ቅድመ ዳሰሳ | ሰበታ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

በ20ኛው ሳምንት ቀዳሚ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

አሁን ላይ የከፋ ስጋት የሌለባቸው ሁለቱ ቡድኖች በሰንጠረዡ አጋማሽ አካባቢ ላይ ሆነው ይበልጥ ራሳቸውን የሚያደላድሉባቸውን ነጥቦች ፍለጋ ይገናኛሉ። ድሬዳዋ ላይ የመጀመሪያ ሦስት ነጥባቸውን ጅማ አባ ጅፋርን በመርታት ያሳኩት ሰበታዎች አሸነፊነታቸውን ካስቀጠሉ የነገ ተጋጣሚያቸውንም በነጥብ በልጠው ከፍ ማለት ይችላሉ። የኮቪድ በትር አብዝቶ ያረፈበት ወላይታ ድቻም ወደ ባለ ሰላሳ ቤት ነጥብ ስብስብ ክለቦች ለመቀላቀል የሚቀርብበትን ውጤት ከጨዋታው ይፈልጋል።

በጨዋታው የተሻሉ የኳስ ቁጥጥር ለመያዝ እንደማይቸገሩ የሚገመቱት ሰበታ ከተማዎች ምን አልባት ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በቀላሉ መድረስ ላይ ሊቸገሩ ይችላሉ። የተጋጣሚያቸው የኳስ ውጪ ትጋት ቅብብሎች በቀላሉ ሰርገው እንዳይገቡ የማይደርግ መሆኑ ለዚህ እንደምክንያትነት የነሳል። ከዚህ በተጨማሪም ሰበታዎች የሚቋረጡባቸውን ኳሶች በቶሎ መልሶ የመንጠቅ ብቃታቸውም በጨዋታው ልክ መሆን ይጠበቅበታል።

በዚህ ረገድ ራሳቸውን ከመልሶ ማጥቃት ሂደቶች መከላከልም ሌላኛው የቤት ሥራቸው ነው። እንደ ክሪዚስቶም ንታንቢ ዓይነት ተጫዋች በጥሩ አቋም ላይ ሆኖ ማግኘታቸውም ለመሰል ነጥቦች ትልቅ እገዛ ያደርግላቸዋል። ሰበታዎች ከጊዮርጊሱ ጨዋታ በቀር ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ግብ እየቀናቸው መሆኑ ይበልጥ በመከላከሉ በኩል ትኩረታ እንዲጨምሩ የሚያደርጋቸው ሲሆን ጅማን ከኋላ ተነስተው ማሸነፍ መቻላቸው ደግሞ በሚከተሉት አጨዋወት በትዕግስት ጠብቀው ግብ በማግኘቱ ረገድ ነገ አዕምሯዊ ጥንካሬ እንዲኖራቸው የሚያግዝ ነው።

የወላይታ ድቻን የነገ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ለመገመት ያለፉትን ጨዋታዎች ውጤት እንደወረደ መውሰድ ስህተት ይሆናል። ከሦስት ጨዋታዎች ሁለቱን የተሸነፉት ድቻዎች በኮቪድ ምክንያት ያልተሟላ ቡድን ይዘው ወደ ሜዳ በመግባት የሚያክላቸው አልተገኘም። ከሁሉም በላይ አስገራሚው ጉዳይ እና ነገም የሚጠበቀው ግን ቡድኑ ሜዳ ላይ የሚያሳየው የተለየ ትጋት ነው።

በተለይም እንደ ሰበታ ዓይነት የኳስ ቁጥጥርን የሚያዘወትር ቡድንን ለመግጠም ከኳስ ውጪ ያለው ጥንቃቄ አዘል አደረጃጀት እና ክፍተቶችን በንቃት የመሸፈን ብቃት አሁን ላይ ድቻዎች ጋር በሚገባ አለ። ኳስን ካሸነፉ በኋላም ወደ ግብ ደጃፍ ደርሶ ከባድ ሙከራዎችን ማድረግ ቡድኑ እምብዛም ሲቸግረው አይታይም። ይህ መሆኑ እና ቡድኖቹ የተለያየ የአጨዋወት ምርጫ ያላቸው መሆኑ በራሱ የጨዋታው ውበት ይሆናል ሊባል ይችላል። ነገር ግን ባለፈው ጨዋታ 8 የሜዳ ላይ ተጫዋቾች ብቻ ቀርተውት የነበረው ድቻ ነገስ ኮቩድ ምን ዓይነት ውጤት ይዞበት ይመጣል የሚለው ጉዳይ ይበልጥ አሳሳቢ ነው።

የሁለቱም ቡድኖች የኮቪድ ውጤት ነገ የሚታወቅ ሲሆን ብቸኛው የጉዳት ዜና ግን የሰበታው የጌቱ ኃይለማርያም መሆኑን ማወቅ ችለናል።

የእርስ እርስ ግንኙነት

– በፕሪምየር ሊጉ የተመዘገበ የመጀመሪያ ግንኙነታቸው በነበረው የዘንድሮው ጨዋታ ያለ ግብ ተለያይተዋል።

* ወቅታዊው የኮቪድ ወረርሺኝ በቡድኖቹ የስብስብ ምርጫ ላይ እያሳደረ ካለው ተለዋዋጭነት አንፃር ግምታዊ አሰላለፍ ለማውጣት አዳጋች በመሆኑ የወትሮው የአሰላለፍ ትንበያችን በዳሰሳው ያልተካተተ መሆኑን እንገልፃለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ