የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 1-1 አዳማ ከተማ

በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች በሱፐር ስፖርት ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

ምክትል አሰልጣኝ አብዱልሀኑ ተሰማ – ወልቁጤ ከተማ

ጨዋታውን ስለጀመሩበት መንገድ

ኳሱን ተቆጣጥረን ነበር መጫወት የፈለግነው። በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ነበር። የምንፈልገውን ነገር ነበር ተጫዋቼች ሲያደርጉ የነበረው። በአጋማሹ ያደረጉት እንቅስቃሴ ደስ የሚያሰኝ ነበር። በምንፈልገው መንገድ ነበር ስንጫወት የነበረው።

ስለአብዱልከሪም ወርቁ ጫና ውስጥ መግባት

ጨዋታው ከመጀማሩ በፊት እሱ ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን መሰረት አድርገን ነበር የገባነው። በፍሬው እና በረመዳን በኩል ነበር ማጥቃት የፈለግነው። እንደጠበቅነውም አብዱልከሪም ላይ ጫና በዝቶበታል። እኛም ያንን ታሳቢ አድርገን ወደ መስመር አውጥተን ነበር ለመጫወት የሞከርነው።

ስለውጤቱ ተገቢነት

በጨዋታው አሸናፊ መሆን ይገባን ነበር። ሦስት ነጥብ ይገባን ነበር እንደጨዋታችን። ጨዋታውን ተቆጣጥረን ጎልም ላይ ደርሰናል። በመጨረሻ በተቆጥሮብን ጎል አቻ ልንሆን ችለናል ፤ በፀጋ እንቀባለልን።

አሰልጣኝ ዘርዓይ መሉ – አዳማ ከተማ

ስለጨዋታው

ጎላችንን ጠብቀን ለመጫወት አስበን ነበር። ዕረፍት ልንወጣ አንድ ደቂቃ ሲቀር የማይሆን ስህተት ሰራን እና ጎል ተቆጠረብን። ትንሽ እሱ ዋጋ አስከፈለን። ከዕረፍት በኋላ ግን ተጭነን ነው የተጫወትነው። ስድስት ሰባት አጥቂዎችን ነው የተጠቀምነው። በተለይ 15 ደቂቃ ሲቀር አማካዮችን አውጥተን አጥቂዎችን ነው ስንጨምር የነበረው። እና ዞሮ ዞሮ መጨረሻ ላይ አግብተን አቻ ወጥተናል። ከዕረፍት በኋላ ግን የተሻልን ነበርን። ጎሎች አግብተን መጨረስ እንችል ነበር ብዬ አስባለሁ። አልተጠቅምንም እንጂ የተሻሉ ኳሶችን አግኝተናል። ከዕረፍት በፊትም ፣ ከዕረፍት በኋላም።

ስለበላይ አባይነህ ቅያሪ እና ስለማስቆጠሩ

መጀመሪያም አስነስተነው ነበር ፤ አጥቂ ለመጨመር። በዝግጅት ላይ እያለን ቅጣት ምት አገኘን ፤ ወዲያው ነው ያስገባነው። ምክንያቱም ቅጣት ምት መቺ ስለሆነ ያንን ይጠቀማል የሚል ነገር ነበረን። ልምምድ ላይም ይመታል። የተሻለ በመሆኑም ያንን ዕድል ተጠቅሞበታል።

ስለውጤቱ ተገቢነት

ያው ማሸነፍ ነበር ዋናው አላማችን። ዞሮ ዞሮ ከመሸነፍ ይሻላል። ከዕረፍት በኋላ የነበረውን ነገር ከመጀመሪያው ብናደርግ ኖሮ ዛሬ ሦስት ነጥብ ይዘን ማውጣት እንችል ነበር። ተጫዋቾቼ ከዕረፍት በኋላ ባደርጉት ተጋትሎ ግን በጣም ደስተኛ ነኝ።

© ሶከር ኢትዮጵያ