በሀዲያ ሆሳዕና እና ወልቂጤ ከተማ መካከል የተደረገው የ10 ሰዓቱ ጨዋታ በሀዲያ አሸናፊነት ተጠናቋል።
የሀዲያ ሆሳዕናው አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ ቡድናቸው ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራበት ቋሚ አሰላለፍ ሦስት ተጫዋቾቸን ለውጠዋል። በዚህም አይዛክ ኢሴንዴ፣ ተስፋዬ አለባቸው እና ካሉሻ አልሀሰንን በፀጋሰው ድማሙ፣ አዲስ ህንፃ እና መድሀኔ ብርሀኔን ተክተው ለጨዋታው ቀርበዋል። በተቃራኒው በኮቪድ-19 ህመም ምክንያት ቡድናቸውን ሜዳ መጥተው መምራት ያልቻሉት አሠልጣኝ ደግአረግ ይግዛው በሲዳማ ቡና ከተረቱበት ጨዋታ አራት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም የመጀመሪያ ጨዋታውን የሚያደርገው ዮናታን ፍሰሀን ጨምሮ ዳግም ንጉሴ፣ አብዱልከሪም ወርቁ እና አሜ መሀመድ ቅጣት ላይ የሚገኘውን ቶማስ ስምረቱ እንዲሁም ተስፋዬ ነጋሽ፣ ጂብሪል ናስር እና በኃይሉ ተሻገርን ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
በርከት ያሉ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ወደ ሜዳ ያስገቡት ወልቂጤዎች በ3ኛው ደቂቃ በተገኘ የቅጣት ምት የመጀመሪያ የጨዋታውን ሙከራ አድርገዋል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በተመሳሳይ የቅጣት ምት ያገኙት ሀዲያዎችም አጋጣሚውን በዳዋ ሁቴሳ አማካኝነት ወደ ግብ ልከውት የነበረ ቢሆንም ጀማል ጣሰው በጥሩ ሁኔታ የተመታውን ኳስ አምክኖታል። ተመጣጣኝ ብቃት እየታየበት የቀጠለው ጨዋታው በ19ኛው ደቂቃ ሌላ ሙከራ በተመሳሳይ ከቆመ ኳስ መነሻ ባደረገ እንቅስቃሴ አስተናግዷል። በዚህ ደቂቃ ሱሌማን ሀሚድ ኳስ በእጁ በመንካቱ ምክንያት የተሰጠውን የቅጣት ምት ወልቂጤዎች ሲያሻሙት ከግብ ክልሉ ወጥቶ ኳሱን ያወጣው መሐመድ ሙንታሪ ወደ ቦታው ሳይመለስ ፍሬው በተንጠልጣይ ኳስ ግብ ለማስቆጠር ጥሮ ለጥቂት ወጥቶበታል።
በአንፃራዊነት የሚያገኟቸውን ኳሶች በፍጥነት ወደ ፊት በማድረስ ቀጥተኛ አጨዋወታቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ሀዲያዎች ዑመድ እና ዳዋን ዒላማ ያደረጉ ኳኮችን በረጅሙ ለመላክ ቢሞክሩም ውጥናቸው ሳይሰምር ቀርቷል። በተቃራኒው ኳስን በተሻለ ተቆጣጥረው መጫወታቸውን የገፉበት ወልቂጤዎች በ29ኛው ደቂቃ አሜ መሐመድ ከአብዱልከሪም ወርቁ የደረሰውም ኳስ ከርቀት መትቶት መሪ ለመሆን ጥረዋል። ነገር ግን ተጫዋቹ ወደ ግብ የመታው ኳስ ፊት ለፊት በመሆኑ ሙንታሪ በቀላሉ ተቆጣጥሮታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ፍሬው አሜ ከሞከረው ቦታ በድጋሜ ሌላ ጥቃት ፈፅሞ ነበር።
ጨዋታው ቀጥሎም በ37ኛው ደቂቃ ወልቂጤዎች በድጋሜ የሀዲያን የግብ ክልል የጎበኙበትን ዕድል አግኝተው ነበር። በዚህ ደቂቃም አቡበከር ሳኒ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት ረመዳን የሱፍ ወደ ጎልነት ለመቀየር ጥሮ ነበር። በአጋማሹ ከፍተኛ የፈጠራ ችግር የነበረባቸው ሀዲያዎች በ39ኛው ደቂቃ የአማካይ መስመር ተጫዋች (አዲስ ህንፃ) አሶጥተው የአጥቂ አማካኝ ተጫዋች (ካሉሻ አልሀሰን) በማስገባት የነበረባቸውም ክፍተት ለመድፈን ጥረዋል። ነገርግን የፈጠነው ቅያሪያቸው በመጀመሪያው አጋማሽ ፍሬ ሳያፈራ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ፍጥነት በታከለበት እንቅስቃሴ ታጅቦ የተጀመረው የሁለተኛው አጋማሽ ገና አንድ ደቂቃ ሳያሳልፍ ሁለት አደገኛ ሙከራዎችን አስመልክቷል። በቅድሚያም አጋማሹን የጀመሩት ሀዲያዎች ኳሱን በፍጥነት ወደ ሳጥን ልከውት በመድሃኔ አማካኝነት ፈጣን ጥቃት ፈፅመዋል። ይህንን ሙከራ ከተመለከትን ከሰከንዶች በኋላ ደግሞ ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያሰቡት ወልቂጤዎች ለግብ የቀረበ ዕድል ፈጥረዋል። በዚህም የቡድኑ የፊት መስመር አጥቂ ሄኖክ አየለ ከግራ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በመጠቀም ኳስ ወደ ግብ ቢልክም ለጥቂት ወጥቶበታል።
በዚህኛው አጋማሽ ተሻሽለው የቀረቡት ሀዲያዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ወልቂጤን ማስጨነቅ ይዘዋል። በ54ኛው ደቂቃም ሄኖክ አርፊጮ ባሻገረው እና ዑመድ በግንባሩ በሞከረው ኳስ መሪ ለመሆን ጥረዋል። ይህንን ሙከራ በግንባሩ ያደረገው ዑመድ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በእግሩ ሌላ እጅግ ጥሩ ኳስ ወደ ጀማል ልኳል። በዚህም ተጫዋቹ ከካሉሻ የተሰነጠቀለትን ኳስ በመጠቀም ከሳጥን ውጪ ጥብቅ ኳስ ወደ ግብ ቢመታም የወልቂጤው የግብ ዘብ ጀማል በጥሩ ቅልጥፍና ዕድሉን አምክኖታል። በዚህኛው አጋማሽ ደከም ብለው የታዩት ወልቂጤዎች በ60 እና 61ኛው ደቂቃ ሀዲያን አስደንግጠው ተመልሰዋል። በቅድሚያም ከሁለት ደቂቃዎች በፊት አቡበከርን ቀይሮ የገባው ያሬድ ከፍሬው የደረሰውን ኳስ መረብ ላይ ለማሳረፍ ሞክሯል። በመቀጠልም ለያሬድ ኳስ ያመቻቸው ፍሬው ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ የሀዲያ ተከላካዮች በሚገባ ሳያፀዱት ቀርተው ያገኘውን ኳስ ቡድኑን መሪ ለማድረግ ተጠቅሞበታል። ነገርግን ሁለቱንም ኳሶች ሙንታሪ በጥሩ ቅልጥፍና ተቆጣጥሯቸዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ የነበራቸውን ብልጫ በጎል ለማጀብ የፈለጉት ሀዲያዎች አሁንም የጀማል ጀርባ የሚገኘውን መረብ ፍለቃ አጠናክረው ቀጥለዋል። በተለይም ዳዋ እና ዑመድ ከሳጥን ውጪ በሚመቷቸው ኳሶች ግብ ለማግኘት ታትረዋል። ከምንም በላይ ግን ዳዋ በ70ኛው ደቂቃ ወደ ቀኝ ባዘነበለ ቦታ ላይ ያገኘውን ኳስ በመጠቀም ጥሩ ኳስ ወደ ግብ ልኮ ነበር። ቡድኑም በ73ኛው ደቂቃ የልፋቱን ውጤት አግኝቶ መሪ ሆኗል። በዚህ ደቂቃም ዑመድ ከመሐል የደረሰውን ረጅም ኳስ በመጠቀም ለዳዋ ጥሩ ኳስ አሻግሮለት ዳዋ በግንባሩ ግብ አስቆጥሯል።
መሪነታቸውን ለማስፋት ፍላጎት ያላቸው የሚመስለው የአሠልጣኝ አሸናፊ ተጫዋቾች በ80ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ጎል ለማግኘት ከጫፍ ደርሰው ነበር። በዚህም ተቀይሮ የገባው ዱላ በፈጣን እንቅስቃሴ ወልቂጤ የግብ ክልል ደርሶ የግብ ማግባት ዕድል ቢፈጥርም ዳግም እና ጀማል ኳሱን አምክነውበታል። በድጋሜም ዑመድ ሙሉ የጨዋታ ክፍለጊዜው ሊጠናቀቅ ሦስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ከጠባብ አንግል ጎል ለማስቆጠር ሞክሮ የግቡ ቋሚ መልሶበታል። በመጀመሪያ አጋማሽ የነበራቸውን ብልጫ በዚህኛው አጋማሽ ያጡት ወልቂጤዎች በ89ኛው ደቂቃ በአሜ አማካኝነት የአቻነት ጎል ለማስቆጠር ጥረው ነበር። ጨዋታው ተጠናቆ በተሰጡት ጭማሪ ደቂቃዎች መጀመሪያ ላይ የቅጣት ምት ያገኙት ሀዲያዎች መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ አድርገዋል። በዚህ ደቂቃም የተገኘውን የቅጣት ምት ሄኖክ ሲያሻማው በነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ፀጋሰው ድማሙ አግኝቶት ወደ ግብነት ቀይሮታል። ጨዋታውም በሀዲያ ሆሳዕና 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ ነጥባቸው ሠላሳ ያደረሱት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከነበሩበት አምስተኛ ደረጃ በመሻሻል አራተኛ ደረጃን በጊዜያዊነት ተረክበዋል(ቅዱስ ጊዮርጊስ ነገ እስኪጫወት ድረስ)። በተቃራኒው ሦስት ነጥብ ለተከታታይ ሦስተኛ ጊዜ ያስረከቡት ወልቂጤዎች ወደ ስምንተኛ ደረጃ የሚሻሻሉበትን ዕድል ሳይጠቀሙበት ቀርተው በ20 ነጥቦች ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ፀንተው ተቀምጠዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ