ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል

አንድ ግብ የተስተናገደበት የሀዋሳ ከተማ እና ባህር ዳር ከተማ ጨዋታ በሀዋሳ አሸናፊነት ተገባዷል።

ወላይታ ድቻን በመርታት ለዚህኛው ጨዋታ የቀረቡት የሀዋሳ ከተማው አሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ድል ካደረጉበት ጨዋታ ሦስት ተጫዋቾችን ለውጠዋል። በዚህም ሄኖክ ድልቢ፣ ዮሐንስ ሴጌቦ እና ቸርነት አውሽን በማሳረፍ መስፍን ታፈሰ፣ ኤፍሬም አሻሞ እና ኤፍሬም ዘካርያስን በቋሚ አሰላለፋቸው አካተዋል። እንደባለፈው ሳምንት ጨዋታ ሁሉ ዋና አሠልጣኙ ፋሲል ተካልኝን በዚህ ጨዋታም በኮቪድ ምክንያት የማያገኘው ባህር ዳር ከተማ በረዳት አሰልጣኙ ታደሰ ጥላሁን እየተመራ ወደ ሜዳ ገብቷል። ቡድኑም ከድሬዳዋ ጋር ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ ሁለት ለውጦችን አድርጓል። በዚህም በአምበሉ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና ሳለአምላክ ተገኘ ምትክ በረከት ጥጋቡ እና ወሰኑ ዓሊን ተክቷል።

ጥሩ ፉክክር በማሳየት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ገና በአምስተኛው ደቂቃ መሪ ለማግኘት ተቃርቦ ነበር። በዚህም ዳንኤል ደርቤ ያሻገረውን የመዓዘን ምት ብሩክ በየነ በግንባሩ ሞክሮት ለጥቂት ወጥቶበታል። ይህንን ሙከራ ካስተናገዱ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ በፈጣን እንቅስቃሴ ሀዋሳ የግብ ክልል የደረሱት ባህር ዳሮች ደግሞ በራሳቸው በኩል እጅግ ለግብ የቀረበ ጥቃት ፈፅመው ተመልሰዋል። በዚህም ወሰኑ ዓሊ በቀኝ መስመር ያገኘውን ኳስ በጥሩ ቅልጥፍና እየገፋ ሄዶ ለፍፁም ጥሩ ኳስ ቢያመቻችለትን የፍፁምን ብዙም ያልጠነከረ ኳስ ሜንሳህ ሶሆሆ አምክኖታል።

ጥሩ ጥሩ የግብ ሙከራዎችን ማስተናገድ የቀጠለው ጨዋታው በ13ኛው ደቂቃ ሌላ ዒላማውን የጠበቀ ጥቃት አስመልክቷል። በዚህም ከመልስ ውርወራ የተነሳውን ኳስ የባህር ዳር ተከላካዮች ሲመልሱት የፍፁም ቅጣት ምቱ ጫፍ ላይ ሆኖ ያገኘው አለልኝ አዘነ ጥሩ ጥቃት ቢፈፅምም የግብ ዘቡ ፅዮን መርዕድ ተቆጣጥሮታል። በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ተሽለው የታዩት ሀዋሳዎች የሚያገኟቸውን ኳሶች ቶሎ ቶሎ ወደ መስመር በማውጣት የማጥቂያ አማራጭ ሲፈልጉ ታይቷል። ባህር ዳሮች ደግሞ ከወገብ በላይ በሚገኙት ፈጣን ተጫዋቾቻቸው ብቃት እየታገዙ ጥቃት ለመሰንዘር ሲጥሩ ተስተውሏል።

የአሠልጣኝ ሙሉጌታ ተጫዋቾች በ30ኛው ደቂቃ የፂዮን ጀርባ የሚገኘውን መረብ በመፈለግ ጥቃት ሰንዝረዋል። በዚህ ደቂቃም ከመዓዘን የተሻገረው ኳስ አለልኝ በግንባሩ ጨርፎት ምኞት ጋር የደረሰ ቢሆንም ተከላካዩ ወደ ግብ የመታው ኳስ ዒላማውን ስቶበት ወደ ውጪ ወጥቷል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በተቃራኒው ሜንሳን ለመፈተን የታተሩት ባህር ዳሮች መሪ ሊሆኑበት የሚችለውን አጋጣሚ በሚያስቆጭ ሁኔታ አምክነዋል። በዚህም የሀዋሳ ተከላካዮች የሰሩትን የኳስ የቅብብል ስህተት ተጠቅሞ የተገኘውን ኳስ ፍፁም ለግርማ ቢሰጠውም ከግብ ጠባቂው ጋር በቅርብ ርቀት የተገናኘው ግርማ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ጥሩ እንቅስቃሴ እየታየበት የነበረው ጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ ሊገባደድ አራት ደቂቃዎች ሲቀሩት ጎል አስተናግዷል። በዚህም ወንድማገኝ ኃይሉ ከብሩክ የተረከበውን ኳስ በጥሩ ቅልጥፍና እና ቦታ አያያዝ እየገፋ ሄዶ ወደ ጎል የመታው ኳስ መረብ ላይ አርፎ ሀዋሳ መምራት ጀምሯል። አጋማሹም በወንድማገኝ ብቸኛ ጎል ተጠናቋል።

ለግብ የቀረበ የጠራ ሙከራ ለማስተናገድ ደቂቃዎች የፈጁበት የሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ቀዝቀዝ ባለ እንቅስቃሴዎች ታጅቦ መደረግ ቀጥሏል። በአጋማሹ ላይ ግን ባህር ዳር ከተማዎች በቶሎ ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል በመፈለግ ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ሲንቀሳቀሱ ታይቷል። ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ አብዛኛውን የአጋማሹን ክፍለ ጊዜ ያገኙትን ሦስት ነጥብ እንዳያጡ በሚያደርጋቸው የመከላከል አደረጃጀት ላይ በማሳለፍ ከኳስ ውጪ ሲጫወቱ ታይቷል። አልፎ አልፎ ግን ባህር ዳሮች ለማጥቃት ትተውት የሚወጡትን ሰፊ ቦታ በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ተጠቅመው ግብ ለማስቆጠር ሲታትሩ ነበር። በተጠቀሰው እንቅስቃሴም በ66ኛው ደቂቃ መስፍን ታፈሰ ጥሩ ኳስ ወደ ግራ ባዘነበለ ቦታ ላይ አግኝቶ የነበረ ቢሆንም ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በብዙ መስፈርቶች በዚህኛው አጋማሽ ተሽለው የታዩት ባህር ዳሮች ከተጋጣሚያቸው በበለጠ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበራቸው ቢሆንም ግዙፎቹን የሀዋሳ ተከላካዮች አልፎ ግብ ማስቆጠር ተራራን የመግፋት ያክል ከብዷቸው ታይቷል። ቡድኑም የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾቸን ቀይሮ ወደ ሜዳ ቢያስገባም ኳስ እና መረብን ማገናኘት ተስኖታል። በ77ኛው ደቂቃ ግን ፍፁም ራሱ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር ሞክሮ ለጥቂት ወጥቶበታል። ከዚህ ውጪ ግብ ቡድኑ በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ለመድረስ ባይቸገርም የጠራ የግብ ማግባት ዕድሎችን መፍጠር ተስኖት ሦስት ነጥብ አስረክቦ ወጥቷል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በሀዋሳ ከተማ አንድ ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ሁለተኛ ተከታታይ ድላቸውን የተቀዳጁት ሀዋሳ ከተማዎች ነጥባቸውን 27 በማድረስ ከሰባተኛ ደረጃ ወደ ስድስተኛ ደረጃ ተሸጋግረዋል። ከአስራ አንድ ጨዋታዎች በኋላ (በ7ኛ ሳምንት በሀዋሳ 2-1) ሽንፈት ያስተናገዱት ባህር ዳሮች ደግሞ በ31 ነጥቦች ያሉበት ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ