የከፍተኛ ሊግ ውሎ| አአ ከተማ ሲያረጋግጥ መከላከያ ተቃርቧል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ አንድ እና ሁለት ጨዋታዎች ተከናውነው አዲስ አበባ ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደጉን ሲያረጋግጥ መከላከያም በእጅጉ የተቃረበበትን ድል አስመዝግቧል።

ረፋድ ላይ ገላን ከተማን የገጠመው መከላከያ 4-0 አሸንፏል። የመከላከያ ረጃጅም ኳሶች እና የገላን ከተማ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት የታየበት ጨዋታው ገና በተጀመረ በ59ኛው ሰከንድ ላይ ከቀኝ መስመር ወደ ግብ ክልል በረጅሙ የተሻገረውን ኳስ ሳሙኤል ሳሊሶ በግንባር ገጭቶ ቴዎድሮስ አካሉ ባዳናት አጋጣሚ ነበር መከላከያዎች ወደ ግብ መጠጋት የጀመሩት። 6ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ገናናው ረጋሳ ከተሰለፈበት የቀኝ የተከላካይ ቦታ ወደ ራሳቸው የሜዳ ክፍል በረጅሙ ወደ ጎል ሲያሻማ የገላኑ ተከላካይ ያሬድ ታረቀኝ ከግብ ጠባቂው ቴዎድሮስ አካሉ ጋር መናበብ ባለመቻሉ በግንባሩ በራሱ ጎል ላይ አሳርፎ መከላከያን መሪ አድርጓል፡፡

ረጃጅም ኳሳቸውን ለመቆጣጠር የተሳናቸው ይመስሉ የነበሩት ገላኖች ሁለተኛ ጎል ለማስተናገድ ተገደዋል፡፡ 13ኛው ደቂቃ ጋናዊው የመስመር አጥቂ ሰሎሞን ዴቪድ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ወደ ግብ ሲመታ ግብ ጠባቂው ቴዎድሮስ አካሉ በአግባቡ መያዝ ሳይችል በመትፋቱ አጠገቡ የነበረው ኤርነስት ባራፎ በቀላሉ ወደ ግብ ለውጦ የመከላከያን የግብ መጠን ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል፡፡

20ኛው ደቂቃ ላይ የመስመር አጥቂው ሰሎሞን ዴቪድ ከገላን ሁለት ተጫዋቾች ጋር መሀል ሜዳ አካባቢ ተጋጭቶ በገጠመው ጉዳት ወደ ሆስፒታል ተወስዷል፡፡ ከስምንት ደቂቃ በኋላ ደግሞ ሳሙኤል ሳሊሶ ከቀኝ በኩል የሰጠውን ልማደኛው ዘካሪያስ ፍቅሬ ሶስተኛዋን ጎል ለመከላከያ በማስቆጠር ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ መከላከያዎች አሁንም በተሻገሪ ኳስ በተጋጣሚው ላይ የግብ ሙከራ የበላይነቱን በመውሰዱ የተዋጣላቸው ሆነው የቀጠሉ ሲሆን በኪቲካ ጅማ ላይ ጥገኛ የማጥቃት አማራጭን ለመጠቀም ብቻ ያሳቡ የነበሩት ገላን ከተማዎች በዚህኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አንፃር ደከም ብለው ቀርበዋል፡፡ ዘካሪያስ ፍቅሬ ባደረገው ሙከራ ወደ ግብ የደረሱት መከላከያዎች 60ኛው ደቂቃ አራተኛ ጎላቸውን አግኝተዋል፡፡ አሚር ሙደሲር በቴዎድሮስ ታፈሰ ላይ በሳጥን ውስጥ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ቴዎድሮስ አስቆጥሮ የመከላከያን የግብ መጠን ከፍ አድርጓል፡፡

ገላን ከተማዎች በከቲካ አማካኝነት ሁለት ሙከራን ብቻ አድርገዋል። ቢኒያም ካሳሁን ከመስመር አሻምቶ ኪቲካ በግንባር ገጭቶ የወጣበት እና አሌክስ ተሰማ ከግብ ጠባቂው ጃፈር ያገኘውን ኳስ በቶሎ ኪቲካ ነጥቆ ብቻውን ከግቡ ጋር ተገናኝቶ የሳተው አስቆጪ ሙከራ ተጠቃሽ ነበሩ፡፡

መከላከያዎች በመጨረሻው ደቂቃ በሰመረ ሀፍታይ አማካኝነት አምስተኛ ጎል ቢያስቆጥሩም ከጨዋታ ውጪ ተብላ ተሽራባቸው ጨዋታው በመከላከያ 4ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ውጤቱን ተከትሎም መከላከያ ከተከታዩ ኤሌክትሪክ በአራት ነጥቦች ርቆ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ መቃረብ ችሏል። ከሁለት ቀሪ ጨዋታዎች አንድ ድል ማስመዝገብም ጦሩነረ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመመለስ በቂ ነው።

ከሰዓት ወሎ ኮምቦልቻን ከ ደብረብርሀን አገናኝቶ ኮምቦልቻ 2-1 አሸንፏል። ለሁለቱም ክለብ አሰልጣኞች ምስጋናን ለማቅረብ በማሰብ ተጫዋቾች ለአሰልጣን ሻምበል መላኩ እና ኤፍሬም ከተበረከተ በኃላ ነበር ጨዋታ የጀመረው። በሊጉ ለመቆየት ብርቱ ፉክክርን ማድረግ የቻሉት ሁለቱ ክለቦች ግብ ማስቆጠርን የጀመሩት ገና ከጅምሩ ነበር፡፡ 10ኛው ደቂቃ ላይ ታምራት በቀለ በግሩም ሁኔታ ከመረብ ባሳረፋት ጎል ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃኖች ቀዳሚ መሆን ችለዋል፡፡

ይሁን እንጂ በመከላከሉ ረገድ የኃላ መስመራቸው ላይ ውጤታማ እንዳልነበሩ የታዩት ደብረብርሃኖች ግብ ተቆጥሮባቸዋል፡፡ 24ኛው ደቂቃ አጥቂው ሲሳይ አቡሌ ቡድኑን አቻ በማድረግ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ በእንቅስቃሴ ካልሆነ ብዙን የጎል አጋጣሚ ለመመልከት ባንታደለም 72ኛው ደቂቃ ላይ ዮናታን ኃይሉ ወሎ ኮምቦልቻን አሸናፊ ያደረገች ጎል በማስቆጠር ጨዋታው 2ለ1 በወሎ ኮምቦልቻ አሸናፊነት ፍፃሜውን ማግኘት ችሏል፡፡

በምድብ ለ መሪው አዲስ አበባ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደጉን ያረጋገጠበትን ድል አስመዝግቧል። ኢኮሥኮን የገጠመው አዲስ አበባ ከተማ 2-0 ሲያሸንፍ ዘርዓይ ገብረሥላሴ እና ፍፁም ጥላሁን የመዲናይቱን ክለብ የድል ጓሎች ማስቆጠር ችለዋል። ድሉም ከተከታዩ ሀምበሪቾ (አንድ ቀሪ ጨዋታ አለው) በ13 ነጥቦች የራቀው አዲስ አበባን ከ2009 በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲመለስ ረድቶታል።

በምድቡ ሌሎች ጨዋታዎች ጋሞ ጨንቻ በአሸናፊ ተገኝ ሐት ትሪክ እና እንዳልካቸው መስፍን አንድ ጎል ካፋ ቡናን 4-2 ሲያሸንፍ ሀምበሪቾ በዳግም በቀለ ጎል ቤንች ማጂ ቡናን 1-0 አሸንፏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ