“የከፍተኛ ሊግ ውድድር ምን እንደሚፈልግ ማወቄ ጠቅሞኛል”- አሰልጣኝ እስማኤል አበቡከር

አዲስ አበባ ከተማን ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲመለስ ካስቻለው አሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር ጋር ቆይታ አድርገናል።

እስማኤል አቡበከር በተጫዋችነት ዘመኑ ድንቅ የሚባሉ የስኬት ዓመታትን አሳልፏል። እግርኳስ መጫወት ካቆመ በኋላ በሰዎች ግፊት ሳያስበው ወደ አሰልጣኝነቱ ገብቷል። ከታች በጀመረው የታዳጊዎች ስልጠና በርከት ያሉ ተስፈኛ ወጣቶችን ለእግርኳሱ አብርክቷል። በተለይ በ2008 በሐረር ሲቲ ከ17 ዓመት በታች ቡድን የአሰልጣኝነት ዘመኑ ሚኪያስ መኮንን እና አቡበከር ናስርን ጨምሮ አሁን ለደረሱበት ደረጃ በስልጠናው ረገድ መሠረትን አስይዟል። በ2009 ሚያዚያ ወር ላይ በአሰልጣኝ አሥራት አባተ መልማይነት አዲስ አበባን በምክትል አሰልጣኝነት የመስራት ዕድሉን ያገኘ ሲሆን የመጣበት ወቅት ቡድኑ በፕሪምየር ሊጉ ላለመውረድ እየተንገዳገደ በነበረበት እና በሊጉ መቆየት አቅቶት የወረደበት ጊዜ ነበር።

ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር እስከ 2012 በምክትል አሰልጣኝነት የቆየው አቡበከር በተለይ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ቡድኑ እጅግ ደካማ የውድድር ዓመት በሚያሳልፍበት ወቅት ቁጭቱን በተደጋጋሚ ሲገልፅ የተመለከቱ የክለቡ የበላይ አካላት ሌላ አሰልጣኝ ከመቅጠር ይልቅ የክለቡን ባህሪ ስለሚያውቀው ወደ ዋና አሰልጣኝነት ለማምጣት በመወሰናቸው በትልቅ ደረጃ ዋና አሰልጣኝ የመሆን ኃላፊነቱን በ2013 አዲስ አበባን በማሰልጠን ጀምሯል። እጅግ ባልተገመተ ሁኔታ ልምድ ያላቸውን ከወጣት ተጫዋቾች ጋር በማጣመር ገና ሦስት ጨዋታ እየቀረው ቡድኑን ዳግመኛ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሊመልሰውም ችሏል። ስለ ቡድኑ ጥንካሬ እንዲሁም ለቀጣይ ዓመት ካሁኑ ያለውን ራዕይ አስመልክቶ እስማኤል አቡበከርን ከድሉ በኃላ አናግረነው ይሄን ብሎናል።

ይህ ውድድር በአንድ ቦታ እና በዝግ መደረጉ ምን ጥቅም አስገኘላችሁ?

ብዙ ጠቀሜታዎች ነበሩት። የዛኑ ያህልም የተወሰኑ ጉዳቶችም ነበሩ። ከጠቀሜታው ስነሳ የመጀመርያው ዳኞች ያለምንም ስጋት ትክክለኛውን ውሳኔዎች እንዲወሰኑ ትልቅ እገዛ አድርጓል። ይህ ማለት የእግርኳሱ ዋና አካል ዳኞች ናቸው። ዳኝነቱ ካላማረ ምንም ትርጉም የለውም። የሜዳ ላይ ትልቁን ስነ ልቦና የሚይዘው ዳኛ ነው። ስለዚህ ዳኞቻችን ያላቸውን አቅም ተጠቅመው ህጉን እንዲተገብሩ ጨዋታው አንድ ቦታ መካሄዱ እና በዝግ መሆኑ ጠቅሟል። ሁለተኛው ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ በጉዞ ምክንያት የምታባክነው ጉልበቶች በአንድ ቦታ መካሄዱ ይህን አስቀርቷል። ሌላው ተጫዋቹ እርስ በእርሱ በደንብ እንዲላመድ ያደርጋል። አሁን እኛ አጭር ጊዜ ልጆቹን ያሰባሰብናቸው ስለነበረ በአንድ ቦታ መሰባሰባችን እርስ በእርስ እንዲላመዱ አድርጓቸዋል። በአጠቃላይ የተቃራኒ ቡድን እንቅስቃሴን ለመቃኘት በሁሉም መልኩ ጠቀሜታ ነበረው። ያዛ ኑ ያህል ከቤተሰብ ከልጆች መራቅ ትንሽ ናፍቆቱ አስቸጋሪ ነበር። ሀዋሳ ሦስት ወር ከቤተሰብ ርቀን ከአንድ ሳምንት እረፍት በኃላ ነው በድጋሚ ወደ ወልዲያ የመጣነው። ከቤተሰብ አኳያ መራቁ ፈታኝ ቢሆንም አጠቃላይ ጠቀሜታው ግን የጎላ ነበር።

አአ ከተማን ከ2009 ጀምሮ ታውቀዋለህ… ባለፉት ዓመታት በከፍተኛ ሊጉ እየተንገዳገደ የሚገኝ ቡድን እንደመሆኑ ዘንድሮ ወደ ሊጉ እንዲገባ ያስቻለው የተለየ ጥንካሬ ምንድነው?

በ2009 ሚያዚያ ወር ነው በአሰልጣኝ አሥራት አባተ ምልመላ ገዛኸኝ ወልዴ ሥራ አስኪያጅ በነበረበት ጊዜ ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት። በእኔ ሙሉ እምነት ነበራቸው። ስመጣ ቡድኑ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ነበር። እንዳውም እንደሚወርድ ታምኖ ለ2010 በደንብ ጠንክረን እንድንሰራ ነበር ቦርዱ ውሳኔ ያሳለፈው። በጣም የሚገርምህ እዚህ ወልዲያ ላይ በወልድያ አንድ ለዜሮ ተሸንፈን ነበር መውረዳችንን ያረጋገጥነው። የአሁኑ አጋጣሚ ደግሞ ደስ የሚልህ ወልዲያ ላይ በተደረገ ውድድር ነው ዳግመኛ ወደ ፕሪምየር ሊጉ መመለሳችንን ያረጋገጥነው። ይህ ግጥጥሞች አስገራሚ ነው። በአጠቃላይ በቆየሁባቸው አራት ዓመታት ውስጥ የመጀመርያዎቹ ሁለት ዓመታት ጥሩ ቡድን መስራት ተችሎ የነበረ ቢሆንም በ2011 እና 12 ግን እጅግ የወረደ፣ መጫወት የሰለቸ ተጫዋች የነበረበት ቡድን በመሆኑ በጣም እየተንገዳገደ ነበር የቆየው። እኔ ዋና አሰልጣኝ ሆኜ ቡድኑን ዘንድሮ ስረከብ መጀመርያ ያደረኩት የከፍተኛ ሊግ ውድድር ምን ይፈልጋል የሚለውን ነው ያጠናሁት። ያለፉትን አራት ዓመታት ውድድሩን ስላየሁት ከዛ በመነሳት ሜዳውን ሙሉ አካለው የሚሸፍኑ የሚሯሯጡ ልጆችን መፈለግ አለብኝ ብዬ ተነሳው። በዚህም ትኩረቴን ወጣቶች ላይ በማድረግ ምርጫ አደረኩ። ጎን ለጎንም ልምድ ካላቸው ጋር በማቀናጀት የሠራነው ስራ ውጤታማ አድርጎናል። ሌላው በአቅም እና በአቅም ብቻ የተመሰረተ የተጫዋች አጠቃቀማችን ለውጤቱ ረድቶናል። ተጫዋች በወቅታዊ አቋሙ ሜዳ ላይ ጥሩ ከሆነ ማንም አይነካውም። ከቻለ ይጫወታል። ይህ በዘመድ በጓደኛ በሌላ አላስፈላጊ ነገሮች ተጫዋችን የምናበላልጥበት ነገር አለመኖሩ ለውጤቱ መምጣት ትልቅ አስተዋፆኦ ነበረው።

በዚህ ዓመት አዲስ አበባን ወደ ሊጉ እመልሰዋለው ብለህ አቅደህ ነበር ?

በፍፁም! ምክንያቱም ገና አዲስ ቡድን ነው የሰራነው። ዘንድሮ በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ በማድረግ ልምድ ወስደን በቀጣይ ቡድኑን ወደሚፈለገው ደረጃ ማድረስ ነበር እቅዳችን። ያም ቢሆን ወደ ውድድር ስንገባ ካደረግነው በቂ ዝግጅት እና ከቡድናችን ጥራት አኳያ የተጋጣሚ ቡድኖችን ደረጃ ስንመለከት ለእያንዳንዱ ጨዋታ ትኩረት በመስጠት አመዛኙን ጨዋታ በማሸነፍ ጥሩ ነጥብ በመሰብሰብ ሦስት ጨዋታ እየቀረን ወደ ሊጉ ልንመለስ ችለናል።

ለቀጣይ ዓመት ካሁኑ ያለህ ራዕይ ምንድነው?

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ስለቀጣይ እንዲህ ነው ብሎ መናገር አይቻልም። ጥቀምት ወር ላይ ኮንትራታችን ይጠናቀቃል። ከሚመለከታቸው የክለቡ ቦርድ አመራር ጋር ተነጋግረን ኮንትራታችን ሲታደስ ስለ ክለቡ የቀጣይ ጉዞ እና ራዕይ በተመለከተ የማሳውቅ ይሆናል።

በተጫዋችነትህ የራስህን ስኬት አስመዝግበሀል. አሁን በአሰልጣኝነቱ ወደ ስኬት እየተንደረደርክ ነው ማለት ይቻላል?

ገና ጀማሪ አሰልጣኝ ነኝ። ምንም እንኳን አዲስ አበባን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ዳግም እንዲመለስ ማድረጌ ትልቅ ስኬት ቢሆንም ገና ብዙ ሥራ ይጠበቅብኛል። ስኬት የሚለካው በብዙ መንገድ ነው። ስለዚህ ይህ አሁን የመጣው ውጤት በቀጣይ ጠንክሬ በመስራት ትልልቅ አሰልጣኞች የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ የሚያንደረድረኝ ይሆናል።

አሁን ለተገኘው ውጤት የምታመሰግናቸው አካላት አሉ ?

በመጀመርያ ዋናውን ምስጋና የሚወስዱት ተጫዋቾቼ ናቸው። ታሪካዊ ነገር ስለሰሩ በዚህ አጋጣሚ ተጫዋቾቼን አመሰግናለሁ። በመቀጠል አብረውኝ ያሉት የአሰልጣኝ የቡድን አባላት ይህ ውጤት ለመምጣቱ ትልቁን ሚና ተጫውተዋል ስለዚህ እነርሱን ማመስገን እፈልጋለሁ። ሌላው ያሬድ የማነህ በዕድሜ የኔ የታናሼ ታናሽ የሆነ ወደ ስልጠናው እንድገባ መጀመርያ የነገረኝ እርሱ ነው። ልጆችን ማፍራት እንደምችል ጥሩ ሞራል በመስጠት ከእንግሊዝ ሀገር የስልጠና መፅሀፍትን በመላክ በአቅም እንድጎለብት ያደረገኝ ትልቁ ሰው ያሬድን ማመስገን እፈልጋለው። በማስከተል ባለቤቴ ዚያዳ ሻሚልን አመሰግናለው። እርሷ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ብዙ ነገር በማገዝ ረድታኛለች። ከአንድ ሰው ጥንካሬ ጀርባ አንድ ሴት አለች የሚባለውን በማድረጓ በዚህ አጋጣሚ እንኳን ደስ አለሽ ማለት እፈልጋለው። ሁለቱ የሰፈር ጓደኞቼ ገዛኸኝ መንግሥቴ እና ሀብታሙ አበበ ከሀረር ሲቲ ጀምሮ ቡድኔን እየተከታተሉ እኔን በማበርታት በማገዝ ያላሰለሰ ትልቁን ሚና የተወጡ ጓደኞቼ ናቸው እና አመሰግናለሁ። በመጨረሻም የክለቡን የቦርድ አመራር እና ሥራ አስኪያጁ አቶ ነፃነት ታከለ አምኖብኝ ኃላፊነት ስለሰጠኝ በዚህ አጋጣሚ ከልብ አመሰግናለው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ