አርባምንጭ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመመለስ መንገዱን አመቻችቷል

ትናንት ወሳኝ ጨዋታ ያሸነፈው አርባምንጭ ከተማ የተከታዩን ነጥብ መጣል ተከትሎ ወደ ፕሪምየር ሊግ የማደግ ዕድሉን ከፍ አድርጓል።

ትናንት በምድብ ሐ 19ኛ ሳምንት ቀግተኛ ተፎካካሪው ከሆነው ኢትዮጵያ መድን ጋር ጨዋታውን ያደረገው አርባምንጭ ከተማ አላዘር ዝናቡ በመጀመርያ እንዲሁም ፍቃዱ መኮንን በመጨረሻ ደቂቃ ባስቆጠሯቸው ጎሎች 2-1 ማሸነፍ የቻለ ሲሆን በዚህም ነጥቡን 43 በማድረስ ዛሬ ጨዋታውን ካደረገው ኮልፌ ቀራኒዮ ያለውን ልዩነት ስድስት ማድረስ ችሎ ነበር። ዛሬ ከካምባታ ሺንሺቾ ጋር ጨዋታውን ያደረገው የሊጉ አስገራሚ ቡድን ኮልፌ ቀራኒዮ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት በመለያየቱ በመሳይ ተፈሪ የሚመራው አርባምንጭ መሪነቱን በአምስት ነጥብ ልዩነት ማድረግ ችሏል።

የምድብ ሐ ሊጠናቀቅ ሦስት ጨዋታዎች ብቻ የቀሩ ሲሆን አርባምንጭ ከቀሪ ጨዋታዎች ሁለቱን ማሸነፍ አልያም የሌሎቹ ነጥብ መጣል ወደ 2014 ፕሪምየር ሊግ እንዲያድግ ያስችለዋል።

በ2004 ወደ ፕሪምየር ሊግ አድጎ በአካባቢው በተገኙ ተጫዋቾች ጠንካራ ቡድን በመገንባት በሊጉ ሲፎካከር የቆየው አርባምንጭ በ2010 የውድድር ዘመን ከሊጉ መውረዱ የሚታወስ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ