የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-1 ጅማ አባ ጅፋር

የከሰዓቱ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞች ከሱፐር ስፖርት ጋር ቀጣዩን ቆይታ አድረገዋል።

አሰልጣኝ ፍራንክ ናታል – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለ ጨዋታው

ሁሌም ጨዋታውን ለማሸነፍ ነው የምንገባው ፤ የዓለም ፍፃሜ አይደለም። ከባድ ጨዋታ እንደሚሆን አውቀን ነበር ፤ ተጋጣሚያችን በሊጉ ለመቆየት እየታገለ ነው። የጠበቅነው ነበር ፤ ያው አንዴንዴ ነገሮች በዚህ መልኩ ሊሄዱ ይችላሉ።

በጊዜ ስለተቆጠረባቸው ግብ

እውነት ለመናገር ከጅማ ጥሩ አጀማመር ነበር።

የቆመ ኳስን መጠቀም ዋና ዕቅዳቸው ስለመሆኑ

ባለፈው ጨዋታ ብዙ ዕድሎችን ከክፍት ጨዋታ ፈጥረናል። 16 ከሚሆኑ ኳሶች አንድ ቢሆር ነው ከቆመ ኳስ የተነሳው። ስለዚህ ከቆመ ኳስ ብቻ ሳይሆን በጨዋታም ዕድል እንፈጥራለን። ዛሬም ያን ለማድረግ ሞክረናል ሆኖም አልተሳካም።

ፉክክሩ ውስጥ ስለመሆናቸው

አሁንም ፉክክር ውስጥ ነን። ሌሎቹም ቡድኖች ውጤት ሲያገኙ እና ሲጥሉ እየተመለከትን ነው። አሁንም በቀጣይ ጨዋታዎች ቀሪ ረጅም ጉዞ አለ። ሌሎች ቡድኖች ፉክክር ውስጥ እንዳሉ ሁሉ እኛም አለን።

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ጅማ አባ ጅፋር

ውጤቱ ፍትሃዊ ስለመሆኑ እና ስለ ቡድኑ እንቅስቃሴ?

የጊዮርጊስ ትልቅነት እንደተጠበቀ ነው። በየቦታው ውጤት ቀያሪ እና ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚያውቁ ተጫዋቾች አሏቸው። ግን በእግር ኳስ በ90 ደቂቃ በሚፈጠሩ ነገሮች የሚወሰን ነው። እኛም ይህንን አስበን ነበር ወደ ሜዳ የገባነው። ዞሮ ዞሮ ግን እኔ የሚያሳስበኝ ቡድኑ እየተሻሻለ ነው ወይ የሚለው ነው። ዛሬ አቻ መውጣታችን ጥሩ ሊሆን ይችላል። ግን ከዚህ በፊት በጣም የሚያስቆጩ ነጥቦችን ጥለናል። የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያችን ያን ያህል ጥሩ ባይሆንም ውጤት አስጠብቀን ባለመውጣታችን እና ልምድ ያለው አጨዋወት በማጣታችን ብዙ ነጥብ ጥለናል። እነዛ ነጥቦች ደግሞ ያስቆጫሉ። ቢሆንም ግን አሁንም ቀሪ ጨዋታዎች አሉን። ከምንም በላይ ግን ውጤቱ ሳይሆን እኔ በቡድኑ ላይ መሻሻሎችን እያየሁ ነው። ትልቁ ነገር እና በስልጠና የማይሻሻለው የፍላጎት ነገር ተጫዋቾቹ አላቸው። በዚህ ደግሞ ተጫዋቾቹን ማመስገን እፈልጋለሁ። ሜዳ ላይ ባላቸው ታታሪነትም ሁሌ እንደኮራሁ ነው። በአጠቃላይ ግን ውጤቱ ፍትሀዊ ነው።

ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በሰከንዶች ውስጥ ግብ ስለማስቆጠራቸው እና መልበሻ ክፍል ስላወሩት ነገር ?

ባለፈውም ከሀዋሳ ከተማ ጋር ስንጫወት በተመሳሳይ ደቂቃ ጎል አስቆጥረናል። ብዙ ጊዜ በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ክለቦች እንጠንቀቅ ነው የሚሉት። እኛ ግን የራሳችን ስትራቴጂ አለን። ብዙ ጊዜም ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ተጋጣሚዎች ትኩረት የሚያጡበት የተለመደ ነገር አለ። ይህንንም ነገር ብዙ ጊዜ ለመጠቀም እንፈልጋለን። ዞሮ ዞሮ ግን ብዙ መሻሻል ያሉብን ነገሮች አሉ። ድክመቶቻችንንም ማስተካከል አለብን። በተለይ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያችን ቅርፁን የጠበቀ እንዲሆን ማድረግ አለብን። በአጠቃላይ ግን በመሻሻል እና በጥረት ላይ ነው የምናተኩረው።


© ሶከር ኢትዮጵያ