የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 1-1 ሀዲያ ሆሳዕና

ሱፐር ስፖርት እና ተጋጣሚ አሰልጣኞች ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ

ስለ እረፍት ሰዓት ንግግራቸው

ገና ከሆቴል ስንመጣ በነበረን የቅድመ ጨዋታ ስብስብ እንደተነጋገርነው ከዚህ በፊት ሆሳዕናን ደጋግሜ እንዳየሁት አጨዋወታቸው በጣም ቀጥተኛ እግርኳስ ነው ፤ ሁለተኛ ደግሞ በቆሙ ኳሶች በጣም አደገኛ ናቸው።ስለዚህ ይህን እድል አለመፍጠር ዋናው ነገር በኳስ ቁጥጥር ሊበልጡን አይችሉም የኛ ልጆች የተሻሉ ናቸው ስለዚህ ያንን ተቆጣጥረን መሄድ ከቻል ውጤት ይዘን መውጣት እንደምንችል ተነጋግረን ነበር ፤ ሜዳ ላይ ግን ያጋጠመን ያ ነው ከቆመ ኳስ ግብ አስተናግደናል። ከግቧ መቆጠር በኃላ በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ 20 ደቂቃዎች ከፍ ያለ ጫና ፈጥረናል በሁለተኛው አጋማሽ ተጫዋቾቼ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የሻምፒዮናነት ጉጉት ስላለ ተረጋግተን በትዕግሥት ተንቀሳቅሰን ቶሎ ግብ አስቆጥረናል። በሂሳብ ስልት አሁን ካለን 46 ነጥብ ተጨማሪ የምንፈልገው ስድስት ነጥብ ነው ተከታዮቻችን ሙሉውን እንኳን ካሸነፉ እኛ የሚጠብቅብን ስድስት በመሆኑ ጥሩ ጉዞ ላይ ነን።

ሀዲያ አስቀድሞ ግብ ማስቆጠሩ በጨዋታ ዕቅዳቸው ላይ ስለፈጠረው ጫና

በሚገባ እነሱም ውጤቱ ያስፈልጋቸው ስለነበረ አስቀድመው ካስቆጠሩ ተነሳሽነታቸው እያደገ እንደሚሄድ ተነጋግረን ነበር ፤ ነገርግ ተጫዋቾቼ ከግቡ በኃላ የነበራቸው ምላሽ ግን ጥሩ የሚባል ነበር።

የተገኙ አጋጣሚዎችን ስላለመጠቀማቸው

የመጨረስ ችግር ብቻ ሳይሆን ሙጂብ ያው ያለው ልምዱ የሚታወቅ ነው ነገርግን በዚህ ሰአት ጉጉትም አለ ቢሆንም ግን ካገኘናቸው እድሎች አንዱን መጠቀም ነበረብን ፤ ነገርግን ከሚያስፈልገን 7 ነጥብ አንዱን ማሳካታችን ትልቁ ነገር ነው።

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና

ስለጨዋታው

ቀድሞ ማስቆጠር ለማሸነፍም ሰፊ ዕድል ይሰጥሀል። እንዳሰብነው ነበር ጨዋታው የሄደው። መጀመሪያ አምስት አስር ደቂቃቆ
ዎች መዘናጋቶች ነበሩ። እነሱ እንደውም የተሻለ የግብ አጋጣሚዎችን አግኝተው ነበር። ሁለተኛውም አጋማሽ ሲጀምርም መዘናጋቶች ነበሩ። እነዛ ነገሮች ዋጋ አስከፍለውናል። እንደ ቡድን ግን ፋሲል በጣም ጥሩ ቡድን ነው። እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለሁ ጥሩ ቡድን ስለሆነ።

ከፋሲካ በፊት ፋሱል እንዳያረጋግጥ አደርጋለሁ ብለው የነበረ ስለመሆኑ

ዋንጫዋን ፋሲል ወስዶታል ማለት ይቻላል። ፋሲል እንደሚታወቀው የ 44 ደብር ባለቤት ነው ። የፋሲልን ሀገር እንዲያደምቁት ነው የምፈልገው። ስለዚህ ቀጣይ ጨዋታቸውን አሸንፈው ደስታቸውን ያከብራሉ ብዬ ነው የማስበው።

በቅያሪዎቻቸው መከላከልን ስለመምረጣቸው

1-1 በፍፁም የማላስበው ውጤት ነው። አቻ አያዋጣንም ከምንፈልገው ክለቡም ከሚፈልገውም ስኬት አኳያ ማሸነፍ የውዴታ ግዴታ ነበር ። የብሩክ እና የአማኑኤል ሚና በጣም ይለያል። ተከላካይ አማካይ ሆነው አይደለም የተጫወቱት። መሀል ላይ በልጠውን ስለነበር ያንን ለመቆጣጠር ነው። ስሌቱ በትክክል ስርቶልናል ብለን እናስባለን እንጂ ለመከላከል አይደለም። አንድ ቡድን ኳስ ሲያጣ የግድ መከላከል አለበት። ይህ በየትኛውም ዓለም ያለ ነው። ኳስ ስናገኝ ደግሞ በከፍተኛ ፍጥነት ወጥተን መጫወት ነው ያሰብነው። በአጠቀላይ ባለን ተመስገን እንላለን።

© ሶከር ኢትዮጵያ