በሀዲያ አሸናፊነት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ አሠልጣኞች የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።
አሸናፊ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና
የዛሬው ሦስት ነጥብ ስላለው ዋጋ?
ቡድኔ ከማሸነፍ ብዙ ርቆ ነበር። ስለዚህ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ዝግጅታችን መልካም ነበር። አሁንም ወደ አሸናፊነት መመለሳችን ለቀጣይ ጨዋታዎች ተስፋ ይሰጣል። በተጨማሪም ለተጫዋቾቹ ተነሳሽነት የዛሬው ድል ጥሩ ነው።
የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ስላደረገው የተጫዋች ለውጥ?
አዲስ ጨዋታውን መቀጠል አቅቶት አደለም። ከዚህም በላይ መጫወት ይችል ነበር። እኔ ግን የፈለኩት የ4-4-2 አጨዋወት መሐል ሜዳ ላይ እንድንበዛ አስተዋፅኦ አላደረገም። ግራ እና ቀኝ ያሉትም ተጫዋቾች ስላላገዙት ብዙ ኳሶች እሱ ጋር ይበላሹ ነበር። ይህንን ለማስተካከል አስበን ነው ለውጡን ያደረግነው። ከእረፍት መልስም አጨዋወታችንን ቀይረን ጥሩ ስራ ሰርተናል።
ስለ ዳዋ እና ዑመድ ብቃት?
ጥሩ ነው። የበለጠ እየተግባቡ እና እየተዋሀዱ ሲሄዱ ለሀገርም ብዙ ነገር ይሰራሉ ብዬ አስባለሁ። ከመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች ለውጦች እና እድገቶች አሉ። ስለዚህ ሁለቱ ተጫዋቾች ቡድኑንም ሆነ ሀገራችንን ይጠቅማሉ ብዬ የማስባቸው አጥቂዎች ናቸው።
ቡድኑ ዘንድሮ ስላለው እቅድ?
ድሬዳዋ ላይ የምናደርጋቸውን ጨዋታዎች ሁሉ አሸንፈን ለመመለስ ነበር ያሰብነው። ባለፈው ግን አዳማ ነጥብ አስጣለን። ውጤቱንም በፀጋ ተቀበልነው። ከዛ ዛሬ ተሻሽለን ቀረብን። ከዋንጫው በጣም የራቅን ይመስለኛል። ተዐምር ካልተፈጠረ በስተቀር ዋንጫው ከፋሲል የሚወጣ አይመስለኝም። ዞሮ ዞሮ ሁለተኛ ሆኖ መጨረስ እና የውድድሩ ጥሩ ተፎካካሪ መሆን የዋንጫ ያህል ነው የሚታየው።
አብዱልሀኒ ተሰማ (ምክትል አሠልጣኝ) – ወልቂጤ ከተማ
ስለ ጨዋታው?
ጨዋታውን በጀመርነው መንገድ መቀጠል ነበረብን። ግን ተጫዋቾቻችን ተጋጣሚ በሚመቸው አጨዋወት በመሄዳቸው ሀዲያዎች ጨዋታውን ተጠቅመውበት ወጥተዋል።
ስለ ረመዳን የሱፍ ብቃት?
ረመዳን እንደ ሌላው ቀን አደለም። ዛሬ ጠብቆ እንዲጫወት ነበር ሀላፊነት የሰጠነው። ነገርግን የሀዲያን ረጃጅም ኳሶች የእኛ ተከላካዮች ሊቆጣጠሩት አልቻሉም። ከዚህ በተረፈ ግን ረመዳን እንደ በፊቱ አጥቅቶ እንዲጫወት ሳይሆን በተሻለ መከላከሉ ላይ እንዲሆን ነበር። በአጠቃላይ ቡድኑ መከላከል ላይ ጥሩ ስላልነበርን እንጂ የረመዳን ብቃት መውረድ አደለም ችግሩ።
ዋና አሠልጣኝ ቡድኑን አለመምራቱ ጫና ፈጥሮብሀል?
ምንም ጫና የለውም። እየተነጋገርን እየሰራን ነበር። እንደተመለከታችሁት ግን ሀዲያዎች ያገኙትን አጋጣሚ ተጠቅመው ሦስት ነጥብ ይዘው ወጥተዋል።
ዕድሎችን ስላለመጠቀማቸው?
መጓገለት ነበር። ከአስር በላይ አጋጣሚዎችን ፈጥረን ነበር። እነዚህን አጋጣሚዊች ብንጠቀም ጨዋታውን ተቆጣጥረን መውጣት እንችል ነበር። ግን ከመጓገለት ጋር በተያያዘ ትንሽ ድክመት ነበረብን። ይህንን ደግሞ በቀጣይ እናስተካክለዋለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ