ቅድመ ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ

የቀጣዩ ዳሰሳችን ትኩረት የነገ ምሽቱ ጨዋታ ይሆናል።

በመካከላቸው በባህር ዳር የበላይነት የሰባት ነጥቦች እና የአራት ደረጃዎች ልዩነት ይኑር እንጂ ይህ ጨዋታ ጥሩ ፉክክር እንደሚኖርበት መናገር ይቻላል። የጣና ሞገዶቹ ማሸነፍ ከቻሉ በዚህ ሳምንት አራፊ ከሆነው ኢትዮጵያ ቡና ሁለተኛነቱን የመረከብ ዕድል በመኖሩ ውጤቱ አብዝቶ ያስፈልጋቸዋል። ኃይቆቹም የሚያስከፋ ሁኔታ ላይ ባይገኙም የታችኛውን የሰንጠረዥ ክፍል ጣጣ ይበልጥ ለመራቅ ድልን ማሳካት አብዝቶ ይጠቅመዋል።

ኢትዮጵያ ቡናን በአስገራሚ የቡድን ሥራ መርታት የቻሉት ሀዋሳዎች በጅማው ጨዋታ ከትኩረት ማነስ የተያባቸው ባህሪ በድቻው ጨዋታ ላይ ደግሞ ይበልጥ ወደ መቀዛቀዝ ከፍ ብሎ ተመልክተነዋል። ከተጋጣሚያቸው አለመሟላት አንፃር በቀላሉ ሊያሸንፉ ይችላሉ ተብሎው ብዙ የተቸገሩበት የመጨረሻው ጨዋታ ለነገ ትምህርት የሚሰጥ ነው። ባህር ዳር ከተማ ጫን ብሎ በማጥቃህ የሚጫወት ቡድን ከመሆኑም አንፃር ኃይቆቹ እንደ ቡናው ጨዋታ ንቁ እና ቶሎ ምላሽ መስጠት የሚያስችል ብቃት ላይ እንዲገኙ የግድ ይላል። በተለይም የቡድኑ የመስመር ተሰላፊዎች ፈጠን ባለ የማጥቃት ሽግግር የግብ ዕድሎችን መፍጠር የመቻላቸው ነገር ለቡድኑ ወሳኝ ይሆናል። በመከላከሉም ረገድ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት በተለይ በሜዳው ቁመት መሀል ለመሀል የሚሰነዘረውን የተጋጣሚያቸውን ጥቃት ማቋረጥ እና ኳሶችን በቶሎ ወደ መስመሮች መበተን ለሀዋሳዎች ሁነኛ የጨዋታ መንገድ ሊሆን ይችላል።

ተከታታይ ሁለት ከባባድ ጨዋታዎችን አድርገው ሁለቴም ነጥብ የታጋሩት የጣና ሞገዶቹ ነገ ወደ ድል ለመመለስ ይበልጥ የማጥቃት ኃይላቸውን ጨምረው እንደሚገቡ ይጠበቃል። የተረጋጋ የተጫዋች ምርጫ ያለው ስብስባቸው በኮሮናው ፈተና በጥቂቱ ቢፈተንም አሁንም ዋናው መዋቅሩ አለመናጋቱ በጥንካሬው እንዲቀጥል አስችሎታል። የፋሲል እና የድሬዳዋ ጨዋታዎች ከሰጡት ፈተናም አንፃር ከኋላ በቀላሉ የማይከፈት ለተጋጣሚ ተደራራቢ ጥቃት ተመሳሳይ ምላሽ መስጠት የሚችል ቡድን መሆኑን አሳይቷል። ነገም ከቡድኑ የሚጠበቀው እንቅስቃሴ ከዚህ የተለየ የሚሆን አይመስልም። በዋነኝነት የሀዋሳን የመስመር ጥቃቶች የመመለሱ ነገር የቡድኑ ትኩረት ሊሆን ሲችል በቅብብሎች ላይ ተመስርቶ በፍጥነት በተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ መሞከሩም የሚቀር አይመስልም። ከሁሉም በላይ ግን በሚፈጥረው ጫና ልክ ግቦችን ለማስቆጠር መትጋቱ ላይ ተሻሽሎ መቅረብ ይኖርበታል። እርግጥ ነው የአማካይ ክፍል ተጫዋቾቹ ግብ አነፍናፊ ቢሆኑም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ግብ ያልቀናው የፊት መስመርም በቶሎ ወደ አስቆጣሪነቱ መመለስ ይኖርበታል።

ይህ በእንዲህ እያለ የተጋጣሚዎቹን የጨዋታ ዕቅድ እና የስብስብ ምርጫ የሚወስነው የኮቪድ ምርመራ ውጤት እስካሁን ባይታወቅም ሁለቱም ከተጫዋቾች ጉዳት ነፃ መሆናቸውን ማወቅ ችለናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ሦስት ጊዜ ተገናኝተው ሁለቱን በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቁ የዘንድሮው ግንኙነታቸው በሀዋሳ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል። እስካሁንም ሀዋሳ ሦስት ባህር ዳር ደግሞ ሁለት ግቦችን አስቆጥረዋል።

* ወቅታዊው የኮቪድ ወረርሺኝ በቡድኖቹ የስብስብ ምርጫ ላይ እያሳደረ ካለው ተለዋዋጭነት አንፃር ግምታዊ አሰላለፍ ለማውጣት አዳጋች በመሆኑ የወትሮው የአሰላለፍ ትንበያችን በዳሰሳው ያልተካተተ መሆኑን እንገልፃለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ