ቅድመ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ ሀዋሳ ከተማ

በነገ ምሽቱ ጨዋታ ዙሪያ የሚያተኩረው ዳሰሳችን ይህንን ይመስላል።

በነገው ዕለት የሚከናወነው የሮድዋ ደርቢ ጠንከር ያለ ፉክክርን እንደሚያስተናግድ ይጠበቃል። ድሬዳዋ ላይ ሁለት ድል እና ሁለት ሽንፈትን ያስመዘገቡት ሲዳማዎች ዛሬ አንድ ነጥብ ያገኘው ተፎካካሪያቸው ድሬዳዋ ከተማን ለመጠጋት ነገ አሸንፈው መውጣት የግድ ይላቸዋል። ባለፉት አራት ጨዋታዎች ከ12 ነጥቦች አስሩን ማሳካት የቻለው ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ ከሰንጠረዡ አጋማሽ ከፍ ብሎ ለመፎካከር ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ መሰብሰብ አስፈላጊው ነው።

በታችኛው ፉክክር ውስጥ እንደሚገኙት ሌሎቹ ቡድኖች ሁሉ ድሬዳዋ ላይ መሻሻል የታየበት ሲዳማ ቡና ለውጡን በተቻለ ፍጥነት በውጤት ማጀብ ከምንም በላይ አስፈላጊው ነው። ከዚህ አንፃር ከመጀመሪያው ዙር በተለየ አስፈሪ ሆኖ የተገነባው የፊት መስመሩ ከአዳማው ጨዋታ በኋላ በሚፈለገው መጠን ግቦችን እያስቆጠረ አለመሆኑ ከነገው ጨዋታ በፊት መሻሻል የሚገባው የቡድኑ ደካማ ጎን ሆኗል። ጥሩ የመከላከል አደረጃጀት ካለው ቡድን ጋር እንደመግጠሙም በርካታ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢቸገር እንኳን ከጥቁት አጋጣሚዎች ውጤት ቀያሪ ግቦች ከአጥቂዎቹ ይፈለጋሉ። ከዚህ ጎን ለጎን በድሬዳዋው ጨዋታ አማካይ ክፍል ላይ ተወስዶበት የነበረው ብልጫም ነገ እንዳይደገም ማድረግ የማጥቃት ሂደቱ ላይ ከሚፈጥረው ልዩነት አንፃር ሌላኛው የቡድኑ የጨዋታ ዕቅድ ዋነኛ ትኩረት መሆን ይገባዋል።

ሀዋሳ ከተማ ወጣ ገባ ከሆነው የውድድር ዓመቱ አንፃር አሁን ላይ በሚፈልገው መልካም አቋም ላይ ይገኛል። ይህ አቋም ከቅርብ ተቀናቃኙ ጋር ከመገናኘቱ አስቀድሞ የመጣ እና በተደላደለ ደረጃ ላይ ሆኖ የተገኘ ከመሆኑ አንፃርም ነገ ያለ ጫና ጨዋታውን የመከወን ዕድል ይሰጠዋል። በሰሞኑ ጨዋታዎች አጥቷቸው የነበሩት እንደቡድን በትጋት የመከላከል እንዲሁም ጠንካራ የመስመር ጥቃቶችን የመሰንዘር ብርታቱ ተመልሰው መምጣት ሲዳማን ለመፈተን የሚያግዘውም ይመስላል። በተለይም ቡድኑ ቀድሞ ግብ ማስቆጠር ከቻለ ራሱን በአግባቡ ከጥቃት ተከታትሎ በመልሶ ማጥቃት ክፍተቶችን ለመጠቀም ሁኔታዎች ምች ሊሆኑለት ይችላሉ። በአንዳንድ የጨዋታ ቅፅበቶች ላይ የሚታይበት የትኩረት መውረድ ግን እንደ ነገ ባለ ውጤቱን አጥብቆ በሚሻ ተጋጣሚ እንዲቀጣ ምክንያት ሊሆነው ይችላል። በመሆኑም አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ቡድናቸው በተለይም በሽግግሮች ወቅት ባልተዛነፈ ትኩረት ውስጥ ጨዋታውን እንዲከውን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

የእርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን 21 ጊዜ ተገናኝዋል። ሲዳማ ቡና 7 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ሀዋሳ 6 ጊዜ አሸንፏል። በቀሪዎቹ ስምንት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

– በአጠቃላይ 20 ግንኙነቶቻቸው 42 ጎሎች ሲቆጠሩ ሲዳማ 23 ፣ ሀዋሳ 21 ጎሎች አስቆጥረዋል።

* ወቅታዊው የኮቪድ ወረርሺኝ በቡድኖቹ የስብስብ ምርጫ ላይ እያሳደረ ካለው ተለዋዋጭነት አንፃር ግምታዊ አሰላለፍ ለማውጣት አዳጋች በመሆኑ የወትሮው የአሰላለፍ ትንበያችን በዳሰሳው ያልተካተተ መሆኑን እንገልፃለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ