የአሠልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 1-1 ድሬዳዋ ከተማ

ጥሩ ፉክክር አስተናግዶ አንድ አቻ ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ከሱፐር ስፖርት ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ታደሰ ጥላሁን (ባህር ዳር ከተማ – ምክትል አሰልጣኝ)

የሚፈልጉትን ስለማግኘታቸው

በተወሰነ መልኩ የምንፈልገውን አግኝተናል ማለት ይቻላል። ግን ይዘን የመጣነውን እንቅስቃሴ ለመተግበር ጨዋታው ግለት ስለነበረው አልቻልንም። እኛ የኳስ ፍሰቱን ጠብቀን በተለመደው አጨዋወታችን ውጤት ይዘን ለመውጣት ነበር ያሰብነው። የቻልነውን ጥረን አቻ ወጥተናል። ጥሩ ነው።

በድሬዳዋዎች ስለተፈጠረባቸው ጫና

አዎ የኛ ተጫዋቾች ኳስ ሲይዙ የመዘግየቱ ሁኔታ ለነሱ ምቹ ነገርን ፈጥሯል። ሌላው እኛ ሜዳ ላይ የምንነካቸው ኳሶች በስህተት የተሞሉ ነበሩ። ፍፁም ቅጣት ምቱም ሆነ ቅጣት ምቱ ሲገኝ ቶሎ የራሳችንን ጎል ለቀን እንድንጫወት የተነጋገርነውን ባለመተግበራችን የተገኙ ናቸው። በአጠቃላይ ከእንቅስቃሴ አንፃር ጥሩ ጨዋታ ነበር።

ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ (ድሬዳዋ ከተማ)

ስለ ውጤቱ ተገቢነት

ጥሩ ነበርን። ባህር ዳር ኳስ መስርቶ ነበር የሚጫወተው። ሜዳቸው ላይም ብዙ ይቆያሉ። እኛ በመልሶ ማጥቃት ጥሩ ነበርን። ጎል የማግባት እድል ፈጥረን፤ የፍፁም ቅጣት ምትም አግኝተን ነበር። አልተጠቀምንበትም እንጂ። እንደዛሬ ጨዋታ ማሸነፍ ይገባን ነበር። ከባህር ዳር በተሻለ ውጤቱ ይገባን ነበር።

ስለ ቡድኑ ተነሳሽነት

ያለንበት ቦታ ያቃጥላል፤ አያስተኛም። ለማሸነፍ መስራት ያስፈልጋል። በተገኘው አጋጣሚ ሦስት ነጥብ በማግኘት በሊጉ መቆየት ያስፈልጋል። ለዛ ነው ጫን እያደረግን የምንጫወተው።

ስለቡድኑ ችግር

ቡድናችን ጥራት ይፈልጋል። ጁንያስ ቢኖር ጥሩ ነበር። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ቡድኑ የተሻለ ነው። ሁሌ እንደምለው የተጫዋቾቹ ብቃት እና ያለንበት ደረጃ አንድ አይደለም። ስለዚህ ማሸነፍ እንፈልጋለን፤ በቀጣዩ የሲዳማ ጨዋታም ውጤት ለማምጣት ጥረት እናደርጋለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ