ቅድመ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ጅማ አባ ጅፋር

ከነገ የሊጉ መርሐ ግብሮች ቀዳሚውን የተመለከቱ ነጥቦችን እንዲህ አንስተናል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በሸገር ደርቢ ወሳኝ ድል ካስመዘገበ በኋላ በወራጅ ቀጠናው ከሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር ጋር ይገናኛል። የባህር ዳር ከተማን የዛሬ ሽንፈት ተከትሎም ጊዮርጊስ ጨዋታውን ወደ ሦስተኛ ደረጃ ከፍ የሚልበትን ዕድል ለማሳካት የሚያደርግ ይሆናል። በሰበታ ከተማ ሽንፈት የደረሰበት ጅማ አባ ጅፋር በበኩሉ በስድስት ነጥቦች የራቀው የወራጅ ቀጠናውን መውጪያ ደጃፍ ለመጠጋት ከባዱን ፈተና ይጋፈጣል።

ዳግም ወደ ድሬዳዋ ተመልሰው ፈታኝ የነበረውን የቡና ጨዋታ ማሸነፍ የቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ድሉ በአዕምሮ ይበልጥ ጠንክረው እንዲመጡ እንደሚያደርጋቸው ግልፅ ነው። በጨዋታው ከባዱን የሜዳ ሁኔታ በመቋቋም እስከ መጨረሻው በትኩረት መጫወታቸው ሲታይ ደግሞ ቡድኑ በአካል ብቃትም ተሻሽሎ ስለመመለሱ መናገር የሚያስችል ነው። አሰልጣኝ ፍራንክ ናታል ጊዮርጊስ እጅግ ተሻሽሎ በታየበት በዛ ጨዋታ መጨረሻ ላይ በዕለቱ የተከተሉትን አጨዋወት ሁሌ እንደማይተገብሩት መናገራቸው ግን ነገ ለየት ያለ ጊዮርጊስን እንድንጠብቅ ያደርገናል። በተለይም ተጋጣሚውን በራሱ ሜዳ ኳስ እንዳይጀመር የማስገደዱ ነገር ከጅማ ጋር አፅዕኖት ላይሰጠው ይችላል። ይልቁኑም ከቡናው ጨዋታ ባንፅፅር የተሻለ ከኳስ ጋር ለመቆየት የሚሞክር ከራሱ ሜዳ ከወጣ በኋላ ግን የግራ እና ቀኝ መስመሮችን በመጠቀም በቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ የሚሞክር ዓይነት ጊዮርጊስን ልናይ እንችላለን። ያም ቢሆን በተናጠል በተጫዋቾች ላይ የታየው ተነሳሽነት እና ከፍ ያለ ትጋት በነገው ዓይነት ጨዋታዎች ላይም ቀጥለው መታየታቸው ለቡድኑ ወሳኝ ይሆናል።

ጅማ አባ ጅፋር አሁንም መጥፎ የማይባል እንቅስቃሴ አሳይቶ ፣ ተጋጣሚውን ጫና ውስጥ ከትቶ እና ጎልም አስቆጥሮ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማሳካት ሳይችል ቀርቷል። ይህ ሁኔታ ከሰበታ ጋር ሲፈጠር ዘንድሮ ለሰባተኛ ጊዜ ነበር። ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ ጨዋታ ከሚጀምርበት ቅፅበት አንስቶ መከላከል ጅማ እስካሁን ከየትኛውም ተጋጣሚ ጋር ያላደረገው ጉዳይ ነው። ነገም እንደ እስከዛሬው ወደ ፊት ገፍቶ ለመጫወት ዓይናፋር ያልሆነ ቡድን ከአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ይጠበቃል። ከተጋጣሚው የኋላ መስመር የቅርብ ጨዋታዎች ጥሩ መሆን አንፃር ጅማ በፈጣን ሽግግሮች ግብ አፋፍ ደርሶ ዕድሎችን የሚፈጥርባቸው ቅፅበቶች እንደልብ ባይገኙም እንኳን ቡድኑ ይህን ከማድረግ ወደ ኋላ የሚል አይመስልም። ነገር ግን የማጥቃት ፍላጎትን በሚያሳይባቸው ጊዜያት ግቡን በምን መልኩ መጠበቅ እንዳለበት አስቦበት እንደሚመጣ ይጠበቃል። ካልሆነ ግን መሪነቱን ቀድሞ አግኝቶ ካላገገመባቸው ጨዋታዎች አንፃር በቶሎ ግቦች ከተቆጠሩበት ደግሞ ይበልጥ ችግር ውስጥ እንሳይገባ የሚያሰጋ ነው።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ቡድኖቹ ለአምስት ጊዜ ከተገናኙባቸው አጋጣሚዎች ውስጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሦስት በማሸነፍ የበላይ ሲሆን ጅማ አባ ጅፋር ሁለቴ ድል አድርጎ አንዱ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። በአምስቱ ግንኙነቶች ቅዱስ ጊዮርጊስ 9 ጎሎችን ሲያስቆጥር ፤ ጅማ 4 ጎሎችን አስቆጥሯል።

* ወቅታዊው የኮቪድ ወረርሺኝ በቡድኖቹ የስብስብ ምርጫ ላይ እያሳደረ ካለው ተለዋዋጭነት አንፃር ግምታዊ አሰላለፍ ለማውጣት አዳጋች በመሆኑ የወትሮው የአሰላለፍ ትንበያችን በዳሰሳው ያልተካተተ መሆኑን እንገልፃለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ