ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

በ19ኛ ሳምንት የጨዋታ መርሐግብሮች በርከት ያሉ ለየት ያሉ ሁነቶችን ያስተናገደ ነበር። እኛም በዚሁ ሳምንት የታዘብናቸውን ተጫዋች ነክ ጉዳዮች በተከታዩ ፅሁፍ ለመዳሰስ ሞክረናል።

👉በድንገት ወደ ሜዳ ላይ ተጫዋችነት የተቀየሩት ግብጠባቂዎች

በጨዋታ ሳምንቱ እጅጉ መነጋገርያ ከነበሩ ጨዋታዎች ግንባር ቀደም በነበረው እና በኮቪድ ክፉኛ የተመቱትን ሁለቱን ቡድኖች ባገናኘው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ወላይታ ድቻን 3-2 መርታቱ ይታወቃል።

በዚህ ጨዋታ ወላይታ ድቻዎች ሦስት ግብጠባቂዎችን በመጀመሪያ ተሰላፊነት ያስጀመሩ ሲሆን ዳንኤል አጃይ የቡድኑን ግብ ጠብቋል፤ ሁለቱ ደግሞ (መክብብ ደገፉ እና አብነት ይስሀቅ) በቋሚዎቹ መካከል በመቆም ግብን ከመጠበቅ በድንገት በመጨረሻው የማጥቃት ወረዳ ላይ የቡድናቸውን የፊት መስመር እየመሩ ወደ መጫወት የተሸጋገሩበት ጨዋታ ነበር።

በቁመት ዘለግ ያለው አብነት ይስሀቅ 23 ቁጥር መለያን ለብሶ የመጨረሻ አጥቂ ሆኖ ሲጀምር 17 ቁጥር ለብሶ ወደ ሜዳ የገባው ሌላኛው ግብ ጠባቂ መክብብ ደገፉ ከአብነት በስተጀርባ ከአማካዮቹ ትንሽ ወደፊት በተጠጋ የአጥቂ አማካይነት ሚና ጨዋታውን አድርጓል።

በማያውቁት ሚና የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያደረጉት ሁለቱ ተጫዋቾች በተለይ በ32ኛው ደቂቃ አብነት ከሀዋሳ ሳጥን በቅርብ ርቀት ኳስ የደረሰውን ኳስ ከሀዋሳ ተከላካዮች ጋር በግሉ ታግሎ በቀጥታ የሞከረው እና ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ የወጣችበት ኳስ እንዲሁም መክብብ በ38ኛው ደቂቃ በግንባሩ ገጭቶ የሞከራት ኳስ ተጠቃሽ የጨዋታ ቅፅበቶች ነበሩ።

በተጨማሪም ሁለቱ ተጫዋቾች በነበራቸው የ90 ደቂቃ የሜዳ ላይ ቆይታ በተለይ መክብብ ደገፉ ከኳስ ውጭ የተጋጣሚን ቅብብሎች ለማቋረጥ ያደርገው የነበረው ጥረት በጣም የሚደነቅ ነበር ። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በአጥቂነት ስለተጠቀማቸው ሁለቱ ተጫዋቾች ብቃት ተከታዩን ሀሳብ ሰጥቷል።

“የሚችሉትን አድርገዋል። ግብ ጠባቂዎቹን ገልብጠን በአጥቂነት እንዲጫወቱ አድርገናል። እንደውም በረኝነቱ ትዝ ብሏቸው ተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጃቸው እንዳይዙ እየሰጋን ነበር (እየሳቀ)። በአጠቃላይ ግን የሚችሉትን አድርገዋል። እነሱ ብቻ ሳይሆን ቡድኑም እንደ ቡድን የሚችለውን አድርጓል። በጣምም ታግለዋል። ሁለት ጎልም ማስቆጠር ትልቅ ነገር ነው። ደግሞም የተቆጠሩብን ጎሎች ያን ያክል ተለፍቶባቸው የመጡ ሳይሆኑ በእኛ የትኩረት ማነስ የመጡ ስለሆኑ ብዙም ቅር አላለኝም። ተጫዋቾቹ በጣም ታግለዋል።”



👉 ምርጡ ቸርነት ጉግሳ

በ18ኛ ሳምንት ወላይታ ድቻ ያለ ተፈጥሮአዊ አጥቂ በሀዋሳ ከተማ በተረታበት ጨዋታ የወላይታ ድቻን የማጥቃት እንቅስቃሴ በመምራት ዘንድ የቸርነት ጉግሳ ሚና በጉልህ የሚነሳ ነው።

በጨዋታው በጥቅሉ ወላይታ ድቻዎች 17 ጥቃቶችን ወደ ተጋጣሚያቸው ሀዋሳ ከተማ የግብ ክልል የሰነዘሩ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አስሩ አጋጣሚዎች ማለትም (58%) የሚሆነው የቡድኑ ጥቃት ቸርነት በተሰለፈበት የቀኝ መስመር የተሰነዘሩ ናቸው። በእነዚህ እንቅስቃሴዎች ውስጥም የተጫዋቹ ተሳትፎ ከፍ ያለ ነበር።

ጥሩ የጨዋታ ቀን ያሳለፈው ተጫዋቹ ወላይታ ድቻ በእንድሪስ ሰዒድ እና ደጉ ደበበ ባስቆጠሯቸው ግቦች ትልቅ ሚና ከመወጣት ባለፈ በመከላከል አደረጃጀት ወቅት የነበረው አበርክቶ ብሎም በሽግግሮች ወቅት በአስደናቂ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ኳሶችን የሚያቆርጥበት ብሎም በአንድ ለአንድ ግንኙነት ወቅት ተጫዋቾች ይቀንስበት የነበረው መንገድ እጅግ ድንቅ ነበር።

ወደ ዋናው ቡድን ባደገባቸው የመጀመሪያዎቹ ወራት ድንቅነቱን ማስመስከር ችሎ የነበረውና በሒደት የነበረውን ተነሳሽነት በማጣቱ ቡድኑን በሚገባ ደረጃ ማገልገል ባለመቻሉ ወቀሳዎችን ያስተናግድ የነበረው ተጫዋቹ ዘንድሮ በተለይ ከአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ሹመት በኃላ ዳግም የተነቃቃ ይመስላል።



👉በፍጥነት ተፅዕኖው እያየለ የመጣው ኦሲ ማውሊ

በውድድር አጋማሹ የዝውውር መስኮት ሰበታ ከተማን የተቀላቀለው ኦሲ ማውሊ በአዲሱ ክለቡ ባደረጋቸው የመጀመሪያ ሦስት ጨዋታዎች የቡድኑ ኮከብ ተጫዋች ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም።

በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በመስመር አጥቂነት ጨዋታዎችን የጀመረው ማውሊ በሁለቱም ጨዋታዎች የሰበታ ከተማን ከመስመር የሚነሱ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን የጥራት ደረጃ በሚታይ መልኩ ማሻሻል መቻሉ ይታወቃል። በሁለቱም ጨዋታዎች ተጫዋቹ ግብ ማስቆጠር ባይችልም ጥሩ የግብ እድሎችንም መፍጠር ችሏል።

በመጀመሪያ ጨዋታ ቡድኑ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አቻ በተለያየበት ጨዋታ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ከመስመር አጥቂነት ወደ ፊት አጥቂነት ሚና ተሸጋግሮ በቆየባቸው የጨዋታ ደቂቃዎች ይበልጥ የተሻለ ግልጋሎት መስጠት እንደሚችል ፍንጮችን አሳይቶ ነበር።

በ19ኛ ሳምንት ቡድኑ ጅማ አባጅፋርን ከመመራት ተነስቶ በረታበት ጨዋታ ላይ በፊት አጥቂነት የተሰለፈው ኦሲ ማውሊ ከአስደናቂ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጋር ቡድኑ ጨዋታውን አሸንፎ እንዲወጣ ያስቻሉ ወሳኝ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ቡድኑን ባለድል ማድረግ ችሏል።
👉የመጀመሪያ ግቡን በሊጉ ያስቆጠረው ቸርነት አውሽ

በ2009 የውድድር ዘመን ከሀዋሳ ከተማ የእድሜ እርከን ቡድኖች ወደ ዋናው ቡድን ካደጉ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ወጣቱ አጥቂ ቸርነት አውሽ በኮቪድ ክፉኛ በተመታው የሀዋሳ ከተማ ስብስብ ምክንያትነት እያገኘ በሚገኘው በመጀመሪያ ተመራጭነት ጨዋታዎችን የመጀመር እድልን በአግባቡ እየተጠቀመ ይገኛል።

ሀዋሳ ከተማ ድቻን ሲረታ የመክፈቻዋን ግብ በግሩም ሁኔታ ያስቆጠረው ተጫዋቹ በሁለተኛው አጋማሽ ሁለተኛ ግብም ለማግኘት ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታው ኳስ የግቡን ቋሚ ለትማ ተመለሰች እንጂ ሁለተኛ ግቡን ለማስቆጠርም ተቃርቦ ነበር።

ከቡድን አጋሩ ብሩክ በየነ ጋር በአካላዊ ቁመናም ሆነ በአጨዋወት መንገድ የሚመሳሰለው ቸርነት ያገኘውን እድል በአግባቡ በመጠቀም ለዓመታት አጥቶት የነበረውን የመሰለፍ እድል ለማግኘት የተቻለውን መጣር ይኖርበታል።

👉ጀማል ጣሰው – ከአምበልም በላይ

አንጋፋው ግብጠባቂ ጀማል ጣሰው ከዓመታት የተጠባባቂነት ቆይታ በኃላ በወልቂጤ ከተማ እያገኘ የሚገኘውን የቋሚ ተሰላፊነት እድልን በሚገባ እየተጠቀመ ይገኛል። ታድያ ተጫዋቹ ጎሉን ከመጠበቅ በዘለለ በሜዳ ላይ ያለው አበርክቶ ግን ከፍ ያለ ነው።

ወልቂጤ ከተማን በአምበልነት የሚመራው ግብጠባቂው ቡድኑን ከኃላ ሆነ የሚመራበት ብሎም የቡድን አጋሮቹን የሚመክርበት እና የሚያነሳሳበት መንገድ በጣም የሚደነቅ ነው። በተለይም ያለ ዋና አሰልጣኛቸው ሀዲያ ሆሳዕናን በገጠሙበት የዚህኛው ሳምንት ጨዋታ በሁለቱ የውሃ እረፍት ወቅቶች ከአሰልጣኞች ቡድን አባላት በተሻለ የቡድን አጋሮቹን ለተሻለ እንቅስቃሴ ያነሳሳበት የነበረው መንገድ ልዩ ነበር።

እርግጥ ወልቂጤ ከተማዎች ሽንፈትን ቢያስተናግዱም በጀማል ደረጃ ከፍ ያለ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች በየቡድኖቻቸው ውስጥ በምሳሌነት የሚጠቀስን ተግባር መከወን እንደሚኖርባቸው የሚያሳይ ነው።

👉ፍፁም ዓለሙ ከጎል ጋር ተመልሷል

በሊጉ የእስካሁኑ ጉዞ ከተመለከትናቸው ድንቅ ተጫዋቾች መካከል የባህር ዳር ከተማው ፍፁም ዓለሙ ይገኝበታል። አቅሙን በሚገባ እያሳየ የሚገኘው የአጥቂ አማካዩ ፍፁም ዓለሙ በጉዳት ሳቢያ በቡድኑ የድሬዳዋ ጨዋታዎች ላይ የሚፈለገውን ግልጋሎት ማበርከት አልቻለም ነበር። ከአስደናቂ የግብ ማስቆጠር አቅሙ ባልተናነሰ በተጋጣሚ ቡድኖች በመስመሮች መካከል በመገኘት አደጋዎችን የሚፈጥርበት መንገድ እንዲሁም ከተከላካይ ጀርባ የሚገኙ ጥልቀቶችን በማጥቃት ረገድ ያለው ብቃት እጅግ አስደናቂ እንደሆነ የሚታወቀው ፍፁም በ19ኛ የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር አስደናቂ ፉክክር ባደረገበት ጨዋታ በመጀመሪያ ተመራጭነት በተሰለፈበት ጨዋታ ተጫዋቹ የቀደመ ብቃቱን ሜዳ ላይ ከማስመልከቱ ባለፈ እጅግ አስደናቂ የቅጣት ምት ጎልን ማስቆጠር ችሏል።

ተጫዋቹ ካለው የጨዋታ ባህሪ አንፃር ተጋጣሚ ቡድኖች የባህርዳር ከተማን እንቅስቃሴ ለመገደብ የተጫዋቹን እንቅስቃሴ ማቆምን እንደአይነተኛ መፍትሔ በመውሰድ ፍፁም ላይ ያነጣጠሩ ተደጋጋሚ ጥፋቶችን መፈፀምን ተቀዳሚ ምርጫቸው በማድረጋቸው ተጫዋቹ በዚህ ሂደት ተደጋጋሚ ጫናዎች ውስጥ መግባቱ ብሎም ለጉዳት መዳረጉ የሚጠበቅ ቢሆንም ተጫዋቹ በእነዚህ ፈተናዎች ውስጥ ሆኖ እንኳን በጣም የተሻለ መንቀሳቀስ መቻሉ በጣም የሚደነቅ ነው።



👉ለየት ያለው የተጫዋቾች ፀጉር ቀለም

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከተመለከትናቸው ጉዳዮች መካከል የተጫዋቾች ለየት ያለ የፀጉር ቀለም ጉዳይ ነው።

ሰበታ ከተማ ከጅማ አባጅፋር ባደረጉት ጨዋታ የሰበታ ከተማው ተከላካይ መሳይ ጳውሎስ እንዲሁም የመስመር አማካዩ ቡልቻ ሹራ ከተለመደው መደበኛ የፀጉር ቀለማቸው ውጭ ቡኒ ቀለም ፀጉራቸውን ተቀብተው ተመልክተናል ። በተመሳሳይ በትናንቱ ውሎ እንዲሁ የሲዳማ ቡና የተከላካይ አማካይ ብርሀኑ አሻሞ በተመሳሳይ የፀጉር ቀለሙን ወደ ቡኒ ቀይሮ ተመልክተናል።

በተቃራኒው የባህርዳር ከተማው የመሀል ተከላካይ ሰለሞን ወዴሳ ደግሞ አልፎ አልፎ ቀለም ጣል ያደረገበትን ፀጉሩን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ሙሉ ለሙሉ ወደ ጥቁር ቀይሮ ተመልክተናል።

ከዓመታት በፊት በ2009 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛው ዙር ኢትዮጵያ ቡና ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ እንዲሁ በወቅቱ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች የነበሩት ጋቶች ፓኖም እና ኤልያስ ማሞ እንዲሁ የተለመደው የፀጉር ቀለማቸውን ለሸክላ ወደ ቀረበ ቀለም ቀይረው ወደ ሜዳ መግባታቸው ብዙ ሲያነጋግር እንደነበረ ይታወሳል።

👉 ክሪዚስቶም ንታምቢ ዳግም በፕሪምየር ሊግ

ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተመለሰው ዩጋንዳዊው አማካይ ክሪዚስቶም ንታንቢ በሰበታ ከተማ የመጀመሪያ ጨዋታውን በዚህኛው ሳምንት ማድረግ ችሏል።

ዩጋንዳዊው አማካይ ወደ ኢትዮጵያ እግርኳስ በተዋወቀበት የጅማ አባቡና ቆይታው እንዲሁም አወዛጋቢ ከነበረው የዝውውር ሒደት በኃላ በኢትዮጵያ ቡና የነበረው ቆይታ ውጤታማ ጊዜያትን ማሳለፉ ይታወሳል።

በአማካይነት ብሎም በመሀል ተከላካይነት መጫወት የሚችለው ተጫዋቹ ለአዲሶቹ ቀጣሪዎች በሁለቱም ቦታዎች ላይ አማራጭ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። ለሰበታ ከተማ ባደረገው የመጀመሪያው ጨዋታ በተከላካይ አማካይነት ጨዋታውን የጀመረው ተጫዋቹ ጥሩ የሚባልን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ማድረግ ችሏል።

በስብስቡ ውስጥ ተፈጥሯዊ የሆነ የተከላካይ አማካይ የሌለው ቡድኑ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና የተሸነፉበትን ጨዋታ ጨምሮ ለተከላካዮች ሽፋን የሚሰጥ እና በእግርኳስ ቆሻሻ የሚባለውን ሥራ የሚሰራ ተጫዋች እጅጉን ያስፈልገው የነበረው ቡድኑ በንታምቢ ይህን ያገኘ ይመስላል።

በመከላከሉ ከነበረው አበርክቶ ባልተናነሳ በተወሰነ መልኩ ከቡድኑ ተጫዋቾች ጋር ያለው መግባባት ገና አልዳበረም እንጂ ጥሩ ጥሩ ኳሶችን ወደፊት ለመጣል ሲሞክር ተመልክተነዋል።



👉 የሸገር ደርቢ የትኩረት ማዕከል የነበሩት ተጫዋቾች

በሳምንቱ ከተካሄዱት ጨዋታዎች መካከል ከፍ ያለ ግምት አግኝቶ የነበረው የሸገር ደርቢ ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በዚህ ጨዋታ ላይም ሦስት ተጫዋቾች የተለየ ትኩረት ያገኙ ነበሩ። አቤል ማሞ፣ አስቻለው ታመነ እና ታፈሰ ሰለሞን።

የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ በትናንቱ ጨዋታ ላይ በተለይ ከዕረፍት በኋላ የተደረጉ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጠንካራ ሙከራዎችን በማዳን ጥሩ ምሽት ያሳለፈ ሲሆን በጨዋታ እንቅስቃሴ የከነዓን ማርክነህን ኳስ ለማገድ ከጎል መስመሩ ውጪ በእጅ ቢነካም በእለቱ ዳኛ በአምላክ ተሰማ በቢጫ ካርድ መታለፉ የብዙዎች መነጋገርያ ሆኗል። አቤል በሁለተኛው አጋማሽ በጉዳት ምክንያት በተክለማርያም ሻንቆ ተተክቷል።

ታፈሰ ሰለሞን ሌላው መነጋገርያ የነበረ ተጫዋች ነው። የኢትዮጵያ ቡናው አማካይ በመጀመርያው አጋማሽ አስቻለው ታመነ ላይ አደገኛ ጥፋት ፈፅሞ የማስጠንቀቂያ ካርድ የተመለከተ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽም በተመሳሳይ ከባድ ጥፋት ከመፈፀሙ አልፎ ስሜታዊነት የተስተዋለባቸው ያልተገቡ ባህርያት ሲያሳይ፣ በውሳኔዎች ላይም ብስጭቱን ሲገልፅ ተስተውሎ በመጨረሻም የዳኛው ፊሽካ ከተሰማ በኋላ ኳስን በመለጋቱ ሁለተኛ ቢጫ ተመልክቷል።

አስቻለው ታመነ የትናንቱ ጨዋታ ዋና ተዋናይ ሆኖ አምሽቷል። ጥሩ የመከላከል እንቅስቃሴ ያሳየው አስቻለው በ12ኛው ደቂቃ የጋዲሳ መብራቴ የማዕወን ኳስን በግንባሩ በመግጨት ከመረብ አገናኝቶ ፈረሰኞቹን አሸናፊ አድርጓል። በአንደኛው ዙር ቡድኑ 3-2 ሲሰነፍ ደካማ ቀን ካሳለፉት ተጫዋቾች አንዱ የነበረው አስቻለው በትናንቱ ጨዋታ ያንን ያስረሳ ምሽት አሳልፏል ማለት ይቻላል። “ያኔ በሙሉ ጤናዬ ስላልተጫወትኩ የትናንትናው ጨዋታ ያንን ለመካስ የገባሁበት ነበር።” ሲልም ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን ሰጥቷል።

ፍቃዱ ዓለሙ ዐፄዎቹን ባለድል አድርጓል

የፋሲል ከነማው አጥቂ ፍቃዱ ዓለሙ በዘንድሮው የውድድር ዓመት እጅግ በጥቂት አጋጣሚዎች ብቻ ተቀይሮ በመግባት የመጫወት ዕድል ቢያገኝም ዐፄዎቹ ወሳኝ የሆኑ ስድስት ነጥቦች እንዲያገኙ ምክንያት መሆን ችሏል።

ከዚህ ቀደም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለ ጎል ሊጠናቀቅ የተቃረበው ጨዋታ ላይ ተቀይሮ በመግባት የፍፁም ቅጣት ምት እንዲገኝ ምክንያት የሆነው ፍቃዱ በትናንትናው ዕለት ቡድኑ ከሲዳማ ቡና ጠንካራ ፉክክር ገጥሞት አቻ ሊወጣ ቢቃረብም ተቀይሮ በመግባት በ87ኛው ደቂቃ ከሱራፌል ዳኛቸው የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን አሸናፊ አድርጓል።

ተጫዋቾቹ እንደ መጀመሪያ ተሰላፊ ተጫዋቾች ብዙ የጨዋታ ደቂቃዎችን ባያስመዘግብም ቡድኑ የሊጉን ክብር የሚያነሳ ከሆነ በሁለቱ ጨዋታዎች የተቀይሮ በመግባት ያደረጋቸው አበርክቶዎቹ ቀላል ዋጋ የሚሰጣቸው አይሆንም።


© ሶከር ኢትዮጵያ