በ19ኛ ሳምንት የታዘብናቸው አሰልጣኝ ነክ የትኩረት ጉዳዮች በዚህ ፅሁፍ ተዳሰዋል።
👉 የኮቪድ-19 ፈተና እና የዘላለም ሽፈራው ምላሽ
በድሬዳዋው ውድድር ሦስት ጨዋታዎችን አድርገው ሁለት ሽንፈት እና አንድ ድል ያስተናገዱት ወላይታ ድቻዎች ከጅምሩ አንስቶ በኮቪድ ክፉኛ ተቸግረዋል። በፋሲሉ ጨዋታ አዲስ ያስፈረሟቸው ተጫዋቾች ጨምሮ ከነበራቹም በአመዛኙ የመጀመሪያ ምርጫዎቻቸው የሆኑ ተጫዋቾችን በቫይረሱ ሳቢያ መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። ድሬዳዋ ከተማን ሲረቱም ጥቂት ተቀያሪዎችን ይዘው ዳግም በርካታ ተጫዋቾችን ሲያጡ በዚህ ሳምንት ደግሞ ከነጭራሹኑ ያለተጠባባቂ ግብ ጠባቂዎችን ጭምር በሜዳ ላይ ተጠቅመው ለመጫወት ተገደዋል።
ይህ ሁሉ ሲሆን የቡድኑ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በሁኔታው በመገረም ውስጥ ሆነው ነገሩን ከማስረዳት አንዳንዴም ፈገግ የሚያስብሉ አስተያየቶችን ከመስጠት ያለፈ ምሬት አልተስተዋለባቸውም። በሀገራችን ሊግ እንኳንስ ይህን ያህል ተፅዕኖ የደረሰበት ቡድን ሆኖ ይቅር እና ሽንፈት ሲመጣ በሜዳ ላይ በተቃራኒ ቡድን እንቅስቃሴ አንዴንዴም በዳኞች ማመካኘት የተለመደ ነው። በዚህ ረገድ የአሰልጣኙ ለዘብ ያለ የሚዲያ ፊት አቀራረብ ለሌሎችም ትምህርት የሚሆን ነው። እርግጥ ነው ቡድኑ ቀደም ብሎ ጥሩ ውጤት መያዙ አሰልጣኙን ከጫና ነፃ እንዳደረጋቸው ዕሙን ቢሆንም በቶሎ ድንጋጤ እና ብስጭት ውስጥ ገብተው ስሜቱን ወደ ቀሪ ተጫዋቾቻቸው አለማዛመታቸው የሚደገፍ ነው። ለዛም ይመስላል ቡድኑ ባልተሟላበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንኳን ሜዳ የገቡ ተጫዋቾች የአልሞት ባይ ተጋዳይነት ባህሪ የሚታይባቸው።
👉መንበራቸው እየተናጠ የሚገኘው ደግአረግ ይግዛው
በተሰረዘው የውድድር ዘመን በፕሪምየር ሊጉ ተስፋ ሰጪ ቡድንን በማሳየታቸው ብዙዎች ዘንድሮ የተሻለ ውጤታማ ቡድንን ይገነባሉ በሚል በብዙዎች ተስፋ የተጣለባቸው አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው በወልቂጤ ከተማ ደረጃ ቡድናቸው ጥሩ የውድድር ዘመን ጅማሬን ቢያደርግም ሰሞነኛ ውጤታቸው ግን የተገላቢጦሽ ሆኖባቸዋል። በዚህም ከየአቅጣጫው ጥያቄዎች እየተነሱባቸው ይገኛል።
ቡድኑ በመጨረሻ ካደረጋቸው አስር ጨዋታዎች በስድስቱ ሲሸነፉ፤ በሁለቱ አቻ እንዲሁም በሁለቱ ደግሞ ማሸነፍ ቢችሉም በመጨረሻ ያደረጓቸውን ሦስት ጨዋታዎችን በመሉ መሸነፋቸው አሰልጣኙ ላይ ዳግም ጫናዎች እንዲበረክቱ እያደረገ ይገኛል። አሰልጣኙ ከጥቂት ሳምንታት በፊት እንዲሁ ቡድኑ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ አዎንታዊ ውጤት በማስመዝገብ ተንፈስ አሉ እንጂ ተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ተሸንፈው መሰል ጫና ውስጥ ገብተው እንደነበር ይታወሳል።
እርግጥ የቡድኑ ውጤት አጠቃላይ የቡድኑን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የማይገልፅ ቢሆንም ቡድኑ በየትኛውም አይነት ሁኔታ ውስጥ እንኳን ቢሆን በአዎንታዊ የጨዋታ አቀራረብ አጥቅቶ ውጤት ለማግኘት የሚፈልግ ጀብደኛ ቡድን ቢሆንም በአንዳንድ አጋጣሚዎች ይህ ታክቲካዊ ገራገርነት ቡድኑን በተወሰነ መልኩ በውጤት የማጣት ጫና ውስጥ ሲከተው ይስተዋላል።
የአጭር ጊዜ እሳቤ በተጠናወተው እግርኳሱ የቡድኑ አመራሮች በመሰል ውጤት አልባ ጉዞ ውስጥ እንኳን ሆነው በአሰልጣኙ ተስፋ ሰጪ የቡድን ግንባታ ሒደት እምነት አሳድረው ምን ያህል ይታገሷቸው ይሆን የሚለው ነገር በጉጉት የሚጠበቅ ነው።
👉ያለ ዋና አሰልጣኞቻቸው ጨዋታ ያደረጉት ቡድኖች
በ19ኛ የጨዋታ ሳምንት የኮቪድ 19 ተፅዕኖ ከእስካሁኖቹ የጨዋታ ሳምንታት እጅጉን የበረታበት ነበር ማለት ይቻላል። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ሁለት አሰልጣኞች በቫይረሱ በመያዛቸው ቡድናቸውን በሜዳ ተገኝተው መምራት ሳይችሉ ቀርተዋል።
ወልቂጤ ከተማዎች ሀዲያ ሆሳዕናን ሲገጥሙ ዋና አሰልጣኛቸው ደግአረግ ይግዛው መገኘት ባለመቻላቸው በምትካቸው ምክትሉ አብዱልሀኒ ተሰማ የመተመሩ ሲሆን በተመሳሳይ ባህር ዳር ከተማ ከድሬዳዋ ባደረጉት ጨዋታ ፋሲል ተካልኝ ቡድኑን መምራት ባለመቻሉ በምትኩ ቡድኑን የመምራት ኃላፊነቱን ምክትላቸው ታደሰ ጥላሁን ተረክበው አከናውነዋል።
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት እንዲሁ ፋሲል ከነማዎች እንዲሁ የአሰልጣኝ ቡድኑ አባላት በቫይረሱ በመያዛቸው መነሻነት የቡድኑን መሪው ሀብታሙ ዘዋለ ቡድኑን መምራቱ ይታወሳል።
👉በውድድር አጋማሽ የሚዘዋወሩ ተጫዋቾች
በሀገራችን እግርኳስ የዝውውር መስኮቶች በተከፈቱ ቁጥር ቡድኖች ተጫዋች ለማዘዋወር የፋይናንስ አቅርቦት እስከተገኘ ድረስ ቡድኖች በተለይም ደካማ የውድድር ዘመንን ያሳለፉ ቡድኖች በአዳዲስ አሰልጣኞቻቸው እየተመሩ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ተጫዋቾን ማዘዋወራቸው የተለመደ ነው።
በዘንድሮው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር አጋማሹ የዝውውር መስኮት አዳማ ከተማ ሙሉ ቡድኑን በሚያስብል መልኩ በርካታ ተጫዋቾን ሲያዘዋውር በተመሳሳይ ሲዳማ ቡና እና ጅማ አባጅፋር በርከት ያሉ ተጫዋቾን ያዘዋወሩ ቡድኖች ናቸው።
እርግጥ እነዚሁ ቡድኖች በመጀመሪያው የውድድር አጋማሽ እጅግ አስቸጋሪ ጊዜያትን ማሳለፋቸው የማይካድ ቢሆንም በዚህ ደረጃ አዳዲስ ተጫዋቾችን ማዘዋወራቸው የቡድኖቹን አፋጣኝ ጥያቄ ሰለመመለሱ ግን በዓመቱ መጨረሻ ምላሽ የሚያገኝ ጉዳይ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የሚመሩት ሰበታ ከተማዎች በመጀመሪያ ዙር በግልፅ ይታዩ የነበሩ ክፍተቶችን ለመድፈን የሚረዱ ሁለት ተጫዋቾን ማዘዋወር ችሏል። በግራ መስመር እንዲሁም በፊት አጥቂነት መጫወት የሚችለውን ኦሲ ማውሊ እና በተከላካይ አማካይነት ሆነ በተከላካይነት አማራጭ መፍጠር የሚችለውን ክሪዚስቶም ንታንቢን ያስፈረመው ቡድኑ በሜዳ ላይ እነዚህን ተጫዋቾችን ለምን እንዳስፈረማቸው በግልፅ የየሚያሳዩ እንቅስቃሴዎችን እየተመለከትን እንገኛለን።
ቡድኑ በሁለቱ ተጫዋቾች ዝውውር ምን ያህል እንደተሻሻለ በድሬዳዋ የቡድኑ ጨዋታዎች ምስክር ናቸው። በተመሳሳይ ሲዳማ ቡና በቁጥር በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ቢያስፈርምም የፈረሙት ተጫዋቾች በተመሳሳይ በውጤት አልባ ጉዞ ላይ የነበረውን ቡድን በተሻለ ደረጃ እያነቃቁ ይገኛል።
👉 ዓበይት አስተያየቶች
* ፀጋዬ ኪዳነማርያም በሁለቱ አጋማሾች ወጥ አቋም ስላለማሳየታቸው
“እንደሚታወቀው በተወሰኑ ተጫዋቾች ነው ተከታታይ ጨዋታ እያደረግን የምንገኘው። ስብስባችን በቁጥር ካልሆነ በቀር በጥራት ላይ የተሟላ ነው ማለት አንችልም። ስለዚህ ያ የፈጠረው ጫና ነው። ቀይረን የምናስገባቸው ቋሚዎቹን የሚተኩ ስላልሆኑ ውጤቱን ሊያበላሽብን ችሏል። ዞሮ ዞሮ የመዳከም ብቻ ሳይሆን ልጆቹ ውጤትን ለማስጠበቅ ወደ መከላከል አደረጃጀት የሚገቡበት መንገድ እንደ ድክመት የሚታይ ነው። በቀሪ ጨዋታዎች ተስፋ አንቆርጥም። ተሻሽለን ለመቅረብ ጥረት እናደርጋለን።”
* ዘላለም ሽፈራው ከጨዋታ በፊት አስቦት ስለነበረው ነገር?
“አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ አይነት ነገሮች ሲያጋጥሙ ልበ ሙሉ መሆን ያስፈልጋል። ምንም አይነት ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ግን እነዛን ችግሮች ተቃቁሞ ማለፍ ያስፈልጋል። ትልቁ አቅም የሚባለውም ይሄ ነው። ትልቁ ብቃት የሚባለው በተሳኩ ሁኔታዎች ማለፍ ሳይሆን በፈተናዎች ተረማምዶ ማሸነፍ ነው። ከተጫዋቾቼም ጋር ስናወራ የነበረው ይሄንን ነወ። ከዚህ መነሻነት ተጨዋቾቼ በደንብ ተጋድለው እንደሚጫወቱ ግምት ነበረኝ። እንደውም እንቅስቃሴው ከገመትኩት በላይ ነው። ሁለት ጎል እናገባለን ብዬ ባላስብም ከጨዋታው ቢያንስ ነጥን ይዘን እንወጣለን የሚል እምነት ነበረኝ።”
*ካሣዬ አራጌ እስከ 30ኛው ደቂቃ ስለመቸገራቸው
“ከሀዋሳ እና ከድቻ ጋር የተጫውትናቸው ጨዋታዎች እንደዚሁ ተመሳሳይ ነበሩ። አንዳንዴ ቡድኖች የሚቀርቡበት መንገድ ተጫዋቾችን በራሳቸው ሜዳ አብዝተው ስለሆነ የግድ ቦታዎችን ለማግኘት መታገስ ያስፈልጋል። አንዳንድ ጊዜ ልክ እንደ አንተ ከፍቶ የሚጫወት ተጋጣሚ ስተገኝ የሚገኙ ክፍተቶችን ለመጠቀም ትሞክራለህ። ግን በዚህ በኩል ክፍት ሜዳዎችን ዘግቶ የሚመጣ ቡድን ሲኖር ትክክለኛ የመሞከርያውን ቦታ እስክታገኝ ጊዜ ሊወስድ ይችላል።”
*ሥዩም ከበደ ውጤቱ ለቀጣዩ ጉዟቸው ስላለው አስተዋፅዖ
“ያሁኑ ብቻ ሳይሆን ከባህር ዳር ጋር ነጥብ መጋራታችንም ትልቅ ውጤት ነው። ይሄ ነጥብ ግን ለእኛ በጣም ጥሩ ነው። ምክንያቱም ተከታዮቻችን እርስ በእርስ የሚያደርጉት ከፍተኛ ፉክክር ስላለ በዛ መካከል ሾለክ ለማለት ዕድሉ አለን። ቀሪ ሁለት ጨዋታዎቻችንን በዚህ ትጋት መጨረስ አለብን። ከዛ በኋላ የሀዋሳውን ጨዋታ ማሟያ እናረገዋለን። ወጣቶቻችንን ለማየት የምንችልበት እናደርገዋለን። ከሁሉም በላይ እዚህ ድረስ ታግሶን ከፍተኛ ደጋፍ ያደረገልን የፋሲል ከነማን ደጋፊ በዚህ አጋጣሚ እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለሁ።”
* ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ስለ ቡድኑ ተነሳሽነት እና የቡድናቸው ችግር
“ያለንበት ቦታ ያቃጥላል፤ አያስተኛም። ለማሸነፍ መሥራት ያስፈልጋል። በተገኘው አጋጣሚ ሦስት ነጥብ በማግኘት በሊጉ መቆየት ያስፈልጋል። ለዛ ነው ጫን እያደረግን የምንጫወተው።
ቡድናችን ጥራት ይፈልጋል። ጁንያስ ቢኖር ጥሩ ነበር። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ቡድኑ የተሻለ ነው። ሁሌ እንደምለው የተጫዋቾቹ ብቃት እና ያለንበት ደረጃ አንድ አይደለም። ስለዚህ ማሸነፍ እንፈልጋለን፤ በቀጣዩ የሲዳማ ጨዋታም ውጤት ለማምጣት ጥረት እናደርጋለን።”
© ሶከር ኢትዮጵያ