“ለፍተናል፤ የሚገባንን አግኝተናል” – ም/አሰልጣኝ ዮርዳኖስ ዓባይ (መከላከያ)

መከላከያ ትናንት ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደጉን ካረጋገጠ በኃላ ለአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ስለ ውድድር ዓመቱ ጉዟቸው ቆይታን እንዲያደርጉ ብንጠይቃቸውም ፈቃደኛ ባለመሆናቸውና ” ይሄ ውጤት የተመዘገው በእኔ ሳይሆን በዮርዳኖስ ዓባይ ጥረት በመሆኑ እርሱን ጠይቁት” በማለታቸው ዘንድሮ ክለቡን ተቀላቅሎ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን ቡድኑን ሲመራ ከነበረው ዮርዳኖስ ጋር ትናንት አጭር ቆይታ አድርገናል፡፡

ስለ ውጤቱ

የዛሬው ስሜት በጣም ከባድ ነው። ከዛሬው በፊት የነበሩትን ጨዋታዎች በብቃት ተወጥተን ነው እዚህ የደረስነው። የሚያሸንፍ ቡድን ነው ያለን። ከደብረብርሀን ጋር ያደረግነው ጨዋታ ከዚህ በፊት ከነበረው አንፃር ትንሽ ከባድ ነበር። ከዚህ በፊት በአርባ አምስት ደቂቃዎች ውስጥ ነበር ጨዋታ የምንጨርሰው። ዛሬም ቢሆን የምናረጋግጥበት ስለሆነ ከዚህ ቀደም የነበረንን እንቅስቃሴ ለማሳየት ነበር የሞከርነው። ግን ከብዶን ነበር። እነሱም ላለመውረድ ስለሆነ ታግለዋል። ይሄ ደግሞ እግር ኳስ ነው፡፡ የዛሬው አጋጣሚ እነሱ ለመትረፍ እኛ ደግሞ ለማለፍ ስለነበረ በጣም ከባድ ጨዋታ ነበር ግን አሳክተነዋል፡፡

እቅዳቸውን ስለማሳካታቸው

መቶ ፐርሰንት እንገባለን ብለን ነበር የተነሳነው። ግን ዝም ብለን በቃል ብቻ አይደለም እንገባለን ያልነው። በስራችንም ጭምር ነው፡፡ ከሰራን እንገባለን። ስለዚህ ስራ እንሰራለን፤ ከዛ እንገባለን። የቦርዱም አመራር ቁጭ ብሎ ሲያዋራን በያዝናቸው ተጫዋቾች እንገባለን ብለን ነበር ቃል የገባነው። ግን በቃል ብቻ ሳይሆን ሰርተን በተግባር እንገባለን ብለን ነበር። ያን ደግሞ አድርገነዋል፡፡

የስኬት ቁልፍ

ትልቁ ነገር አሰልጣኝ ዮሐንስ ተጫዋቾቹን ከተሰራ የማይታለፍ የለም ብሎ አሳምኗቸዋል። ከተለፋ ደግሞ መቶ ፐርሰንት እንደሚሳካ ተጫዋቾቹቹ አመኑበት። ስራቸውንም ሰሩ። ከልምምድ ጀምሮ ሁሉም ኮቺንግ ስታፉን ጨምሮ በመስራታችን ይሄን ድል ልናገኝ ችለናል፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን ልፋት ተለፍቷል፤ የሚገባንን አግኝተናል። እውነተኛ የሆነ ልፋትንሞ ዮሐንስ ሳህሌ ለፍቷል። ያንን ልፋቱን ደግሞ በተጫዋቾቹ አይተናል፡፡

ስለ ከፍተኛ ሊግ ፉክክር

 በጣም ከባድ ፉክክር ያለበት ነው። አንደኛ እኛ ጠቅሞናል ብዬ የማስበው ውድድሩ እንደ ቶርናመንት በአንድ ቦታ ቁጭ ብለን መወዳደራችን ነው። ይሄ በመሆኑ ከሁሉ በበለጠ ጥሩ ዓመት እንደነበር መናገር ይቻላል። ተዟዙረህ ስትጫወት ክልል ላይ ነጥብ ማግኘት ያስቸግራል፡፡ ሌላው ብዙም ሰው በኮቪድ የተነሳ ስለማይገባ ዳኞች በነፃነት ያጫውታሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ