“ይህ የመጨረሻዬ አይደለም…” – ቸርነት ጉግሳ

በአስደናቂ አቋም ላይ ከሚገኘው ፈጣኑ የወላይታ ድቻ የመስመር አጥቂ ቸርነት ጉግሳ ጋር ቆይታ አድርገናል።

ዕድገቱ ፈጣን በመሆኑ ብዙም በታዳጊ ቡድን ቆይታ ሳያደርግ በ2009 ወደ ዋናው ቡድን በማደግ አቅሙን እያሳየ መጥቷል። ሆኖም የአሰልጣኝ መቀያየር እና የሊጉን ባህል በፍጥነት አለመላመዱን ተከትሎ ብዙም የመሰለፍ ዕድል ሳያገኝ። ይህም ቢሆን የመሰለፍ እድል ባገኘባቸው ጨዋታዎች ላይ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ማሳየት ቢችልም በወጥነት አቋሙን ለማሳየት ሳይችል ቆይቷል። አሁን ደግሞ ከአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ሹመት በኋላ ዳግም በተነቃቃው ቡድን ውስጥ ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል። በተለይም በድሬዳዋው ውድድር ላይ ያለው አበርክቶ ከፍ ወዳለ ደረጃ ደርሷል። ለዕድገቱ የወንድሞቹ አስተዋፆኦ የጎላ እንደሆነ የሚናገረው ቸርነት አሁን ስለሚገኝበት ሁኔታ እና በሒደት መድረስ ስለሚፈልገው ዕቅዱ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

” ሊጉ ሲጀመር አጀማመሬ ጥሩ አልነበረም። ለዚህም የጤናዬ ሁኔታ ጥሩ ያልነበረ መሆኑ ትንሽ ተፅእኖ አድርጎብኛል። ከረጅም የዕረፍት መልስ ወደ ውድድር መምጣታችንም ጥሩ ነገር እንዳላሳይ እክል ፈጥረውብኝ ነበር። ያው የራሴም አንዳንድ ነገሮች ነበሩ። በሚቀሩኝ ነገሮች ላይ ሰርቼ አሁን ያለሁበት ጊዜ ላይ እገኛለሁ።

” አሁን መሻሻሎች እያሳየሁ ነው። የቡድናችን አሰልጣኝ ሆኖ የመጣው ዘላለም ሽፈራው ጥሩ እያሰራኝ ያሉብኝን ክፍተቶች በደንብ እየነገረኝ እዛ ላይ በትኩረት እየሰራሁ ሙሉ ለሙሉ ወደምፈልገው ደረጃ ባልደርስም አሁን እየተሻሻልኩ መጥቻለሁ።

” ከወንድሜ ሽመክት ብዙ ነገር ተምሬያለሁ። እርሱን እያየው ነው ያደኩት። በዚህ ምክንያት ከእርሱ ብዙ ነገር ወስጃለሁ። ታታሪነቱን፣ ለለበሰው ማልያ የሚሰጠውን ክብር፣ ኳስ አገፋፉን በአጠቃላይ ብዙ ነገር የወሰድኩት ከሽመክት ነው። በእኔ ዕድገት ውስጥ እና መሻሻል የሽመክት አስተዋፆኦ በጣም በትልቁ እና በሰፊው አለ። ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የእርሱ ሚና በእግርኳስ ህይወቴ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው። ብዙ ነገር ነው የሚመክረኝ እርሱ ነው። በዚህ አጋጣሚ በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ።

” ሁልጊዜም ነፃ ሆኜ ስጫወት ደስ ይለኛል። ነፃ ስትሆን ብዙ ነገር የማድረግ ዕድልህ ይሰፋል። ማድረግ የምትፈልገውን ነገር ለማድረግ ትጠቀማለህ። ታክቲካል ነገሮችንም ለማድረግ ብዙ ባልቸገርም የበለጠ ነፃ ስሆን አቅሜን አውጥቼ እንድጠቀም ያደርገኛል። ያው ኳስ ተጫዋች ከሆንክ በሁሉም መልኩ ራስን ማዘጋጀት ይገባል።

” ይህ የመጨረሻዬ አይደለም። እኔ ውስጥ ያለው አቅም ገና ነው። ከዚህም በላይ ማሳየት እፈልጋለሁ። ይሄን አቅሜን በጎሎች የታጀቡ አድርጌ እንቅስቃሴዬን ማሳደግ እፈልጋለሁ። ማንም ሰው እንደሚያስበው ሀገርን ማገልገል በጣም ያስደስታል። ጊዜው ሲደርስ ሀገሬን ማገልገል እመኛለሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ