ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

19ኛ የጨዋታ ሳምንቱ ላይ በደረሰው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተመለከትናቸው እና ትኩረት የሳቡ ክለብ ነክ ጉዳዮችን በዚህ ፅሁፍ ለመዳሰስ ሞክረናል።

👉 በፈተናዎች አልበገር ያሉት ዐፄዎቹ

ፋሲል ከነማ እውነተኛ አሸናፊ ቡድን መሆኑን አሁንም በዚህ ሳምንት አስመስክሯል። ለጨዋታ እጅግ ፈታኝ በነበረው ሜዳ ከሰሞኑ ጥሩ መነቃቃት ላይ የነበረው ሲዳማ ቡናን የገጠሙት ዐፄዎቹ ከተጋጣሚያቸው እጅግ ከባድ ፈተና ቢገጥማቸውም በስተመጨረሻ ድል አድርገው መውጣት ችለዋል።

ገና በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ሙጂብ ቃሲም ባስቆጠራት ግብ ፋሲሎች መምራት ቢችሉም ቀስ በቀስ በጨዋታው እያደጉ የመጡት ሲዳማዎች ቡናዎች የመጀመሪያው አጋማሽ እስኪጠናቀቅ በጨዋታው የበላይ ነበሩ። በዚህም ተደጋጋሚ አስቆጭ የግብ ሙከራዎችን በማድረግ ፋሲሎችን መፈተን ችለው ነበር። ከዚያም አልፎ ከዕረፍት መልስ ኦኪኪ አፎላቢ ግብ አስቆጥሮ ሲዳማዎች ይገባቸው የነበረውን አቻነት አስገኝቶላቸው ነበር። ቅያሬዎችን በማድረግ የበላይነቱን ያገኙት ፋስሎች ግን በሁለት አጥቂዎች ከመስመር የሚሻገሩ ኳሶችን ለመጠቀም ያረጉት ጥረት ሰምሮ 86ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ፍቃዱ ዓለሙ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ በግንባሩ አስቆጥሮ ቡድኑን ባለድል አድርጓል።

አሸናፊ ቡድኖች የተሻሉ በሆኑበትም ሆነ በተጋጣሚያቸው ብልጫ ተወስዶባቸው በተቸገሩበትም ጨዋታ እንኳን ቢሆን ጨዋታዎችን በየትኛውም ዓይነት መንገድ አሸንፈው ይወጣሉ። አፄዎቹ ይህን ሂደት በተደጋጋሚ በዘንድሮው የውድድር ዓመት እያስመለከቱን ይገኛሉ። ቡድኑ የተቸገረ ቢመስልም በመጨረሻም ከጨዋታዎች በአሸናፊነት ብቅ ያሉባቸው አጋጣሚዎች እየተበራከቱ መጥተዋል።

ይህን ጨዋታ ማሸነፋቸውን ተከትሎ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከባህርዳር ከተማ ጋር ነጥብ በመጋራታቸው በተወሰነ መልኩ የጠበበ ይመስል የነበረው ልዩነት ደግም በተከታዩ ኢትዮጵያ ቡና ነጥብ መጣል መነሻነት ወደ 12 ከፍ ብሏል።

👉 ፈረሰኞቹ በሸገር ደርቢ ደምቀዋል

ከሦስት ነጥቦች ጋር ተራርቀው የከረሙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሸገር ደርቢ ኢትዮጵያ ቡናን በአስቻለው ታመነ ብቸኛ የግንባር ኳስ በማሸነፍ ከአራት ጨዋታዎች በኃላ ወደ ድል ተመልሰዋል።

እንደ መጀመሪያው ዙር ጨዋታ ሁሉ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ኳሶችን ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ይዘው እንዳይወጡ ከፍተኛ ጫናን በማሳደር በጀመሩት ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ከሜዳውም ጭቃማነት ጋር ተዳምሮ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ተደጋጋሚ ጥፋቶች እና ስህተቶችን ለመስራት ተገደዋል። በዚህም ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሁለት አጋጣሚዎች ከቆሙ ኳሶች በቀጥታ ሁለት አደገኛ ሙከራዎችን አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ከኳስ ጋር በቂ ጊዜ እንዳያገኙ ምቾት መንሳት የቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ12ኛው ደቂቃ አስቻለሙ ታመነ በግንባር በመግጨት ካስቆጠራት ግብ በተጨማሪ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችንም መፍጠር ችለዋል። በሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጠኑም ቢሆን ከጊዮርጊሶች ጫና መውጣት ቢችሉም ወደ ጊዮርጊስ ሜዳ የሚያድጉት ኳሶች እምብዛም አደጋ ሲፈጥሩ አልተመለከትንም።

ጥሩ ፉክክር በታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በፈረሰኞቹ የበላይነት መጠናቀቅ ተከትሎ ፈረሰኞቹ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሦስት በማጥበብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተመልሰዋል።

👉በሽንፈት ውስጥ እንኳን አንገታቸውን ቀና አድርገው የወጡት ወላይታ ድቻዎች

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተፅዕኖ እጅጉን እያየለ መጥቷል። በ19ኛ የጨዋታ ሳምንት ወላይታ ድቻ እና ሀዋሳ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ግልጥልጥ አድርጎ ያሳየ ነበር። በሁለቱም ተጋጣሚ ቡድኖች በኩል በድምሩ በጨዋታ ዕለት ስብስብ ውስጥ ከተካተቱት 24 ተጫዋች ውጪ የቀሩት የሁለቱ ቡድኖች ተጫዋቾች በቫይረሱ በመያዛቸው ተከትሎ ሁለቱም ቡድኖች እጅግ ፈታኝ የነበረ የጨዋታ ዕለትን አሳልፈዋል።

ወላይታ ድቻዎች በጨዋታው ሁለት ግብጠባቂዎችን በሜዳ ላይ ተጫዋችነት በመጀመሪያ 11 ሲያካትቱ በኮሮና ከፉኛ የተመታው ስብስባቸው ያለ ተጠባባቂ ተጫዋች ጨዋታቸውን አድርገዋል። በተመሳሳይ ሀዋሳ ከተማዎች እንዲሁ ከመጀመሪያ ተመራጫቻቸው ውጪ ሁለት ተጫዋቾችን ብቻ (አንድ ግብጠባቂ እና አንድ የሜዳ ላይ ተጫዋች) ብቻ ይዘው ጨዋታቸውን አድርገዋል።

እርግጥ በሊጉ ተካፋይ የሆኑ ክለቦች መጠኑ ይለያይ እንጂ በኮሮና ቫይረስ ክፉኛ እየተቸገሩ ቢገኝም በወላይታ ድቻ ረገድ የዚህ ቫይረስ ተፅዕኖ ያረፈበትን ቡድን ፈልጎ ማግኘት እጅጉን ይከብዳል። ከጥቂት ቀናት በፊት በ17ኛ የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ በፋሲል ከነማ 2-0 በተሸነፈበት ጨዋታ በርካታ ቁጥር ያላቸው የቡድኑ የመጀመሪያ ተመራጭ ተሰላፊ ተጫዋቹ በቫይረሱ በመያዛቸው ሳቢያ ብዙ ለውጦችን አድርጎ ለጨዋታ መቅረቡ ይታወሳል።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንትም ቡድኑ የመጀመሪያ 11 ተሰላፊ ተጫዋቾቹን ለማሟላት እጅጉን ተፈትኗል። ይህን ክፍተት ለመድፈንም የቡድኑ ተጠባባቂ ግብ ጠባቂዎች የሆኑት መክብብ ደገፉ እና አብነት ይስሀቅ ከተመለመደው የግብ ጠባቂነት ሚናቸው ውጪ የወላይታ ድቻን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመምራት በአጥቂነት ተሰልፈው ቡድናቸው ማገልገል ችለዋል። በተጨማሪም የተከላካይ አማካዩ በረከት ወልዴም እንዲሁ የሚና ሽግሽግ በማድረግ በግራ የመስመር ተከላካይነት ጨዋታውን አድርጓል።

የወላይታ ድቻ የቡድን ስብስብ ይፋ ከተደረገበት ወቅት አንስቶ ብዙዎች ወላይታ ድቻዎች ይህን ጨዋታ እንዴት ይወጡት ይሆን የሚል ስጋቶች የነበረባቸው ቢሆንም የጨዋታ ሂደት ግን ከእዚህ በተቃራኒ ነበር ማለት ይቻላል። ድቻዎች ገና ከጅምሩ ብዙዎች ጥንቃቄን ይመርጣሉ ተብሎ ቢገመትም ከጅምሩ ኳሶችን በሚያገኙባቸው ቅፅበቶች በጀብደኝነት በማጥቃት ግቦችን የማስቆጠር ፍላጎት እንደነበራቸው ተመልክተናል።

በጨዋታው ወላይታ ድቻዎች አስቀድመው ግብ ቢያስተናግዱም ሳይጠበቁ በእንድሪስ ሰዒድ እና ደጉ ደበበ አማካኝነት በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት ባስቆጠሯቸው ግቦች ጨዋታውንም መምራት ችለው ነበር ። ምንም እንኳን የመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት አቻ በሆነ ውጤት ቢጠናቀቅም ድቻዎች በመጀመሪያ አጋማሽ የነበራቸው እንቅስቃሴ ጥሩ የሚባል ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ እንዲሁ ያለ ተጠባባቂ ተጫዋች ጨዋታ እንደማድረጋቸው ጉልበታቸውን ቆጥበው ሊጫወቱ ይችላል ተብሎ ቢገመትም በአመዛኙ በሁለተኛው አጋማሽም እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በተሻለ ፍላጎት ለመጫወት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ችለዋል።

ጨዋታው በአቻ ውጤት ለመጠናቀቅ በተቃረበት ወቅት በ88ኛው ደቂቃ በሀዋሳ ከተማዎች በኩል በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገባው እና በጨዋታው በተደረገው ብቸኛ ለውጥ ወደ ሜዳ የገባው ዘላለም ኢሳያስ ባስቆጠራት ግብ ሀዋሳ ከተማ ከጨዋታው ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል።

በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ ሆነው ጨዋታቸውን ያደረጉት ወላይታ ድቻዎች በንፅፅር የተሟላ ስብስብ የነበረውን ሀዋሳ ከተማ ጋር ብርቱ ፉክክር አድርገው በስተመጨረሻ በተቆጠረችባቸው ግብ ነጥብ ቢያጡም በጨዋታው ወቅት ሜዳ ላይ የነበሩት የቡድኑ ተጫዋች ያሳዩት አስደናቂ ትጋት እና ቁርጠኝነት በልዩነት ውዳሴ የሚገባው ነው። ቡድኑ ከቀናት በፊት በፋሲል ከነማ እንዲሁም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ሽንፈትን ቢያስተናግድም ተሸንፈውም ቢሆን አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲወጡ የሚያበቃ አስደናቂ የሜዳ ላይ ብቃትን አሳይተዋል።

👉 ውጤታማው የሀዲያ ሆሳዕና አቀራረብ

ከሰሞኑ መነጋገርያ ሆኖ የሰነበተው ሀዲያ ሆሳዕና በ19ኛው ሳምንት ደግሞ ሌላው ሰሞነኛ የውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘውን ወልቂጤ ከተማን 2-0 በመርታት ወደ አሸናፊነት የተመለሱበትን ውጤት አግኝተዋል።

ተጋጣሚያቸው ወልቂጤ ከተማዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እንደሚወስድባቸው የተረዱት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በተለምዶ ኳስን ለመቆጣጠር የሚፈልጉ ቡድኖች ወደ ተጋጣሚ የሜዳ አጋማሽ ተጠግተው ለመጫወት በሚያደርጉት ጥረት ለማጥቃት ከሚፈልጉት የሜዳ ክፍል የሚልቅ የሜዳውን ክፍል ትተው እንደምጣታቸው ሀዲያዎች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ከወልቂጤ ከተማ ተከላካዮች ጀርባ የሚገኘውን የሜዳ ክፍል ለማጥቃት ያደረጉት ጥረት በስተመጨረሻ ፍሬ አፍርቶላቸዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ በተለይ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በተወሰኑ አጋጣሚዎች ውጭ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴያቸው እምብዛም ውጤታማ አልነበሩም ነገርግን በሁለተኛው አጋማሽ ከአልሀሰን ካሉሻ ወደ ሜዳ መግባት ጋር በተያያዘ ሀዲያዎች እነዚህን የሚከፈቱ የሜዳ ክፍሎችን ለማጥቃት የሚያደርጉት ጥረት ውጤታማ ነበር። በተለይም ይህ ሂደት ዳዋ ሆቴሳ ባስቆጠራት የመጀመሪያዋ ግብ ላይ በደንብ የተስተዋለ ሲሆን በዚሁ ሂደት ተደጋጋሚ አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩም መጠቀም አልቻሉም።

በሜዳ ውጪ ባሉ ሁነቶች መነሻነት የሜዳ ላይ ውጤቱ እየታደከመ ለሚገኘው ቡድኑ ወልቂጤ ከተማን የረታበት ድል ለቡድኑ ከፍተኛ መነሳሳትን ይፈጥራል ተብሎ ይገመታል።

👉ውጤት ማስጠበቅ የተሳነው ጅማ አባ ጅፋር

በሊጉ የእስካሁኑ የ19 ሳምንታት ጉዞ የጅማ አባ ጅፋርን ያህል እየመራ ነጥብ የጣለ ቡድን ማግኘት አይቻልም። ጅማ አባ ጅፋሮች በእስካሁኑ የሊግ ጉዞ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በሰበታ ከተማ የተሸነፉበትን ጨዋታ ጨምሮ በሰባት ጨዋታዎች ላይ ከመምራት ተነስተው ሙሉ ነጥብ አጥተው ወጥተዋል።

ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ውስጥ በአስራ አንድ ነጥቦች አስራ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቡድኑ በእነዚሁ ሰባት ጨዋታዎች በእጃቸው ገብቶ የነበረውን መሪነት ማስጠበቅ ቢችሉ ኖሮ አሁን ላይ ቡድኑ ከመውረድ ስጋት ተላቆ ወደ ሰንጠረዡ አናት መጠጋት በቻለ ነበር።

ከዚህ የውጤት ማጣት በስተጀርባ የቡድኑ አጨዋወት መንገድ ወጥነት መጉደሉ ዓይነተኛ ምክንያት ሲሆን እንመለከታለን። የቡድኑ አጨዋወት በጥቅሉ ከአዎንታዊነት ይልቅ ወደ አሉታዊነት ያደላ ቢሆንም ቡድኑ በተሻለ መነሳሳት በተለይ በመልሶ ማጥቃት የሚገኙ ዕድሎችን በተሻለ ጥራት ማስቆጠር በቻሉባቸው ጨዋታዎች ሁሉ ግብ ካስቆጠረ ወዲህ ይበልጥ ግብ ያገኙበትን መንገድ ለማስቀጠል ጥረት ከማድረግ ይልቅ የተገኘችውን ግብ ለማስጠበቅ ጥንቃቄን ምርጫቸው ሲያደርጉ ይስተዋላል።

መሰል አጨዋወቶች ደግሞ ተጋጣሚ ቡድኖች ይበልጥ ጨዋታውን ተቆጣጥረው ተደጋጋሚ ጫናዎችን እንዲፈጥሩ ዕድሎችን የሚሰጥ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ቡድኑ በተደጋጋሚ ግቦችን እያስተናገደ ይገኛል። ይህም ጅማ ላለመውረድ በሚያደርገው ጥረት ላይ ተግዳሮት እየሆነበት ይገኛል።

👉 ዕድለ ቢሱ ድሬዳዋ ከተማ

በ19ኛ የጨዋታ ሳምንት ጭቃማ በነበረው የድሬዳዋ ስታድየም እጅግ ማራኪ በነበረው የድሬዳዋ ከተማ እና ባህርዳር ጨዋታ አንድ አቻ ተጠናቋል። ጨዋታው እንደ ወትሮዎቹ ሁሉ ድሬዳዋ ከተማ የነበራቸውን ጥሩ የሚባል የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በውጤት ማጀብ ተስኗቸው የተስተዋለበት ጨዋታ ሆኗል።

በጨዋታው ድሬዳዋ ከተማዎች በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ከፍ ባለ ተነሳሽነት ጨዋታውን መጀመር የቻሉ ሲሆን የቡድኑ አሰልጣኝ ከጨዋታው በፊት እንደናገሩት ቡድኑ በሁሉም መንገዶች ለማጥቃት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ ለወትሮው ብዙም በማጥቃቱ ተሳትፎ ያልነበራቸው ሁለቱ የተከላካይ አማካዮች ጭምር ከፍተኛ ጥረቶችን ሲያደርጉ ተመልክተናል። በተለይም ኳስን በሚያጡበት ወቅት ከፍ ባለ ብርታት እንደ ቡድን ኳስን መልሶ ለማግኘት ያደርጉት የነበረው ጥረት እጅግ ድንቅ ነበር።

በጨዋታውም ሄኖክ ኢሳያስ ከቅጣት ምት ባስቆጠራት ግብ መምራት ቢችሉም መሪነታቸው መዝለቅ የቻለው ለአስር ያህል ደቂቃዎች ብቻ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ እንዲሁ የተሻለ ለመንቀሳቀስ የሞከሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኙም በመጀመሪያው አጋማሽ ከቅጣት ምት ያደረጋት አስደናቂ ሙከራ በግቡ አግዳሚ የተመለሰበት ዳንኤል ኃይሉ ፍፁም ቅጣት ምቱን መጠቀም ሳይችል ቀርቷል።

በአስራ ሰባት ነጥቦች አስረኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች ከወራጅ ቀጠና ለመራቅ በሚያደርጉት ትግል በጨዋታው የተሻለ በሚንቀሳቀሱባቸው ቅፅበቶች የሚገኙ የግብ አጋጣሚዎችን ስልነት ተላብሰው ወደ ግቦች መቀየር ተቀዳሚ የቤት ሥራቸው ይሆናል። በተጨማሪም ቡድኑ በርካታ ኳሶች በግብ አግዳሚ እና ቋሚ የተመለሰበት መሆኑ ይታወቃል ታድያ ይህ አጋጣሚ ከዕድለ ቢስነት ብቻ ሳይሆን ከአጥቂዎቻቸው የሥልነት ጉዳይ ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ነውና አሁንም ቢሆን በአፋጣኝ መሻሻሎችን ማሳየት ይጠበቅበታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ