ሪፖርት | ጠንካራ ፉክክር የታየበት ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሃያኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ፋሲል ከነማን ከሀዲያ ሆሳዕና አገናኝቶ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ፋሲል ከነማ ሲዳማን ካሸነፈበት ጨዋታ ሁለት ለውጦች በማድረግ በረከት ደስታ እና ይሁን እንዳሻውን በናትናኤል ገብረጊዮርጊስ እና ሰራፌል ዳኛቸው ምትክ ሲያሰልፍ ሆሳዕናዎች በበኩላቸው በወልቂጤ ከተማ ላይ ድል ካስመዘገበው ስብስብ የአንድ ተጫዋች ለውጥ በማድረግ ካሉሻ አልሀሰንን በአዲስ ህንፃ ምትክ አሰልፈዋል።

ከጅምሩ እስከ ፍፃሜው ፋታ ያልነበረውና በሙከራዎች የታጀበው ጨዋታ ጎል ለማስተናገድ ተቃርቦ የነበረው ገና ከጅምሩ ነበር። በሦስተኛው ደቂቃ ሙጂብ ቃሲም ከሽመክት የደረሰውን ኳስ መትቶ ከጎሉ ለቆ የወጣው ሙንታሪ በእግሮቹ መልሶበታል።

ከሙከራው በኋላ ባሉት ቀጣይ ሃያ ደቂቃዎች ሀዲያ ሆሳዕናዎች ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን ከቆሙ ኳሶች አስደንጋጭ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። በተለይም በ11ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት ሄኖክ ያሻማውን ኳስ ዳዋ ሆትሳ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጪ የወጤበት እንዲሁም ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በድጋሚ ከሄኖክ የተሻማውን የማዕዘን ምት ካሉሻ አልሀሰን ገጭቶ የጎሊ አግዳሚ የመለሰበት የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ።

በቀጥተኛ ጥቃት እና በቆሙ ኳሶች የጎል ዕድል መፍጠራቸውን የቀጠሉት ሆሳዕናዎች በሃያኛው ደቂቃ መሪ የሆኑበትን ጎል አስቆጥረዋል። በግራ መስመር በኩል የተሰጠውን የቅጣት ምት ሄኖክ አርፊጮ አሻምቶ ተከላካዩ ፀጋሰው ድማሙ የግንባሩ ገጭቶ ተከታታይ ጎሉን ማስቆጠር ችሏል።

ከውሀ እረፍት በኋላ ወደ ጨዋታው መመለስ የቻሉት ዐፄዎቹ ኳስ በመቆጣጠር ከመሐል ሜዳ በሚነሱ ኳሶች ጥቃት ለመሰንዘር ጥረት አድረገዋል። በመጨረሻዎቹ የአጋማሹ ደቂቃዎችም በሁለት ሙከራዎች የሆሳዕናን ግብ ፈትሸዋል። በ41ኛው ደቂቃ ከመሐል ሜዳ ከይሁን እንደሻው የተላከውን ኳስ ሙጂብ ወደ ጎሉ ዞሮ ራሱን በማመቻቸት መትቶ ሙንታሪ ሲያወጣበት ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በረከት ያሻማውን ቅጣት ምት በዛብህ መለዮ በግንባሩ ጨርፎ አግዳሚውን ጨርፎ ወጥቶበታል።

በመጀመርያ አጋማሽ ከነበረው ግለት በቀጠለው ሁለተኛው አጋማሽ ፋሲሎች ጎል ለማግኘት ጥረታቸውን የጀመሩት በቶሎ ነበር። ይህም ተሳክቶላቸው በ48ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ በዛብህ መለዮ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ዐፄዎቹን አቻ አድርጓል።

የአቻነት ጎሉ ከተቆጠረ በኋላ በቀሩት የመጀመርያ አጋማሽ ደቂቃዎች አንድ ጊዜ ነብሮቹ ሌላ ጊዜ ዐፄዎቹ ብልጫ መውሰድ ቢችሉም እንደመጀመርያው አጋማሽ በሙከራዎች የታጀበ መሆን አልቻለም። 67ኛው ደቂቃ ላይ ለመሐል ሜዳ ከተጠጋ ቦታ የተሰጠውን ቅጣት ምት ዳዋ ሆቴሳ አክሮ መትቶ ሳማኬ የመለሰው በሀዲያ በኩል የሚጠቀስ ሙከራ ነበር።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የማሸነፍያ ጎል ፍለጋ ጫና የፈጠሩት ፋሲሎች በመጠናቀቂያው ደቂቃ ላይ ጠንካራ ኳስ በሙጂብ አማካኝነት ሞክረው በተከላካዮች ተደርቦ ሲወጣ ጭማሪው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሙጂብ ከሳጥኑ ጠርዝ ያገኘውን ኳስ በቀጥታ ወደ ጎል ልኮት አግዳሚው የገጨበት ፋሲልን ወደ ድል ልትመራ በእጅጉ የተቃረበች ብትሆንም ወደ ጎልነት ሳይቀየር ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ