” ጨዋታ ለማረፍ ብዬ ካርድ አልመለከትም ” ዳንኤል ደምሴ

በኃይል አጨዋወቱ የሚታወቀው የተከላካይ አማካዩ ዳንኤል ደምሴ ከዚህ ጋር በተያያዘ ስለሚቀርብበት ስሞታ፣ ስለ አጨዋወቱ፣ ተጫዋቾች እና ዳኞች ለእርሱ ባላቸው አመለካከት ዙርያ ይናገራል።

በኢትዮጵያ መድን፣ ወልዲያ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ መቐለ ሰባ እንድርታ ከተጫወተባቸው ክለቦች መካከል ከሚጠቀሱት ናቸው። ሜዳ ላይ ለአንድ ቡድን መስጠት የሚገባውን ነገር ሁሉ ሳይሰስት በመስጠት ይታወቃል። ብዙም ጊዜ ሜዳ ላይ ባለው ችሎታ ሳይሆን በየጨዋታዎች የሚያሳያቸው የኃይል አጨዋወቶች እና ይህን ተከትሎ በዳኞች የሚወሰድበት እርምጃ ከጨዋታ ውጭ የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች በርከት ያሉ ናቸው። በተደጋጋሚ የማስጠንቀቂያ ካርድ የሚመለከተው ተጫዋቹ ከችሎታው በላይ ስሙ ሲጠራ ቀድሞ የሚመጣው የኃይል አጨዋወቱ ሆኗል። እኛም የዳንኤል የካርድ ቁርኝቱ እና ከተጫዋቾች የሚቀርብለትን ተማፅኖኦ አስመልክቶ የተለያዮ ጥያቄዎችን አቅርብንለት ተከታዩን ምላሽ በግልፅነት ሰጥቶናል።

በድሬዳዋ ዘንድሮ ያለህ ቆይታ ለአንተ እንዴት ነው ?

የድሬዳዋ ቆይታዬ በከፊል ጥሩ ነው። ይህ ማለት አጀማመራችንን እንዳያችሁት ቡድናችን ጎል ላይ በመድረስ የተሻለ ነበር። ሆኖም ግን በብዙ ችግር ውስጥ ነው የመጣነው። ገና ውድድሩን እንደጀመርን በተጫዋች አመራረጥ ችግር ነበረብን፤ ፉክክር የሌለበት ቡድን ነበር። አንድ ቦታ ተጫዋች ይበዛል። አንድ ቦታ ደግሞ ሰው የለም ነበር። ብቻ በከፊል ጥሩ ነበር። አሁን ያለንበት ሁኔታ ደግሞ ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻልን ጥሩ ደረጃ ላይ እንገኛለን።

እስካሁን በተጫወትክባቸው ክለቦች በተለይ ቀይ ካርድ ያየህባቸውን ብዛት ታውቃቸዋለህ ?

(እየሳቀ…) አዎ አውቃቸዋለው። ወልዲያ እያለሁ ሁለት፣ ድሬዳዋ አንድ፣ መቐለ አንድ፣ ቡናም አንድ ተመዞብኛል። ቢጫዎቹ ብዙ ስለሆኑ አልቆጠርኳቸውም።

ብዙ ጊዜ ለማስጠንቀቂያ ካርድ ተጋላጭ ከሆኑ ተጫዋቾች መካከል ግንባር ቀደም ተጫዋች ነህ። ይህ የሆነው የአጨዋወት ምርጫህ ነው? ወይስ ከአሰልጣኝ የሚሰጥ ትዕዝዛ ነው ?

እኔ አሁን ጉራ አይደለም እንጂ ኳስ ልጫወት ካልኩ እንደኔ ኳስን በሚገባ የሚጫወት የለም። ኳስ በደንብ መጫወት የምችል ነኝ። የካርዱ ነገር ከየት እንደመጣ ባላውቅም እኔ መሸነፍን አልወድም። ብዙ ጊዜ ካያችሁ ቡድናችን ሲበለጥ ዋጋ የምከፍለው እንጂ ካርድ ለማየት አስቤ አልገባም። መጫወት በጣም ነው የምፈልገው፤ ከዚህም የተነሳ መርፌ ሁሉ ተወግቼ ወደ ሜዳ የምገባበት አጋጣሚ አለ። አንዳውም ተጫዋች ቀይ ካርድ የሚያየው ሦስት አልያም አንድ ጨዋታ ለማረፍ ነው። እኔ ግን ይሄን አልፈልግም። ቀይ ተመልክቼ በነጋታው ከጓደኞቼ ጋር ልምምዴን በአግባቡ ነው የምሰራው። በቀጣይ ጨዋታ ጥሩ ሆኜ ለመመለስ። እና ካርድ የማይበት ምንም ተዓምር የለውም። እጅ ላለመስጠት እና መሸነፍ ስለማልፈልግ በሚፈጠሩ ሁኔታዎች የማገኘው ነው።

አሰልጣኝ የተቃራኒ ቡድን ተጫዋችን ለይቶ እንቅስቃሴውን ለመቆጣጠር የጉልበት አጨዋወት ተጠቀም ብለው አዘውህ ያውቃሉ ?

አልዋሽም የሚሰጠኝም ታክቲክም ጭምር አለው። አሁን እሩቅ አትሂድ ትናንትና ቢጫ ያየሁበት መንገድ የተሰጠኝን ታክቲክ ለመተግበር ስሞክር ነው። ቢጫ ካየሁ በኃላ አጨዋወቴን ሊያቀዘቅዝብኝ ይችላል እንጂ ታክቲክ አለው። አሁን ከቡና ጋር ስንጫወት ሚኪያስ መኮንን በጣም ሲያስቸግረን የመታሁበት አጋጣሚ ግልፅ ነው። አሁን ሚኪ በጣም ወንድሜ ጓደኛዬ ነው። ግን ተፅዕኖ ይፈጥር የነበረው እርሱ ነው። እርሱ ተጎድቶ ከወጣ በኃላ እኛ በጣም ቀሎን ነበር። ይህ አንድ ታክቲክ ነው። አሰልጣኝ አድርግ የሚልህን ታደርጋለህ።

ዳንኤል ሜዳ ውስጥ ካርድ ካላየ ደስ አይለውም የሚባለውስ?

(እየሳቀ…) ኧረ እንደዚህ አይደለም። እውነት አይደለም። ያው ላለመሸነፍ በማደርገው ጥረት እና ቡድናችን ሲበለጥ ማየት ስለማልፈልግ የሚፈጠር እንጂ ካርድ ካለየሁ ደስ አይለኝም ብዬ የማደርገው ነገር የለም።

ጥሩ የእግርኳስ የመረዳት አቅም አለህ። ምን አልባት ይህ በእግርኳስ ዕድገትህ ላይ ተፅዕኖ አድርጎብሀል ?

አይ እግዚአብሔር ይመስገን እስካሁን ተፅዕኖ አላደረገብኝም። ግን ሜዳ ውስጥ የጨዋታ ሚናዬን ይቀንሰዋል። በጊዜ ቢጫ ካየሁ የኔ አጨዋወት ይታወቃል ኃይል ቀላቅዬ ስለምጫወት ይህን ሊያቀዘቅዝብኝ፤ ያለኝን ነገር ለቡድኔ እንዳልሰጥ ሊያደርገኝ ይችላል። አንዳንዴ ተጫዋቾችም የኔ አጨዋወት ስለሚታወቅ ሆን ብሎ እኔ ካርድ እንዳይ የሚያደርጉት ነገር አላቸው። በአጠቃላይ ከካርድ ውጭ እኔ ላይ ምንም ተፅዕኖ አላመጣም።

ከአሰልጣኞችስ የተማረሩብህ የሉም ?

አይ የለም። እንዲያውም ያኔ አሰልጣኝ አሥራት ኃይሌ ጋር እየሰራሁ አሰልጣኝ አሥራት ተደብቆ ተጫዋች እየጠቆመ እጁን አንገቱ ጋር አድርጎ “ግደል” ይለኛል። ዳንኤል “ግደል” ይለኛል። ትዝ ይለኛል በዛ ዓመት ሦስት ቀይ ካርድ አይቼ ወጥቼ “የኔ ልጅ ዳንኤል” ይል ነበር። አንዳንዴ ከዛ የመጣ ነው የሚመስለኝ።

ተጫዋቾች ሜዳ ሲገቡ እንዳትመታቸው የሚለምኑህ አሉ ይባላል። እስኪ የማትረሳው ገጠመኝ ካለ ንገረኝ ?

በጣም ብዙ ናቸው የሚለምኑኝ። ከምልህ በላይ በጣም የማረሳው መድን ሆኜ ሳሙኤል ሳኑሚ በአማርኛ አልቀረው በእንግሊዘኛ እየተከተለ እባክህ እንዳትመታኝ አትንካኝ እያለ በተደጋጋሚ የጠየቀኝን መቼም አልረሳውም። እና አሁን ደግሞ በቅርቡ ከቡና ጋር ስንጫወት አቡበከር ናስር ያው ጥሩ ጊዜ ላይ ስለሆነ ዳንኤል እባክህ እንዳትነካኝ ብሎኛል።

ዳኞችስ ሜዳ ውስጥ ምን ይሉሀል ? የምትፈራውስ ዳኛ ማን ነው?

አንዳንዱ ዳኛ ምንም ሳላደርግ አስቀድሞ በሰማው ነገር እርሱ እንዲህ ነው ብሎ በመገመት ምንም ሳላደርግ ካርድ የሚሰጠኝ አለ። ያው ብዙዎቹ ግን ይመክሩኛል። ኧረ ዳንኤል ሥራችንን እንስራበት የሚሉኝ አሉ። አንዳንዶቹም ገና ወደ ሜዳ እንደገባን “ኳስ እየቻልክ ዝም ብለህ አትጫወትም” ብለው የሚመክሩኝ አሉ።

ከዳኞች የምፈራው ለሚ ንጉሤ ነው። ምንም አይምረኝም፤ አይደራደረኝም። በጣም ነው የምፈራው። አይደለም ሜዳ ውስጥ መልበሻ ክፍል ራሱ ካርድ ቢሰጠኝ ደስታው ነው።

ብዙ ጊዜ ተጫዋች እንደምትጎዳ ይነገራል። አንተን ሆን ብሎ ሜዳ ውስጥ ሊጎዳህ ያሰበ ተጫዋችስ አለ ?

በሚገባ የኔ ደርቢ ተስፋዬ አለባቸው ነዋ። በቃ እርሱ እኔን ለመጉዳት ሆን ብሎ እንደሚመጣ ስለማውቅ እኔም ደንብ ተዘጋጅቼ እጠብቀዋለሁ። በቀጣይ ሳምንት የምንገናኝ ስለሆነ የምታዩት ይሆናል።

የመጨረሻ ጥያቄ የድሬዳዋ ቀጣይ ጉዞ ምን ይሆናል ብለህ ታስባለህ ?

አሁን እየሠራን የምንገኘው በጣም በከፍተኛ ተነሳሽነት ነው። ያው ከሆሳዕና ጋር የምናደርገው ጨዋታ በጣም ወሳኝ ነው። የመቆየት ያለመቆየት ዕድላችንን የምንወስንበት ነው። በዚህ ጨዋታ ነጥብ ይዘን ወደ ሀዋሳ የምንሄድ ከሆነ በእርግጠኝነት በሊጉ እንቆያለን።

© ሶከር ኢትዮጵያ