ቅዱስ ጊዮርጊስ አራት ተጫዋቾቹን አገደ

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ድሬዳዋ ላይ ውድድሩን እያከናወነ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ አራት ተጫዋቾቹን ማገዱን አስታውቋል።

የታገዱት ተጫዋቾች ጌታነህ ከበደ፣ አስቻለው ታመነ፣ ጋዲሳ መብራቴ እና ሙሉዓለም መስፍን ሲሆኑ የዲሲፕሊን ግድፈት የእርምጃው ምክንያት መሆኑና ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ መደረጉን ክለቡ ገልጿል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ የውሳኔ መግለጫ ይህንን ይመስላል:-

” የቅዱስ ጊዮርስ ስፖርት ማህበር በ2013 ዓ.ም በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እየተሳተፈ የሚገኘው ቡድናችን ውጤታማ እንዲሆን የስራ አመራር ቦርዱ ባለው አቅም ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ቡድኑ እየተደረገለት ካለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አንጻር የሚጠበቅበትን ያህል አርኪ የሚባል እንቅስቃሴዎችን እያደረገ አለመሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ባለንበት ጊዜ ደግሞ አልፎ አልፎ በቡድኑ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ተጫዋቾቻችን የሚያሳዩት ያልተገባ ባህሪና የስነ-ምግባር ጉድለት እጅጉን የሚያስቆጭ ነው፡፡ ትናንት ቡድናችን በድሬዳዋ ስታዲየም ከጅማ አባጅፋር ጋር ካካሄደው የ20ኛ ሳምንት ጨዋታ በኃላ ጌታነህ ከበደ፣ አስቻለው ታመነ፣ ጋዲሳ መብራቴ እና ሙሉዓለም መስፍን ከፍተኛ የዲሲፒሊን ግድፈት ፈጽመዋል፡፡ አብዛኞቹ ተጫዋቾች ከዚህ ቀደም ቡድኑ በባህርዳር በነበረው ቆይታም የስነ ምግባር ጉድለት ፈጽመው የነበረ ቢሆንም አጠቃላይ ለቡድኑ ውጤታማነትና አንድነት ሲባል በማስጠንቀቂያ እንዲታለፉ ተደርጎ ነበር፡፡ የክለቡ ስራ አመራር ቦርድ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ተጫዋቾቹ በፈጸሟቸው የዲስፕሊን ግድፈቶች ዙሪያ የቡድን መሪው በተፈጸመው የሥነ ምግባር ጉድለት ዙሪያ በዝርዝር በሚያቀርቡት ሪፖርት ላይ ቦርዱ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ ለጊዜው ከቡድኑ ታግደው እንዲቆዩ ተወስኗል፡፡ ስለሆነም አራቱም ተጫዋቾች ከድሬዳዋ በዛሬው እለት ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ ”

ክለቡ ከዚህ ቀደም ሳላዲን ሰዒድን አግዶ እንደነበር የሚታወስ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ