የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 0-1 ቅዱስ ጊዮርጊስ

ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስአበባ ውጭ ከተደረገውና ቅዱስ ጊዮርጊስ በአስቻለው ታመነ ብቸኛ ግብ ከረተታበት የሸገር ደርቢ መጠናቀቅ በኃላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

ፍራንክ ናታል – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ወደ ጨዋታው ይዘውት የገቡት እቅድ ውጤታማ ስለመሆኑ

“በሚገባ ከፍ ባለ ፍጥነት ጨዋታውን ለመጀመር ሞክረናል እሱም ተሳክቶልናል። ለሁለታችንም ሜዳው እጅግ ፈታኝ ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ ተጨማሪ ግብ ሊሆኑ የሚችሉ እድሎችን ፈጥረን ነበርነበር። በጥቅሉ ግን ድሉ ይገባን ነበር። በተጨማሪም ሁለቱን ቡድኖች በዚህ አስቸጋሪ ሜዳ የተቻላቸውን ነገር ሜዳ ላይ ለማድረግ ስለሞከሩ ማመስገን እፈልጋለሁ። ስላሸነፍንም ደስ ብሎኛል።”

የዛሬው ጨዋታ መንገዳቸው ለሌሎች ጨዋታዎች ፍንጭ የሰጠ ከሆነ

“አይደለም፤ ከጨዋታ ጨዋታ የሚለወጥ ነገር ይኖራል። ቀሪ ሰባት ጨዋታዎች አሉ። እነሱን ጨዋታ በጨዋታ እያደረግን እንሄዳለን። ይህን ድል በቅድሚያ እናጣጥማለን። ከዛ እገግመን ለቀጣዩ ጨዋታ እንዘጋጃለን። በቀጣይ ጨዋታ ደግሞ የሚሆነውን እንመለከታለን።”

በጨዋታው የእርሳቸው ኮከብ ስለነበረው ተጫዋች

“በዛሬው ጨዋታ ተጫዋቾች ሜዳ ላይ አስራ አንድ መሪዎች እንዲኖሩኝ ጠይቄያቸው ነበር። ሜዳ ላይ የተመለከትኩትም ይሄን ነው። ስለዚህ በዛሬው ጨዋታ የኔ ኮከብ ቡድኑ ነው።”

ካሣዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

እስከ 30ኛው ደቂቃ መቸገራቸው

“ከሀዋሳ እና ከድቻ ጋር የተጫውትናቸው ጨዋታዎች እንደዚሁ ተመሳሳይ ነበሩ። አንዳንዴ ቡድኖች የሚቀርቡበት መንገድ ተጫዋቾችን በራሳቸው ሜዳ አብዝተው ስለሆነ የግድ ቦታዎችን ለማግኘት መታገስ ያስፈልጋል። አንዳንድ ጊዜ ልክ እንደ አንተ ከፍቶ የሚጫወት ተጋጣሚ ስታገኝ የሚገኙ ክፍተቶችን ለመጠቀም ትሞክራለህ። ግን በዚህ በኩል ክፍት ሜዳዎችን ዘግቶ የሚመጣ ቡድን ሲኖር ትክክለኛ የመሞከርያውን ቦታ እስክታገኝ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ”

ስለዊልያም ሰለሞን ቅያሬ

“ሜዳው ኳስ ይይዛል፤ ስታቀብለም ሆነ ስተገፋ ኳስ ይይዛል። ስለዚህ እሱ በተመቸ ሜዳ ላይ ነው ያለበለዚያ ብዙ ንክኪ እና ትግል በሚጠይቀው አይነት ነገር ውስጥ ሲሆን ሊቸገር ይችላል። ብዙ ኳሶች እየቀሩበት እየወሰዱበት ነበር። በዚህ መንገድ ለመቀጠል እሱ ምቹ አልነበረም። ለዚህም ነበር የቀየርነው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ