ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

በ19ኛ ሳምንት የተመለከተናቸው ሌሎች ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች የመጨረሻው ፅሁፋችን አካል ናቸው።

👉 ጨዋታዎችን ማዘዋወር ስለምን አልተቻለም?

የዘንድሮው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከቀደሙት ውድድሮች ዘንድ እጅግ በተሻሻለ መልኩ እየተመራ ይገኛል። በዚህም በቀደሙ ዘመናት ይነሱ የነበሩ ድክመቶች አሁን ላይ ሙሉ ለሙሉ ተቀርፈዋል ለማለት በሚያስደፍር መልኩ የተሻለ የውድድር ሒደት ላይ እንገኛለን።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በ19ኛው ሳምንት በተለይ ወላይታ ድቻ እና ሀዋሳ ከተማ የቡድን አባላት የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ውጤታቸው በርካታ ተጫዋቾች እንደተያዙባቸው ቢገለፅም አወዳዳሪው አካል ግን የቴሌቪዥን ስርጭቱን ብቻ ከግምት ውስጥ ያስገባ በሚመስል መልኩ ቡድኖቹ ያለ በቂ የጨዋታ ዕለት ስብስብ ጨዋታቸውን እንዲያካሄዱ የተገደዱበት መንገድ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው።

በዚህ ፈታኝ ወቅት አወዳዳሪው አካል ጨዋታዎችን ለሌላ ጊዜ ማሸጋገር የሚቻልበት አማራጭን ከመመልከት ይልቅ ተጫዋቾቹን ሆነ ቡድኖቹን አላስፈላጊ ጫና ውስጥ የከተተ ውሳኔ እየወሰነ እንደሆነ በቅሬታ መልክ እየተነሳ ይገኛል። በተቃራኒው ደግሞ “ክለቦች ተጫዋቾቻቸውን እና የቡድን አባላቶቻቸውን ከኮቪድ ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራትን መከወን ሲገባቸው በራሳቸው ጥንቃቄ ጉድለት በሚመጣ ችግር ጨዋታዎች ሊራዘሙ አይገባም።” የሚሉም አልታጡም።

👉 የኮቨድ ተፅዕኖ መበርታት

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት እየተደረጉ የሚገኙ የሊጉ ውድድሮች ኮቪድ ክፉኛ እየፈተናቸው ይገኛል። በተለይ የ19ኛ ሳምንት ጨዋታ መርሃግብሮች በበርካታ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ የተደረጉ ነበሩ።

የወላይታ ድቻ እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በርካታ ቁጥር ያላቸው ተጫዋቾች በመያዛቸው ያለ ተጠባባቂ ተጫዋች ሁለት ግብ ጠባቂዎች በወላይታ ድቻ በኩል እንደ ሜዳ ላይ ተጫዋቾች ለመጠቅም ያስገደደ ነበር።

በተጨማሪም በርካታ ቁጥር ያላቸው የጨዋታ ዳኞች በቫይረሱ በመያዛቸው መነሻነት ጥቂት ዳኞች በመሐል ብሎም በሌሎች ጨዋታዎች በረዳት እና አራተኛ ዳኝነት ጨዋታዎችን እንዲመሩ ያስገደደ ነበር። በዚህም ምክንያት ከመጨረሻው የኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ በቀር በሌሎቹ ጨዋታዎች ላይ በዋና ዳኝነት የምናውቃቸው ዮናስ ካሣሁን፣ ኃይለየሱስ ባዘዘው፣ አዳነ ወርቁ እና ማኑሄ ወልደፃድቅ በረዳት ዳኝነት ለማጫወት ተገደዋል። ሁለት ረዳት ዳኞች ደግሞ (በአንደኛው ጨዋታ ሶርሳ ዱጉማ እና በሌላኛው ጨዋታ ለዓለም ዋሲሁን) ደግሞ እየተቀያየሩ ጨዋታ ሲመሩ ተስተውለዋል።

በተመሳሳይ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የወልቂጤ ከተማ እና ባህርዳር ከተማ አሰልጣኞች በቫይረሱ በመያዛቸው ቡድናቸውን ሜዳ ተገኝተው መምራት ሳይችሉ ቀርተዋል። በዚህም ምክንያት ምክትሎቻቸው አብዱልሀኒ ተሰማ እና ታደሰ ወርቁ ቡድኖቻቸውን መርተዋል።

ታድያ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እየተካሄደ በሚገኘው ውድድሩ ተጫዋቾች ሆነ ሌሎች በውድድሩ የሚሳተፉ አካላት ከፍ ባለ የሙያተኝነት ስሜት ራሳቸውን ብሎም ሌሎችን ከዚህ አስከፊ በሽታ ለመጠበቅ ጥረት የማያደርጉ ከሆነ የውድድሩ ህልውና አደጋ ውስጥ መግባቱ አይቀርም።

👉 ከአዲስ አበባ ውጭ የተደረገው የመጀመሪያው የሸገር ደርቢ

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከፍ ያለ ቦታ ከሚሰጣቸው መካከል ቀዳሚው የሆነው የሸገር ደርቢ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ ውጭ ተደርጓል።

በ19ኛ የጨዋታ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ቡናን በአስተቻለው ታመነ ብቸኛ ግብ የረታበት የትናንት ምሽቱ ጨዋታ ከአዲስ አበባ ውጭ የተደረገ የመጀመሪያው የሸገር ደርቢ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ ይህን ውድድር በማስተናገድ ባለታሪክ መሆንም ችላለች።

👉 የዮናታን ፍሰሐ መለያ

በውድድር አጋማሹ ሲዳማ ቡናን ለቆ ወልቂጤ ከተማን የተቀላቀለው የመስመር ተከላካዩ ዮናታን ፍስሐ በሳምንቱ መጨረሻ በወልቂጤ ከተማ የመጀመሪያውን ጨዋታውን አድርጓል።

ታድያ ተጫዋቹ በዚህ ጨዋታ ወቅት ለብሶ ወደ ሜዳ የገባው መለያ ግን ትኩረትን የሚስብ ነበር ፤ ቀድሞ በሌላ ተጫዋች ስም እና ቁጥር ተዘጋጅቶ የነበረውን መለያ ተጫዋቹ በእለቱ ለብሶት የገባውን 23 ቁጥር እንዲሆን ለማድረግ በርካታ ልጥፎች እንዲሁም በሰማያዊ ቀለም ለመፃፍ የተደረገው ጥረት ለተመለከተው አዝናኝ ነበር።

ይባሱኑ ልጥፎቹ ለቀው ተጫዋቹ በሚሮጥበት ወቅት ተገነጣጥለው በንፋስ ሲንቀሳቀሱ የታየ ሲሆን መሰል ሁነቶች በወልቂጤ ከተማ ብቻ ሳይሆን በሌሎች በተለይ በአጋማሹ ተጫዋቾች ለቀው አዳዲስ ተጫዋቾች ባስፈረሙ ቡድኖች በብዛት እየተመለከትነው የምንገኝ ሊሻሻል የሚገባ ጉዳይ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ