ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ የሸገር ደርቢን አሸንፏል

በ19ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአስቻለው ታመነ ብቸኛ ግብ ኢትዮጵያ ቡናን 1-0 ማሸነፍ ችሏል።

ኢትዮጵያ ቡናዎች ሰበታን ሲያሸንፉ ከተጠቀሙበት አሰላለፍ ውስጥ ሁለት ለውጦችን ሲያደርጉ ምንተስኖት ከበደ እና አማኑኤል ዮሐንስ በወንድሜነህ ደረጄ እና ሬድዋን ናስር ምትክ ተሰልፈለዋል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግሞ ከሰበታ ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ በደስታ ደሙ ፣ ምንተስኖት አዳነ ፣ እና አቤል ያለው ምትክ ሄኖክ አዱኛ፣ አብዱልከሪም መሐመድ እና ጋዲሳ መብራቴን ለውጠው ቀርበዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጨዋታውን ጫን ብለው ነበር የጀመሩት። በቀዳሚዎቹ ደቂቃዎች ከቆሙ ኳሶች መነሻነት ያደረጓቸው ሙከራዎችም ለግብ የቀረቡ ነበር። የጋዲሳ መብራቴ የቀኝ መስመር ቅጣት ምት በግቡ ቋሚ ሲመለስ ከደቂቃዎች በኋላ ጌታነህ ከበደ የመታው ወደ ግራ ያዘነበለ ሌላ ቅጣት ምትም በአቤል ማሞ የተመለሰ ነበር። ይህ ኳስ ወደ ውጪ ከወጣ በኋላ የተሰጠውን የማዕዘን ምትም ጋዲሳ ሲያሻማ አስቻለው ታመነ በግንባር በመግጨት 12ኛው ደቂቃ ላይ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ከግቡ በኋላም ጨዋታው በተመሳሳይ መልኩ የቀጠለ ነበር በሳጥኑ ዙሪያ ተደጋጋሚ የቅጣት ምቶችን ያገኙ የነበሩት ጊዮርጊሶች ብልጫውን ወስደው መቀጠል ችለዋል። ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ምት እየገቡ እና ቅብብሎቻቸው እየታዩ የመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች መሀል ሜዳውን የተሻገሩባቸው አጋጣሚዎች መፈጠር ቢጀምሩም በተደጋጋሚ ኳሶች ይቋረጡባቸው ነበር። በመሆኑም ቀጣዮቹን ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎችን መፍጠር የቻሉትም ጊዮርጊሶች ነበሩ። 23ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አዱኛ አማኑኤል ገብረሚካኤልን ከግብ ጠባቂ ጋር ያገናኘበትን ኳስ አማኑኤል ሲሞክር አቤል ማሞ ያዳነበት ሲሆን ጌታነህ በድጋሚ ሞክሮት አቤል አሁንም አውጥቶበታል።

34ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉዓለም መስፍን አሻምቶት ጌታነህ በግንባር ሞክሮ ከወጣበት ኳስ በኋላ ቡናዎች የተሻለ ከጫና ወጥተዋል። የጊዮርጊስን ፈጣን ጥቃቶች ማብረድ እንዲሁም በተሻለ ሁኔታ ኳስ ይዘው ከሜዳቸው መውጣት ቢጀምሩም የመጨረሻ የግብ ዕድል መፍጠር ላይ ግን እምብዛም አልነበሩም። 35ኛው ደቂቃ ላይ ሚኪያስ መኮንን ከሳጥን ውጪ የመታው እና ባህሩ ጥላሁን በቀላሉ የያዘው ኳስም በመጀመሪያው አጋማሽ የታየ የቡና ሙከራ ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀንን በዊልያም ሰለሞን ምትክ ቀይረው ያስገቡት ቡናዎች አማካይ ክፍላቸው ላይ የተሻለ ጉልበት ጨምረዋል። በታፈሰ ሰለሞን አማካይነት ከሳጥን መግቢያ ላይ ሙከራ በማድረግ ጀምረውም ከዕረፍት በፊት ከነበረው በተሻለ ወደ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ሲቀርቡ ታይተዋል። ነገር ግን አደገኛ ሙከራዎችን በማድረጉ አሁንም የተሻሉ የሆኑት ጊዮርጊሶች በሀይደር ሸረፋ እና ጌታነህ ከበደ ሌሎች ሙከራዎችን ማድረጋቸው አልቀረም። አሁንም ከቆሙ ኳሶች ጫና መፍጠር ያላቆሙት ጊዮርጊሶች 64 ኛው ደቂቃ ላይ ባሻሙት ኳስ መነሻነት በተፈጠረ ግጭት ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው አቤል ማሞ በተክለማርያም ሻንቆ ለመቀየር ተገዷል።

ብርቱ ፉክክር እየታየበት በቀጠለው ጨዋታ ጊዮርጊሶች ተጋጣያቸው ኳስ እንዳይጀምር ጫና ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ቡናዎች በቅብብሎቻቸው በጊዮርጊስ ሳጥን አቅራቢያ የሚታዩባቸው ቅፅበቶች ጨምረዋል። በተለይም 69ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ናስር ከሚኪያስ መኮንን ተቀብሎ ከቀኝ ያደረሰውን ኳስ አስራት ቱንጆ ለማስቆጠር ቢቃረብም ባህሩ በቅልጥፍና አድኖበታል።

የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሙከራዎች አይታዩባቸው እንጂ ሜዳ ላይ የነበረው የቡድኖቹ የደርቢ ስሜት ያለው ፍልሚያ እስከፍፃሜው የዘለቀ ነበር። ቡናዎች ተሻሽለው በታዩበት አጋማሽ ባሰቡት መጠን እንደወትራቸው ሳጥን ውስጥ ከኳስ ጋር በቁጥር በርከት ብለው መድረስ ያልቻሉ ሲሆን የጊዮርጊሶች ረጃጅም ኳሶችም ከባድ የመልሶ ማጥቃት ዕድል ሲፈጥሩ አልታየም። 86ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ሞክሮት በተክለማሪያም የተመለሰው እና እሱን ተከትሎ በድጋሚ ጌታነህ ከማዕዘን ምት በግንባሩ ያደረገው ሌላ ሙከራ የጨዋታው ፍፃሜ የተሻሉ አጋጣሚዎች ሆነዋል።

ጨዋታው በጊዮርጊስ 1-0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ታፈሰ ሰለሞን የአርቢትሩን ፊሽካ ተከትሎ ኳስ በመለጋቱ የኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ ሁለተኛ ቢጫ ካርድ ሰለባ ሆኗል።

በውጤቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አራተኝነት መመለስ ሲችል ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከረጋው ኢትዮጵያ ቡና ጋር የነበራቸው ልዩነትም ወደ ሦስት ነጥብ ዝቅ ብሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ