ኢትዮጵያ የምታስተናግደው የሴካፋ ውድድር የሚደረግበት ጊዜ እና ቦታ ታውቋል

የምስራቅ እና መካከለኛው የአህጉሪቱ ቀጠና ላይ የሚገኙ ብሔራዊ ቡድኖችን የሚያሳትፈው የሴካፋ ውድድር በየትኛው የኢትዮጵያ ከተማ እና መቼ እንደሚደረግ ታውቋል።

ከ1926 ጀምሮ መደረግ የጀመረው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ ውድድር የ2021 የውድድር ዓመት ፍልሚያውን እድሜያቸው ከ23 ዓመት በታች በሆኑ ተጫዋቾች በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት እንዲከናወን መወሰኑ ይታወቃል። ኢትዮጵያ የውድድሩ አዘጋጅ መሆኗ በተነገረበት ወቅት ደግሞ መቼ እና የት ከተማ እንደሚከናወን ሳይገለፅ አልፎ ነበር። አሁን ግን የውድድሩ አዘጋጆች ከጁላይ 3-18 (ከሰኔ 26- ሐምሌ 11) ድረስ ውድድሩ እንዲደረግ ጊዜያዊ ቀን ማውጣታቸው ታውቋል።

ይህንን ጉዳይ እንዲያረጋግጡልን የጠየቅናቸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን የተጠቀሰው ጊዜ ልክ መሆኑን አውስተው ፌዴሬሽናቸው ይህንን ውድድር በባህር ዳር ከተማ ለማድረግ ማሰቡን አስረድተውናል። ኃላፊው ጨምረውም በክረምት ወር የሚደረገውን የቀጠናው ውድድር በደማቅ ሁኔታ ለማከናወን የቅድመ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ይህንን ውድድር ለአራት ጊዜያት (1980፣ 1997፣ 1999 እና 2008) አዘጋጅታ እንደነበር ይታወሳል።


© ሶከር ኢትዮጵያ