረጃ ላይ መሆን የግድ ይለዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ቡና ሁሉ ይህንን ዘገባ በምንሰራበት ሰዓት የፈረሰኖቹም የኮቪድ-19 የምርመራ ውጤት ባይደርስም አዲስ ግዳይ እና ሮቢን ንጋላንዴ ባጋጠማቸው ጉዳት የነገው ጨዋታ እንደሚያመልጣቸው ታውቋል።
እርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 41 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 18 ጨዋታ ሲያሸንፍ፤ ኢትዮጵያ ቡና 7 ድል አሳክቷል። በ16 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
– በሸገር ደርቢ ባለፉት 41 ግንኙነቶች 78 ጎሎች ተቆጥረዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 51፤ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 27 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።
* ወቅታዊው የኮቪድ ወረርሺኝ በቡድኖቹ የስብስብ ምርጫ ላይ እያሳደረ ካለው ተለዋዋጭነት አንፃር ግምታዊ አሰላለፍ ለማውጣት አዳጋች በመሆኑ የወትሮው የአሰላለፍ ትንበያችን በዳሰሳው ያልተካተተ መሆኑን እንገልፃለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ