ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ19ኛ ሳምንት ምርጥ 11

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በየቦታቸው የተሻሉ ሆነው የተገኙ ተጫዋቾችን በሳምንቱ ምርጥ 11 ውስጥ አካተናል።

አሰላለፍ : 4-3-3

ግብ ጠባቂ

መሐመድ ሙንታሪ – ሀዲያ ሆሳዕና

በዚህ ሳምንት ባልተለመደ ሁኔታ ግብ ጠባቂ መምረጥ ከባድ ሆኖብን ነበር። ፅዮን መርዕድ ፣ ጀማል ጣሰው ፣ ፍሬው ጌታሁን ፣ ሚኬል ሳማኬ እና ኤቤል ማሞ ጥሩ በቃት ያሳዩ ተጫዋቾች ነበሩ። ያሳዩትን ተቀራራቢ አቋም ከግምት አስገብተን ባደረግነው ምልከታ አራት ኢላማቸውን የጠበቁ ኳሶችን ያዳነው እና ግብ ያልተቆጠረበት መሐመድ ሙንታሪን የሳምንቱ ምርጥ አድርገዋል።

ተከላካዮች

ሄኖክ አዱኛ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቡና በብልጫ በጨረሰባቸው ጨዋታዎች ሁሉ ዋነኛ ጠንካራ ጎኑ የነበረውን የግራውን የቡድኑን ክፍል የመከላከል ኃላፊነት የነበረበት የጊዮርጊሱ ሄኖክ ጨዋታውን በአግባቡ ከውኗል። ከመከላከሉ ባለፈ በድፍረት ወደ ፊት የሄደባቸው አጋጣታሚዎች ሲኖሩ አማኑኤል ገብረሚካኤልን ከግብ ጠባቂ ጋር ያገናኘበት በሦስት ተከላካዮች መሐል የሰነጠቀው የግብ ዕድልም ተጠቃሽ ነው።

አስቻለው ታመነ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጠባቂውን ጨዋታ ያሸነፈባትን ብቸኛ ግብ ያስቆጠረው አስቻለው ታመነ በዋነኛው ኃላፊነቱም ጥሩ ቀን አሳልፏል። ለስህተት በሚያጋልጠው የሜዳው ሁኔታ ውስጥ የቡድኑን የኋላ ክፍል በአግባቡ በመምራት ክፍተት ሲፈጠር ግቦችን ማምረት የማይቸግረው የተጋጣሚውን የፊት መስመር እንደቡድን ለማቋም ላቅ ያለ ድርሻ መወጣት ችሏል።

መናፍ ዐወል – ባህር ዳር ከተማ

በሳምንቱ ከተደረጉ እጅግ ፈታኝ ጨዋታዎች መካከል የባህር ዳር እና የድሬዳዋ ጨዋታ አንዱ ነበር። በጨዋታው መናፍ ዐወል የድሬዳዋ የማጥቃት አጋጣሚዎች ወደ ግብ ተቀየሩ ሲባል በአንድ ለአንድ አጋጣሚዎች ይወስናቸው የነበሩ ውሳኔዎች ጨዋታው ለባህር ዳሮች ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን ወሳኝ ሚና ነበራቸው።

ሄኖክ ኢሳይያስ – ድሬዳዋ ከተማ

ቡድኑ ባህር ዳርን በገጠመበት ጨዋታ ሙሉ ነጥብ አያግኝ እንጂ ቀዳሚ የሆነበትን ግብ የግራ መስመር ተከላካዩ ከቅጣት ምት ማስቆጠር ችሏል። ከአሰልጣ ኝ ዘማርያም መምጣት በኋላ ቦታውን መልሶ ያገኘው ሄኖክ በትጋት መስመሩን ለመሸፈን ሲንቀሳቀስ መዋሉ የቦታው ተመራጭ አድርጎታል።

አማካዮች

ክሪዚስቶም ንታንቢ – ሰበታ ከተማ

ለኢትዮጵያ እግርኳስ አዲስ ያልሆነው ዩጋንዳዊው አማካይ ዳግም ከተመለሰ በኋላ የመጀመሪያ የመስለፍ ዕድል ባገኘበት ጨዋታ የቀድሞው መልካም አቋሙ ላይ እንደሚገኝ አሳይቷል። የቡድኑን እንቅስቃሴ ሚዛን በመጠበቅ ጥሩ የኳስ ስርጭት እንዲኖር ሲያደግ ቆይቶ ለኦሴይ ማዎሊ ሁለተኛ ግብም ጥሩ ኳስ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

ፍፁም ዓለሙ – ባህር ዳር ከተማ

ከሊጉ ደንቅ አማካዮች ውስጥ አንዱ የሆነው ፍፁም ጠፈት ብሎ በተመለሰበት ጨዋታ የተለመደው ብቃቱ ላይ ተገኝቷል። ከባድ ፍትጊያ በነበረት ጨዋታ እንደወትሮው በድፍረት በየፍልሚያው ላይ የማይታጣ የነበረው ፍፁም በቡድኑ ማጥቃት ውስጥ ዋና ተዋናይ መሆን ሲችል ባህር ዳርን አቻ ያደረገችውን ወሳኝ ግብ ከቅጣት ምት በቀጥታ በመምታት ማስቆጠር ችሏል።

ጋዲሳ መብራቴ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

በጭቃማው እና ጉልበት ይጠይቅ በነበረው የሸገር ደርቢ ጊዮርጊሶች በተሻለ ጉልበት ጨዋታውን እንዲያስኬዱ ከረዱ ተጫዋቾች አንዱ ጋዲሳ ነበር። ብቸኛዋ የአስቻለው ታመነ የማሸነፊያ ጎል ስትቆጠር ኳስን ከማዕዘን ያሻገረው ጋዲሳ አይደክሜ ሆኖ ያመሸበት ብቃቱ ተመራጭ አድርጎታል። በጨዋታው ሚናው የመስመር ተጫዋችነት ቢሆንም ከሁለገብነቱ አንፃር በአማካይ ስፍራ አካተነዋል።

አጥቂዎች

ዑመድ ኡኩሪ – ሀዲያ ሆሳዕና

የጠንካራ ግራ እግር ባለቤቱ ወደ ሀገሩ ሊግ ተመልሶ ሀዲያ ሆሳዕናን በመቀላቀል ፊት መስመር ላይ ተፅዕኖውን ማሳየት ጀምሯል። በወልቂጤው ጨዋታ ከቀደሙት ሁለት የጨዋታ ቀናት ይበልጥ የተሻሻለው ዑመድ ከባባድ ሙከራዎችን ሲያደርግ ቆይቶ ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገው ወሳኙ የዳዋ ሆቴሳ ግብ ምክንያት የሆነ የተመጠን ግሩም ኳስ ማድረስ ችሏል።

ቸርነት ጉግሳ – ወላይታ ድቻ

ዓመቱ ሲጀመር ጥሩ ሆኖ የታየው እና ቀስ በቀስ የደበዘዘው ቸርነት ድሬዳዋ ላይ ዳግም ፈክቷል። በዚህ ሳምንት ቡድኑ ያለበቂ ተጫዋቾች ሀዋሳን ሲፈተን የቸርነት እንቅስቃሴ አስገራሚ ነበር። የድቻ ሁለት ግቦች ሲቆጠሩ ዋናውን ሥራ የሰራው አጥቂው ሁለት ከባባድ ሙከራዎችንም በማድረግ ለተከታታይ ሁለተኛ ሳምንት ምርጫችን ውስጥ ተካቷል።

ኦሰይ ማዎሊ – ሰበታ ከተማ

ጋናዊው አጥቂ በዚህ የውድድር አጋማሽ ወደ ሊጉ ተመልሶ ከመጣ በኋላ በሰበታ መለያ ሦስት ጨዋታዎችን አድርጓል። ከጅምሩ ለቡድኑ የማጥቃት ሂደት ተስፋ እንደሆነ ሲያሳይ ቆይቶም በዚህ ሳምንት ሰበታ ከተማ ጅማ አባ ጅፋርን 2-1 እንዲያሸንፍ የረዱትን ሁለት ጎሎች ማስቆጠር ችሏል።

አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ

የሊጉ መሪዎች በሲዳማ ቡና እጅግ በተፈተኑበት ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብ እንዲያሳኩ የአሰልጣኝ ሥዩም ጥሩ ውሳኔዎች አስፈላጊ ነበሩ። በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ የበረታውን የሲዳማን የበላይነት ከመግታት አልፎ ቡድናቸው ዳግም የበላይነቱን ወስዶ ተጨማሪ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታውን እንዲያሸንፍ የረዱ ሁለት ስኬታማ ቅያሪዎች በማድረጋቸውም የሳምንቱ ምርጥ አሰልጣኝ አድርገናቸዋል።

ተጠባባቂዎች

ፅዮን መርዕድ – ባህር ዳር ከተማ
ደጉ ደበበ – ወላይታ ድቻ
ከድር ኩሊባሊ – ፋሲል ከነማ
ዮናስ ገረመው – ሲዳማ ቡና
ሀይደር ሸረፋ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ቸርነት አወሽ – ሀዋሳ ከተማ
ዳዋ ሆቴሳ – ሀዲያ ሆስዕና


© ሶከር ኢትዮጵያ