ሪፖርት | ዐፄዎቹ አንድ እጃቸውን የሊጉ ዋንጫ ላይ አሳርፈዋል

በደረጃ ሠንጠረዡ ግርጌ እና አናት ላይ የሚገኙት አዳማ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ያደረጉት ጨዋታ በሊጉ መሪ ቡድን አሸናፊነት ተገባዷል።

የአዳማ ከተማው አሠልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ከቀናት በፊት ከወልቂጤ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ ሦስት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም ደስታ ጌቻሞ፣ በቃሉ ገነነ እና ያሬድ ብርሀኑ በማሳረፍ ትዕግስቱ አበራ፣ ደሳለኝ ደባሽ እና ማማዱ ኩሊባሊን በቋሚ አሰላለፍ አካተዋል። በ20ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር በተመሳሳይ ነጥብ የተጋሩት ፋሲል ከነማዎች ግን ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ጨዋታውን ጀምረዋል።

ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት በ81 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና ኢትዮጵያ ሲሚንት ተጫዋች ፀጋዬ ተስፋዬ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት ተደርጓል። ከወትሮው ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ በተለየው ብራማ ቀን የተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያ ሙከራ ለማስተናገድ ስምንት ደቂቃዎች ወስዶበታል። በዚህም ደቂቃ የሊጉ መሪ ፋሲል ከነማዎች በዛብህ መለዮ ለአምሳሉ ጥላሁን አቀብሎት የግራ መስመር ተከላካዩ ከርቀት በሞከረው ኳስ ቀዳሚ ለመሆን ሞክረዋል። ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ወዲያው ምላሽ ለመስጠት ያሰቡ የሚመስለው አዳማ ከተማዎች ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ኤልያስ ማሞ የፋሲል ተጫዋቾች የሰሩትን የቅብብል ስህተት ተጠቅሞ በሞከረው ኳስ ግብ ለማግኘት ጥረዋል። ከአስር ደቂቃዎች በኋላም የግራ መስመር ተከላካዩ ሚሊዮን ሰለሞን ኤልያስ ከቅጣት ምት የተገኘን ኳስ ሳጥን ላይ ሲጥለው አግኝቶ ወደ ግብ ቢመታም ኳሱ ዒላማውን ስቶ ወደ ውጪ ወጥቶበታል።

የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበራቸው ፋሲል ከነማዎች በበኩላቸው የመጀመሪያው አጋማሽ የውሃ እረፍት ከመወሰዱ ከሰከንዶች በፊት እጅግ ለግብ ቀርበው ነበር። በዚህም ሽመክት ጉግሳ ከቀኝ መስመር ጥሩ ኳስ አሻግሮ የነበረ ቢሆንም አዳማ ሳጥን ውስጥ የነበሩት በዛብህ እና ሙጂብ ኳሱን ሳይጠቀሙበት ቀርቷል። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪም የቡድኑ አምበል ያሬድ ባየ የግብ ክልሉን ትቶ ኳስ እየገፋ በመምጣት ጥቃት ቢፈፅምም ኳሱ ሴኩምባ ካማራ ከሚጠብቀውን የግብ መረብ ርቆ ወደ ውጪ ወጥቷል። እጅግ ቀዝቃዛ እንቅስቃሴ የታየበት የመጀመሪያው አጋማሽም ያለ ግብ ተጠናቆ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

እጅግ ፍጥነቱ ዝግ ያለ የመጀመሪያ አጋማሽ ያሳለፈው ጨዋታው በዚህኛው አጋማሽ በመጠኑም ቢሆን ሞቅ ብሎ ታይቷል። ገና በተጀመረ በሁለተኛው ደቂቃም መሪ ለማግኘት ተቃርቦ ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ የመዓዘን ምት ያገኙት አዳማዎች አጋጣሚውን በመጠቀም በአብዲሳ ጀማል አማካኝነት ወደ ግብ ቢቀርቡም የፋሲል ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተውባቸዋል። አንድ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ብቻ ያደረጉት ፋሲል ከነማዎችም የማጥቂያ አማራጫቸውን አሻሽለው ወደ ሜዳ በመግባት አዳማን ማስጨነቅ ይዘዋል። በ55ኛው ደቂቃም ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ መሪ ሆነዋል። በዚህ ደቂቃም ሽመክት የግራ መስመር ተከላካዩን ሚሊዮንን በማለፍ ወደ ሳጥን የላከውን ኳስ ሙጂብ አግኝቶት መረብ ላይ አሳርፎታል።

ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል በመድረስ ረገድ እጅግ የተሻሻሉት ፋሲል ከነማዎች መሪነታቸውን የሚያሰፉበትን ጎል ለማግኘት መታተር ቀጥለዋል። በዚህም አምሳሉ በ60 እንዲሁም በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገባው ናትናኤል በ63ኛው ደቂቃ በሞከሯቸው ኳሶች የግብ ዘቡ ሴኩምባ ካማራን ፈትነዋል። በተቃራኒው በመጀመሪያዎቹ የአጋማሹ ደቂቃዎች ተዳክመው የታዩት አዳማዎች በ71ደቂቃ አቻ የሚያደርጋቸውን ጎል ለማግኘት ፋሲል የግብ ክልል ደርሰው ነበር። በዚህ ደቂቃም ተቀይሮ የገባው ሰይፈ ፈጣን የመስመር ላይ ሩጫ በማድረግ ራሱን የፋሲል የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በማስገባት ለኤልያስ ያቀበለውን እጅግ ጥሩ ኳስ የቡድኑ አምበል ሳይጠቀምበት ቀርቶ ያሬድ አምክኖበታለወ። ይህ ሙከራ እንዲደረግ የእርሱ የግል ጥረት አስፈላጊ የነበረው ሰይፈ ከደቂቃ በኋላም በግሉ ጥሩ ጥቃት ፈፅሞ ነበር።

ጨዋታው ቀጥሎም በ76ኛው ደቂቃ ፋሲል ከነማ ሁለተኛ ጎል አስቆጥረዋል። በዚህም ከርቀት የተላከውን ኳስ ያገኘው በዛብህ መለዮ በአንድ ንክኪ ኳስ እና መረብን በድንቅ ሁኔታ አገናኝቶ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል። ጨዋታው ከቁጥጥራቸው ውጪ እየሆነ የመጣው አዳማዎች ባላቸው ደቂቃ መፍጨርጨራቸውን ይዘዋል። በዚህም በ80ኛው ደቂቃ ከድር ኩሊባሊ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት በመጠቀም ኤልያስ ግብ ለማግኘት ታትሮ ነበር። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ግን ቡድኑ የማስተዛዘኛ ጎል አግኝቷል። በዚህም ተቀይሮ ወደ ሜዳ ከገባ በኋላ እጅግ ጥሩ እንቅስቃሴ እያሳየ የነበረው ሰይፈ ዛኪር ከአብዲሳ ጀማል የደረሰውን ኳስ መረብ ላይ አሳርፏል። በቀሪዎቹ ደቂቃዎችም ቡድኑ አቻ ለመሆን ቢጥርም ውጥኑ ሳይሰምር ጨዋታው በፋሲል ከነማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ በጨዋታው ሦስት ነጥብ ያገኙት ፋሲል ከነማዎች የዘንድሮውን የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ለማንሳት አንድ ጨዋታ ብቻ የሚያስፈልጋቸውን ሁነት ፈጥረው ከሜዳ ወተዋል። አዳማ ከተማዎች ደግሞ በ19 ጨዋታዎች በሰበሰቧቸወ 9 ነጥቦች የደረጃው ግርጌ ላይ ፀንተው ተቀምጠዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ