የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ከውዳሴ ዳያግኖስቲክ ማዕከል ጋር የስምምነት ውል ተፈራረመ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን እና ውዳሴ ዳያግኖስቲክ ማዕከል ለ2 ዓመታት አብሮ ለመስራት የሚያስችላቸውን ውል በዛሬው ዕለት በፌደሬሽኑ ፅ/ቤት በተደረገ ጋዜጣዊ መግለጫ ተፈራርመዋል።

በፊርማ ስነ ስርዓቱ ወቅት የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ በስምምነቱ የተሰማቸውን ደስታ በመግለፅ በፌደሬሽኑ ስር የሚተዳደሩት ቡድኖች ማለትም የወንድ እና ሴት ዋና ፣ ከ20 ዓመት በታች ፣ ከ17 ዓመት በታች እና የኦሊምፒክ ቡድን የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ያስታወቁ ሲሆን የፌደሬሽኑ ሠራተኞችም ምርመራ በሚያስፈልጋቸው ወቅት በውዳሴ በኩል አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ ተገልጿል። ፌደሬሽኑ በበኩል በብሔራዊ ቡድኖች ትጥቅ እና አልባሳት ላይ ውዳሴ ዳያግኖስቲክ ማዕከልን የሚያስተዋውቅ ይሆናል።

የውሉን ይዘት በማስመልከት ማብራርያ የሰጡት አዲሱ የፌዴሬሽኑ የህክምና ክፍል አመራር ዶ/ር ሳሙኤል የሺዋስ በበኩላቸው የተደረገው ስምምነት ፌደሬሽኑን በዓመት እስከ 5.5 ሚሊዮን ብር ወጪ ከማድረግ እንደሚጠብቀው ተናግረዋል። በቅርቡም ተመሳሳይ ዓይነት ከህክምና አጋርነት ጋር የተያያዙ ስምምነቶችን ለመፈራረም ፌደሬሽኑ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የውዳሴ ዳያግኖስቲክ ማዕከል ባለቤት እና ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዳዊት ኃይሉ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ጋር አንድ ላይ ለመሥራት ዕድሉን በማግኘታቸው ኩራት እና ክብር እንደተሰማቸው የተናገሩ ሲሆን በቅርቡም ዋልያዎቹ ወደ አፍሪካ ዋንጫ በማለፋቸው እንኳን ደስ አለን መልዕክትን አያይዘው አስተላልፈዋል። ምርመራ በህመም ወቅትም ብቻ ሳይሆን ጤና በተሰማን ወቅት መደረግ እንዳለበት እና ድርጅታቸውም ይህን አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል ።

© ሶከር ኢትዮጵያ