“ይሄ ድል ለእኔ ታሪካዊ ነው” ቴዎድሮስ ታፈሰ (መከላከያ)

ያለፉትን ስድስት ዓመታት በወጥነት መከላከያን እያገለገለ የሚገኘውና ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲመለስ ካስቻሉ ቁልፍ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ቴዎድሮስ ታፈሰ ይናገራል።

መከላከያ በ2011 ከፕሪምየር ሊጉ ሲወርድ የቡድኑ አያል የነበረው አማካዩ ዘንድሮ ክለቡ በከፍተኛ ሊጉ በምድብ ሀ ላደረገው ጠንካራ ጉዞ ለግብ የሆኑ ኳሶችን በማቀበል እና ጎሎችንም በማስቆጠሩ ረገድ የነበረው ድርሻ እጅጉን ላቅ ያለ ነበር፡፡ በ15ኛ ሳምንት ሰሜን ሸዋ ደብረብርሀንን 1ለ0 ሲያሸንፍ ቡድኑን በአምበልነት ሲመራ የነበረው አማካዩ ብቸኛዋን ጎል በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሮ መከላከያ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲሻገር አስችሏል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም ቴዎድሮስ ታፈሰ ስሜቱን አጋርቶናል፡፡

“በጣም ደስታ ነው የተሰማኝ። ይሄ ድል ለእኔ ታሪካዊ ነው። ምክንያቱም ቡድኑ ሲወርድ የተወሰንን ተጫዋቾች እዚህ ቡድን ውስጥ ነበርን። ያኔ የነበርን ተጫዋቾች ስንጫወት የነበረው በቁጭት ነበር። ያ ሁሉ አልፎ መከላከያን ወደሚገባው ቦታ መመለስ በመቻላችን ከሚገባው በላይ ደስታ ተሰምቶኛል

“ያኔ ስንወርድ በጣም ከባድ ጊዜን ነበር ያሳለፍነው። መውረድ የሌለበት ጥሩ ቡድን ነበር ነገር። ግን በአንዳንድ ስህተቶች ልንወርድ ችለናል። ወደነበርንበት ለመመለስ ደግሞ ይሄን ዓመት መጠቀም አለብን ብለን በእልህ በመጫወት አሳልፈናል፡፡ ዘንድሮ አንድነት እና ህብረት ስለነበረን አሳክተነዋል፤ በጣም በጣም ደስ ብሎኛል።

“ገና ዓመቱን ስንጀምር ያሰብነውን አሁን በደንብ አሳክተናል፡፡ ነገር ግን ከፍተኛ ሊግ ከፕሪምየር ሊግ በጣም የሚለይበት ነገር አለ። ጉልበት እና ኃይል የተቀላቀለበት አጨዋወት ይበዛል። ነገር ግን በውድድሩ ጥሩ ጥሩ ልጆችም ታይተውበታል። እንደ ቡድን ከአሰልጣኛችን ጋር በመሆን አንድ እና አንድ ለማሳለፍ ነበር ያን አሳክተናል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ