የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር የምድብ ድልድል ወጥቷል

የ2013 የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር የምድብ ድልድል ዛሬ ሲወጣ የሚረግበት ከተማም ወደ አንድ ተሸጋሽጓል።

በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል በተከናወነው የምድብ ድልድል እና የውድድር አካሄድ ውይይት ላይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ፣ የውድድር እና ስነሥርዓት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ከበደ ወርቁ፣ የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ ልዑሰገድ በጋሻው እንዲሁም የአንደኛ ሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ብዙዓየሁ ጌታቸው የተገኙ ሲሆን ፕሬዝዳንቱ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር መልዕክታቸውን በዚህ መልኩ አስተላልፈዋል።

” በመጀመርያ እንኳን ደስ አላችሁ፤ ለማጠቃለያ ውድድር በመብቃታችሁ እና ብሔራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፉ። የብሔራዊ ቡድኑ ስኬት የአሰልጣኝ እና ፌዴሬሽን ሥራ ብቻ ሳይሆን የሁሉም የጋራ ስለሆነ እንኳን ደስ አለን። ከኮቪድ ጋር በተያያዘ ድሬዳዋ ላይ በፕሪምየር ሊጉ ውድድር እየሆነ ያለውን እያያችሁ ስለሆነ እናንተም መጠንቀቅ አለባችሁ። ውድድሩ በሰላም እንዲያልቅም ቀናነት እና የሁላችሁም ተሳትፎ ይጠበቃል። ከምርጫው አስር ቀን በፊት ስለምናጠናቅቅ የእናንተ ትብብር አስፈላጊ ነው። በዙር ውድድሩ ላይ ምንም አይነት ቅሬታ ወደ ፌዴሬሽን አልመጣም። አንድዳንድ ቅሬታዎችም ወደከፋ ደረጃ ሳይደርስ እዛው ያለቁ ናቸው። ለዚህ መመስገን አለባቸው። የጤና ሴክተሩም በአግባቡ ኃላፊነቱን ስለተወጡ ሊመሰገኑ ይገባል። በአጠቃላይ በሥራ ጫና ምክንያት የዙር ውድድሩን ማየት አልቻልኩም። ይህን ግን በቦታው ተገኝቼ ለማየት እሞክራለሁ። መልካም እድል! ”

በመቀጠል አቶ ብዙዓየሁ ጌታቸው (የአንደኛ ሊግ ሰብሳቢ) በውድድሩ ደንብ ዙርያ ማብራርያ የሰጡ ሲሆን አጠቃላይ የውድድር ደንቡ እና የኮቪድ ፕሮቶኮሉ በቀደመው የሚቀጥል ሆኖ አንዳንድ ደንቦች ላይ ማሻሻያ መደረጉን ገልፀዋል። በዚህም
በዙር ውድድር እስከ እስከ አራት ቢጫ ድረስ ያላቸው ተጫዋቾች በማጠቃለያ ውድድሩ ካርዱ ይነሳላቸዋል። ቀይ ካርድ የተመለከቱ እና የጨዋታ ቅጣት የተላለፈባቸው ተጫዋቾች ግን የተቀጡት ጨዋታ በማጠቃለያውም ተፈፃሚ ይሆናል። በሦስት ቢጫ የተመለከተ ተጫዋች አንድ ጨዋታ እና 1000 ብር የሚቀጣ ይሆናል። (በዙር ውድድር 1500 ብር እና አንድ ጨዋታ ቅጣት ነበር)

በመቀጠል ከተሰብሳቢዎች ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን በቅድሚያ የተገለፀው የውድድር ቦታ (አዳማ እና አሰላ) ወደ አንድ እንዲደረግ አመዛኞቹ ጥያቄ አቅርበዋል። በተጨማሪም በኮቪድ ምርመራ፣ የውድድሩ ጊዜ ማራዘም እና በተለይ የአማራ ክልል ክለቦች ከፀጥታ ጋር ያላቸውን ስጋት የገለፁ ሲሆን ከፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት በተሰጠው ምላሽ የውድድሩ ቀን እንደማይገፋ፣ የአማራ ክልል ክለቦች በፖሊስ መኪና ታጅበው ወደ ውድድር ስፍራ እንዲመጡ ከኦሮሚያ እና ፌዴራል ፖሊስ ጋር መነጋገራቸውን እንዲሁም የውድድር ቦታን በተመለከተ ተነጋግረው መስማማት እንደሚቻል ገልጸዋል።

ከሻይ እረፍት በኋላ ውይይቱ ሲቀጥል ሁሉም ጨዋታዎች አዳማ ላይ እንዲከናወኑ የተወሰነ ሲሆን ከሚያዚያ 27 – ግንቦት 18 ድረስ በቀን አራት ጨዋታ እንደሚደረግ ተገልጿል። ከዚህ ቀደም ባለው አሰራር መሰረትም ግማሽ ፍፃሜ የሚቀላቀሉ አራት ክለቦች በቀጥታ እንዲሁም በሩብ ፍፃሜ የሚሸነፉ ክለቦች የመለያ ጨዋታ አድርገው ሁለቱ በድምሩ ስድስት ክለቦች ወደ ከፍተኛ ሊግ የሚያድጉ ይሆናል።

በመጨረሻም የምድብ ድልድል የእጣ ማውጣት የተከናወነ ሲሆን የአንድ ክልል እና በአንድ ምድብ የነበሩ ክለቦች በተቻለ መጠን በተመሳሳይ ምድብ እንዳይገናኙ ተደርጓል።

ምድብ ሀ

ሐረር ከተማ
አውሥኮድ
አምቦ ከተማ
ጉለሌ

ምድብ ለ

ሰንዳፋ በኬ
ደብረማርቅስ
ሞጆ ከተማ
ጎፋ ባሬንቼ

ምድብ ሐ

ኤጀሬ ከተማ
እንጅባራ ከተማ
ጎባ ከተማ
አዲስ ከተማ

ምድብ መ

ሾኔ ከተማ
ዳሞት ከተማ
ቡራዩ ከተማ
ድሬዳዋ ፖሊስ

የመጀመርያ የምድብ ጨዋታዎች

ሚያዚያ 27
03:00 ሰንዳፋ በኬ ከ ጎፋ ባሬንቼ
05:00 ጎጃም ደ/ማርቆስ ከ ሞጆ ከተማ
08:00 ሾኔ ከተማ ከ ድሬደዳዋ ፖሊስ
10:00 ዳሞት ከተማ ከ ቡራዩ ከተማ

ሚያዚያ 28
03:00 ሐረር ከተማ ከ ጉለሌ
05:00 አውሥኮድ ከ አምቦ ከተማ
08:00 ኤጀሬ ከተማ ከ አዲስ ከተማ
10:00 እንጅባራ ከተማ ከ ጎባ ከተማ

© ሶከር ኢትዮጵያ