የአሰልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 1-0 ሲዳማ ቡና

ጠንካራ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታ በድሬዳዋ አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞች ለሱፐር ስፖርት ይህንን ብለዋል።

አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ – ድሬዳዋ ከተማ

የጠበቁትን ስለማግኘታቸው

ውጤቱን በትክክል አግኝተነዋል። ነገር ግን የዛሬው ጨዋታ በሁለታችንም በኩል ጫና ነበረው። ተጋጣሚያችን መሀል ሜዳ ላይ የመከላከል ባህሪ ያለው የአማካይ ተጫዋች አልነበረውም። ስለዚህ ተጭነን ለመጫወት ለእኛ የተመቸ ነበር። ተደጋጋሚ ኳሶችን እንዳይዙ እየተጫንን ወደ ፊት እንሄድ ነበር። በአጠቃላይ ተሳክቶልናል ብዬ አስባለሁ።

ስለአማካይ ክፍላቸው

ኳስ ስናጣ የመስመር አጥቂዎቻችን ወደ ኋላ ተመልሰው አምስት ያደርጉልን ነበር አማካዩን። እነጁኒያስ ይህ ዓይነት ባህሪ ስላላቸው ነው መስመር ላይ ያወጣናቸው እንጂ ፊት መስመር ላይ የመጨረሻ አጥቂ ሆነው መጫወት ይችላሉ። ነገር ግን ዛሬ ውጥረት ነበረው እና የምንጫወትበት መንገድ ይህ ነበር ከማለት በላይ ማሸነፉ አስፈላጊ ነበር ለእኛ።

ስለፍሬው ጌታሀን ብቃት

ብሔራዊ ቡድን ላይ ወደቦታው መመለስ አለበት ብዬ አስባለሁ። ከዚህ በፊት ተመርጦ ነበር አሁን ምርጫ ውስጥ የለም እና አሁን ባለው አቋም ተመልሶ የመጀመሪያ ተመራጭ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። በሥነ ልቦናም እያዘጋጀነው ነው ፤ ጥሩ ብቃት ላይ ነው ያለው።

አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና

ከአሸናፊነት መንገድ ስለመውጣታቸው

አንወጣም። ምክንያቱም ከዚህ በኋላ ብዙ ጨዋታዎች አሉ። በቀሪ ስድስት ጨዋታዎች ላይ ጠንክረን ሰርታን ከመውረድ ስጋት እንወጣለን ብዬ አስባለሁ። ዛሬ ተጫዋቾቼ የምንፈልገውን ማድረግ አልቻሉም። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ዝግጁ አልነበሩም። እኔ አልገባኝም ፤ ለራሴም ሚስጥር ነው የሆነብኝ። ተጋጣሚ እንደልቡ እንዲጫወት መፍቀድ ፣ ተነሳሽነቱም ወርዷል ለምን እንደሆነ አልገባኝም። በሁለተኛው አጋማሽ በተሻለ ሁኔታ ቀርበናል ነገር ግን ብዙ ነገሮች ምቹ አልነበሩም። ውሳኔዎቹ ፣ የነበረው የኃይል አጨዋወት ፣ ብዙ ነገሮች ምቹ አልነበሩም። ከዚህ አንፃር ተሸንፈን ወጥተናል። ግን ለሚቀጥለው ስድስት ጨዋታ ጊዜ አለን ። ጠንክረን ሰርተን ነፃ እንሆናለን ብዬ አስባለሁ።

ኃይል የቀላቀሉ አጨዋወቶች ስለመታየታቸው

አዎ ግን አላስፈላጊ ጥቅም የመፈለግ ነገር ነበር። በተለያየ ምክንያቶች ማለት ነው ፤ በጩኸት ፣ በሰብሰብ ይህ ለእግር ኳሱ አይጠቅምም። እኔ መናገር ብፈልግ ብዙ ነገር እናገራለሁ ግን ጥቅም አይኖረውም። አሁን ስለቡድናችን ብቻ ማሰብ ስለሚኖርብን የነበሩትን ሁኔታዎች ተቀብለን ወጥተናል።

ስለዳኝነቱ

ፍፁም ቅጣት ምቱን ምንም ማድረግ አይቻልም። አንዳንዴ እጅ ወደ ኳስ ፣ ኳስ ወደ እጅ የሚሉት ነገር አላቸው። ይህ እንደዳኛው እይታ ነው። ግን አጠቃላይ ከዛ በላይ ብዙ ውሳኔዎች ነበሩ። እና እነሱ ነገሮች ናቸው ልዩነት የፈጠሩት ፤ ሊያጋጥም ይችላል። በአጠቃላይ ሲታይ ግን በመጀመሪያው አጋማሽ የሰራነው ስህተት ዋጋ አስከፍሎናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ