የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 1-0 ባህር ዳር ከተማ

ሀዋሳ ከተማ ባህር ዳርን 1-0 ከረታበት ጨዋታ ፍፃሜ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ለሱፐር ስፖርት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ሙሉጌታ ምኅረት (ሀዋሳ ከተማ)

መስፍን፣ ብሩክ እና ወንድማገኝ ተሳቡን የተረዱበት መንገድ እና ጨዋታውን ስለማቅለላቸው

በታክቲኩ ረገድ እንደውም እኔ እንዳሰብኩት አልነበሩም። ወጣቶች ስለሆኑ ጉልበት ሲያባክኑም ነበር። ያም ሆኖ ወጣት እንደመሆናቸው ብዙ መስራት ይችላሉ።

ባህር ዳሮች ኳስ እግራቸው ስር ብዙ እንዳይቆይ ስለማሰባቸው

በመጀመርያው አጋማሽ እኛም ለመጫወት ነበር የፈለግነው። ሆኖም የምንፈልገውን ቶሎ ስላገኘን ከእረፍት በኋላ ወደ ኋላ ሆነን ለመጫወት ሞክረናል። ባህርዳሮች በኳስ መቆጣጠርም በአየር ኳስም ለመጫወት ሞክረው ያንን ለመቆጣጠር ችለናል።

ስለ ምኞት ቀጣዩ ጨዋታ አለመኖር

(ከሲዳማ ቡና ጋር ለሚደረገው ጨዋታ) ቢኖር ጥሩ ነበር። የቡድኑ ምርጥ ተከላካይ ነው። ነገር ግን ሌሎች ወጣት ተጫዋቾች ስላሉ መተካት እንችላለን።

ታደሰ ጥላሁን (ባህር ዳር /ምክትል አሰልጣኝ)

የፍቅረሚካኤል ዓለሙ አለመኖር የፈጠረው ክፍተት

በተወነ መልኩ የሚታይ ነገር ነው። አሰዛ ቦታ ላይ ያለውን ጫና ተቋቁሞ የሚወጣው እሱ ነው። የከፋ ባይሆንም ክፍተት ታይቷል። ያንን ለማስተካከል ተጫዋቹ አገግሞ እስኪመጣ እኛ መስራት ያለብንን መስራት አለብን።

በማጥቃት እንቅስቃሴ ስለነበረው ጉጉት

ከመጀመርያው ጀምሮ ጉጉት ነበር። የማሸነፍ ፍላጎታችን ከፍተኛ ስለነበር በተጫዋቾቹ ላይ ችኮላ እና አለመረጋጋት ይታይባቸው ነበር። ጨዋታው ማለቅ የነበረበት ከእረፍት በፊት ነበር። ሁለት እድሎች ፍፁም እና ግርማ ካልጠቀሙ በኋላ ነው ጎልም የተቆጠረብን።

በተጋጣሚ የጎል ክልል በቁጥር ስለመብዛት

ከእረፍት በኋላ የተሻለ ነበር። ከእረፍት በፊት ወደ ጎል የደረስናበቸው አጋጣሚዎች ውስን ናቸው። ከእረፍት በኋላ ግን እነሱም ለማስጠበቅ ሲጫወቱ ስለነበር ጫና ፈጥረን ያደረግነው እንቅስቃሴ ጥሩ ነው። ግን ጎል በማስቆጠርም አልሳካልንም፤ የረባ ሙከራም አላደረግንም። የጨዋታው ፍሰት ግን ጥሩ ነበር።

ስለ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቦታ

ከቦታው እየሸሸ ነው ማለት አይቻልም። ካለው የነጥብ መቀራረብ አንፃር ስታየው ይህ ጨዋታ ወሳኝ ነበር። ነገር ግን ወጣን የሚያስብል አይደለም። ወደፊት ብዙ ቻሌንጅ ይጠብቀናል። በዛ ውስጥ የምንፈልገውን ነገር አሳክተን እዛ ላይ እንደርሳለን ብዬ አስባለሁ።


© ሶከር ኢትዮጵያ