በነጥብ እኩል ሆነው በግብ እዳ በአንድ ደረጃ የተለያዩት ድሬዳዋ ከተማ እና ሲዳማ ቡና የሚያደርጉትን ወሳኝ ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
ካለፉት ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ የራሳቸው ያደረጉት ድሬዳዋ ከተማዎች ከስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ ጅማ አባጅፋር ላይ የተቀዳጁነት ድል ለመድገም እና በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ያሳዩትን መሻሻል በውጤት ለማሳጀብ የነገውን ፍልሚያ ይጠባበቃሉ። በተቃራኒው ለረጅም ጊዜያት ከነበሩበት የወራጅ ቀጠና ለመውጣት እየታተሩ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ በሊጉ መሪ ከተረቱበት ጨዋታ በፊት የነበሩበትን የአሸናፊነት መንገድ ዳግም ለማግኘት እና የነገ ተጋጣሚያቸውን በማሸነፍ ከአስጊው ቀጠና ለመውጣት ሦስት ነጥብን እያለሙ ለጨዋታው ይቀርባሉ።
በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻል እያሳዩ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች ነገም በጥሩ አቀራረብ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይገመታል። በተለይ ቡድኑ በቅርብ ጨዋታዎች እያሳየ የሚገኘው ከፍተኛ የተነሳሽነት ስሜት ድንቅ ነው። ይህ የተነሳሽነት ስሜቱም በነገው ጨዋታ የሚደገም ከሆነ በጎ ነገሮችን ከፍልሚያው ሊያገኝ ይችላል። እርግጥ ይህ የበዛ ጨዋታን የማሸነፍ ፍላጎት በአንዳንድ አጋጣሚዎች ዋጋ ሲያስከፍለው ቢታይም በቁርጠኝነት ጨዋታዎችን ኮስተር ብሎ መቅረቡ መልካም ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ይህ ወደአላስፈለገ ጉጉት የሚከተው ፍላጎት ፊት መስመር አካባቢ መስተዋል የለበትም። ከዚህ ውጪ ግን የሞክሼዎቹ ዳንኤሎች ጨዋታን የመቆጣጠር ብቃት፣ የአጥቂ አማካዮች ፍጥነት እና የግብ ዘቡ ፍሬው ምርጥ ብቃት ላይ መገኘት ለድሬዳዋ መልካም ነገሮችን ሊያስገኝ እንደሚችል ይገመታል።
የሊጉ ሦስተኛው ብዙ ጎሎችን ያስተናገደው ድሬዳዋ (26) በነገው ጨዋታ የኋላ መስመሩ በአስተማማኝ ደረጃ ላይ መገኘት ይጠበቅበታል። በተለይ ቡድኑ የሚገጥመው ቀስ በቀስ የሰላ የአጥቂ መስመር እያገኘ የሚገኘውን ሲዳማ መሆኑ ሲታሰብ የአሠልጣኝ ዘማርያም ተጫዋቾች አደጋ ላይ እንዳይወድቁ የኋላ መስመራቸውን ማጠናከር የግድ ይላቸዋል።
ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ግብ ግብ የገጠሙት ሲዳማዎች ዘግየት ብለው የነቁ ቢመስልም ከአስጊው ቀጠና ለመውጣት እንደ ነገው አይነት እና በቅርብ ርቀት ከሚበልጧቸው ብድኖች ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታዎችን በድል መወጣት ያስፈልጋቸዋል። በአሠልጣኝ ገብረመድህን የሚመራው ቡድኑን እንደ ድሬዳዋ ሁሉ በቅርብ ጨዋታዎች የተነቃቃ እና ዘንድሮ ያጣውን ጠንካራነት ያገኘ ይመስላል። በተለይ ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች ደጋፊዎች ለወትሮ ለደረጃ የሚፎካከረውን ጠንካራ ቡድን እየተመለከቱ ይመስላል። ከምንም በላይ ደግሞ እስከ ቅርብ ጊዜያት የሊጉ ደካማ የአጥቂ ክፍል ባለቤት የሆነው ስብስቡ የስልነት ችግሩን የቀረፈ ይመስላል። ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ብቻ እንኳን ቡድኑ ከበፊቶቹ አስራ አራት ጨዋታዎች ካስቆጠራቸው ጎሎች (8) በሦስት ያነሱ ግቦችን ማስመዝገቡ (5) ሲታይ ምን ያህል የፊት መስመሩ እንደጠነከረ ያመላክታል።
ሲዳማ ከማጥቃት በተጨማሪ ጨዋታዎችን በጥሩ ፍጥነት እና ሀይል ለማድረግ የሚጥርበት መንገድም ለተጋጣሚ ፈተና ነው። ይህ ቢሆንም ግን በጨዋታው ከተጋጣሚው በበለጠ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ የሚገባው ሲዳማ ስለሆነ በመከላከሉ ረገድ ክፍተት እንዳያሳይ ያሰጋል። በፋሲሉም ጨዋታ የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት በአንዳንድ አጋጣሚዎች ጥያቄዎች ሲነሱበት ስለነበረ ነገም በዚህ ረገድ ተጋጣሚው እንዳይፈትነው ያሳስባል። በተለይም ፈጣኖቹ የድሬ የአጥቂ አማካዮች ይህንን ክፍተት ሊጠቀሙ ስለሚችሉ ቡድኑ ማጥቃቱ ላይ ብቻ ሳይሆን መከላከሉ ላይም ትኩረት ሰጥቶ ወደ ሜዳ መግባት አለበት።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– በሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ15 ጊዜያት ተገናኝተው ሲዳማ ቡና በ8 ድል ቀዳሚ ሲሆን ድሬዳዋ 1 ጊዜ ብቻ አሸንፏል ፤ በቀሪዎቹ 6 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። እስካሀን ሲዳማ 17 ጎሎች ሲያስቆጥር ድሬዳዋ 7 አስመዝግቧል።
* ወቅታዊው የኮቪድ ወረርሺኝ በቡድኖቹ የስብስብ ምርጫ ላይ እያሳደረ ካለው ተለዋዋጭነት አንፃር ግምታዊ አሰላለፍ ለማውጣት አዳጋች በመሆኑ የወትሮው የአሰላለፍ ትንበያችን በዳሰሳው ያልተካተተ መሆኑን እንገልፃለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ