የከፍተኛ ሊግ ውሎ | መከላከያ ማደጉን ሲያረጋገጥ አርባ ምንጭ ከጫፍ ደርሷል

የከፍተኛ ሊግ በዛሬ ውሎው መከላከያ ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደጉን ያረጋገጠበትን፣ አርባምንጭም በእጅጉ የተቃረበበትን እንዲሁም ወራጅ ቡድኖች የታወቁበት እና አወዛጋቢ ጨዋታዎች ተስተናግደውበታል።

ዘጠኝ ክለቦች በሚገኙበት የምድብ ሀ ላይ ተወዳዳሪ የነበረው መከላከያ ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን 1ለ0 በመርታት ወደ 2014 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አንድ ጨዋታ እየቀረው ማደጉን አረጋግጧል፡፡ ረፋድ 4፡00 በተካሄደው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ተንፀባርቶ የነበረ ቢሆንም ኳስ በመቆጣጠሩ ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን፤ በሙከራ ረገድ መከላከያ ተሽለው ታይተዋል፡፡ በሳሙኤል ሳሊሶ የሶስተኛ ደቂቃ የቅጣት ምት ኳስ ወደ ደብረብርሃን የግብ ክልል መድረስ የቻሉት መከላከያዎች የተሻለ ወደ ጎል ቢቀርቡም ጎል ሳያስቆጥሩ ወደ እረፍት አምርተዋል።

በ2ኛው አጋማሽ መከላከያዎች በቶሎ ግብ አግኝተዋል፡፡ ጋናዊው የመስመር አጥቂ ሰሎሞን ዴቪድን ቀይሮ የገባው የቀድሞው የወልዋሎ ፈጣኑ የመስመር አጥቂ ሰመረ ሀፍታይ በደብረብርሃኑ ተከላካይ አዲስ ገብረመስቀል በሳጥን ውስጥ በመጠለፉ ፌድራል ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ የሰጡትን የፍፁም ቅጣት ምት አምበሉ ቴዎድሮስ ታፈሰ ከመረብ በማሳረፍ ጨዋታው 1ለ0 እንዲጠናቀቅ አድርጓል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ መከላከያ ወደ ቀጣዩ አመት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ማለፉን ሲያረጋግጥ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስ ዕድል የነበረው እና ትላንት ደሴ ከተማን 3ለ1 አሸንፎ የነበረው ኢትዮ ኤሌክሪክ በአንፃሩ በሁለተኝነት ማጠናቀቁን አረጋግጧል፡፡

ከምድብ ሀ 10፡00 ላለመውረድ እየታገለ የነበረው ወልዲያ እና ፌድራል ፖሊስን ያገናኘው ጨዋታ በአሰልቺ እንቅስቃሴ እና ጭቅጭቅ ታጅቦ ያለ ጎል ተጠናቋል፡፡ ወልዲያ ማሸነፍ አልያም አንድ ነጥብ ማስመዝገብ በሊጉ መቆየቱን የሚያረጋግጥበት ሲሆን ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን በአንፃሩ በሊጉ ለመቆየት የወልዲያን መሸነፍ የግድ ይጠብቅ ነበር፡፡

አንድም የጠሩ የግብ አጋጣሚዎችን ከእንቅስቃሴ ውጪ መመልከት ያልቻልንበት ይሄ ጨዋታ ልክ 40ኛው ደቂቃ ላይ ውዝግብ አስከስቷል፡፡ የሰሜን ሸዋ ደብረብርሃንን የቡድን አመራሮች ጨዋታውን እየተከታተሉ የነበሩ ሲሆን ሆን ተብሎ ከአቅም በታች ቡድኖቹ እየተጫወቱ ነው በሚል ለአወዳዳሪው አካል ስሞታን አሰምተው ጨዋታውን እየታዘቡ የነበሩት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ አሊሚራህ መሐመድ እና የከፍተኛ ሊግ ሰብሳቢው ሻምበል ሀለፎም ከምድቡ ሰብሳቢ እና ከዕለቱ ዳኞችና ኮሚሽነሮች ጋር በጋራ በመሆን የሁለቱም ክለብ አምበሎች እና ቡድን መሪን ጭምር በመጥራት አግባብ ያልሆነ ነገርን እየተመለከቱ መሆኑን በመግለፅ ይህ ከቀጠለ ግን በዳኛው ሪፖርት መሠረት እንደሚወስኑ የማስጠንቀቂያ መልዕክት ሲያስተላልፉ ተመልክተናል። ጨዋታውም ቀጥሎ አንድም የረባ ነገርን ሳንመለከትበት ያለጎል ተጠናቋል፡፡ ይህን ውጤት ተከትሎ ረፋድ በመከላከያ 1ለ0 ተሸንፎ የነበረው ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን ወሎ ኮምቦልቻን በመከተል ሁለተኛው ወራጅ ቡድን ሆኗል፡፡

በምድብ ለ ወልዲያ ላይ በተስተካካይ ጨዋታ ረፋድ ላይ በአቃቂ ቃሊቲ እና ሀምበሪቾ መካከል የተደረገ ሲሆን በ67ኛው ደቂቃ አጥቂው ዳግሞ በቀለ ባስቆጠራት ጎል ሀምበሪቾዎች 1-0 አሸናፊ ሆነዋል፡፡

የቀን እና የሰዓት ማሻሻያ የተደረገበት የአርባምንጭ እና የየካ ክፍለ ከተማ ጨዋታ 10፡00 ሲል በነቀምት ስታዲየም ተደርጎ አርባምንጭ ከተማ የካን 2ለ1 አሸንፏል፡፡ በላይ ገዛኸኝ እና ልማደኛው የክለቡ ጎል አስቆጣሪ ፍቃዱ መኮንን የአርባምንጭን የድል ጎሎች ከመረብ ሲያሳርፉ በኮቪድ 19 የተነሳ አሰልጣኝ ባንተይርጋ ጌታቸው ላልመሩት የካ ክፍለ ከተማዎች በመጨረሻው ደቂቃ ብቸኛዋን ጎል ኪሩቤል ይጥና አስቆጥሯል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ አርባምንጭ ከተማዎች ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማለፍ ከቀጣዩ ጨዋታ አንድ ነጥብን ማሳካት በቂያቸው ይሆናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ