ወላይታ ድቻ እና ኮቪድ ምርመራ ውጤት…

በድሬዳዋ እየተካሄደ በሚገኘው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ በኮቪድ ምክንያት ክፉኛ እየተቸገረ የሚገኘው ወላይታ ድቻ የዛሬው የምርመራ ውጤት ታውቋል።

በድሬዳዋ ውድድር ላይ ከየትኛውም ቡድን በበለጠ የኮሮና ተጠቂ ቁጥር በማስመዝገብ ቀዳሚ የሆኑት ወላይታ ድቻዎች ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች የተሟላ ቡድን ይዘው ወደ ሜዳ መግባት ተቸግረው ቆይተዋል። በተለይም ከሀዋሳ ከተማ ጋር በነበረው የ19ኛ ሳምንት ጨዋታ ሀያ አንድ ተጫዋቾች በኮሮና በመያዛቸው አሰልጣኝ ዘላለም ሺፈራው ነፃ የሆኑት አስራ አንድ ተጫዋቾችን ብቻ ያለ ተቀያሪ ይዘው ሁለት ግብጠባቂዎች ደግሞ ከሚናቸው ውጭ በአጥቂነት ማጫወታቸው ይታወቃል።

ከኮቪድ ውጤት ጋር በተያያዘ ሰሞነኛው የሊጉ መነጋገርያ ቡድን የሆኑት ወላይታ ድቻዎች ከትናንት በስቲያ አዲስ አበባ የኮቪድ ምርመራ አድርገው አሁን ውጤቱ ደርሷቸዋል። በዚህም መሠረት ባለፈው ያጣቸው 21 ተጫዋቾች ጨምሮ ሁሉም የቡድኑ አባለት ነፃ መሆናቸው ተነግሯቸዋል። ይህም የተሟላ ስብስቡን ከማግኘት አንፃር ለቡድኑ መልካም ዜና ሆኗል።

በተቃራኒው ደግሞ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ዛሬ በኮቪድ ምክንያት ቡድናቸውን የማይመሩ ሲሆን ምክትላቸው አሰልጣኝ ዳዊት ሀብታሙ ቡድኑን እንደሚመሩ ለማወቅ ችለናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ