በወልቂጤ ከተማ መሪነት የዘለቀው ጨዋታ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ወልቂጤ ከተማ ከመጨረሻው የሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ ቶማስ ስምረቱ ፣ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ እና አሳሪ አልመሀዲን በመሀመድ ሻፊ ፣ ሀብታሙ ሸዋለም እና አሜ መሀመድ ቦታ ሲጠቀም አዳማ ከተማ በበኩሉ ጀሚል ያዕቆብ እና ማማዱ ኩሊባሊን በታፈሰ ሰርካ እና ያሬድ ብርሀኑ ለውጧል።
በጨዋታው ላይ የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ እንዳለ ገብረመስቀል የተገኙ ሲሆን የቡድኑ የመስመር ተከላካይ ረመዳን የሱፍ የወሩ የክለቡ ደጋፊዎች ኮከብ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠበትን ሽልማት ተረክቧል።
የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ በአመዛኙ ቀዝቃዛ ነበር። ከፍ ያለ የኳስ ቁጥጥርን ማሳካት የቻሉት ወልቂጤ ከተማዎች በተጋጣሚያቸው ላይ ብልጫን ይዘው ቢዘልቁም ሙከራዎችን ማድረግ ተቸግረው ቆይተዋል። የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች በአዳማ ሳጥን አቅራቢያ እየደረሱ የሚቋረጡባቸው ወቅቶች በርካታ ነበሩ። ለመልሶ ማጥቃት የቀረበ የጨዋታ ዕቅድ የነበራቸው አዳማ ከተማዎችም ተጋጣሚያቸው አደጋ እንዳይፈጠር አደረጉ እንጂ ሲያስጨንቁት አልታዩም። 29ኛው ደቂቃ ላይ ኤልያስ ማሞ ከሳጥን ውጪ ሞክሮት በግቡ አግዳሚ የተመለሰበት ኳስ የቡድኑ ብቸኛ የግብ ሙከራ ሆኗል።
የተለመደው የግራ መስመር ጥቃታቸው ዛሬም ጠንከር ብሎ የታየው ወልቂጤዎች በረመዳን የሱፍ አማካይነት ከበድ ያለ ጫና የፈጠሩት አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሲል ነበር። ተጫዋቹ ሁለት ጊዜ በሳጥን ውስጥ ተገኝቶ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክር የታየ ሲሆን በዚህ መነሻነት 45ኛው ደቂቃ ላይ ሰራተኞቹ የማዕዘን ምት አግኘተዋል። የማዕዘን ምቱ ተሻምቶ ከተጨረፈ በኋላ ያገኘው ረመዳን ከቀኝ የሳጥኑ ክፍል አክርሮ የመታው ኳስም ቡድኑን ከዕረፍት በፊት ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
ከዕረፍት በኋላም ጨዋታው በተመሳሳይ መንገድ የቀጠለ ነበር። ወልቂጤዎች በተሻለ ሁኔታ ቅብብሎችን ሲከውኑ ቢታዩም ፊት ላይ ተመሳሳይ ውጤት ነው ነበራቸው። ሳጥን ውስጥ በቁጥር እያነሱ መገኘታቸውም ከብልጫቸው ተፈላጊውን ውጤት እንዲያገኙ አላስቻላቸውም። በአዳማ በኩልም አልፎ አልፎ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶች ይታዩ የነበረ ሲሆን 65ኛው ደቂቃ ላይ የተለመደው የወልቂጤ የኋላ ክፍል አለመናበብ ከፈጠረው አጋጣሚ አብዲሳ ጀማል ያገኘውን ዕድል ሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቶበታል።
በሂደት በተለይም የአማካያቸው አብዱልከሪም ወርቁን ጉዳት በኋላ የወልቂጤ ከተማዎች ጥቃት እየተቀዛቀዘ መጥቷል። እምብዛም ሙከራዎች እየታዩበት ያልነበረው ጨዋታ ተጠናቀቀ ሲባል ግን አዳማዎች የአቻነት ግብ አግኝተዋል። በመጨረሻ ደቂቃ ከሳጥኑ በቅርብ ርቀት ወደ ግራ ካመዘነ ቦታ የተሰጠውን ቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው በላይ ዓባይነህ በመጀመርያ ንክኪው በቀጥታ መትቶ አስቆጥሯል። በጭማሪ ደቂቃ ላይ አዳማዎች አሸናፊ ሊሆኑበት የሚችሉበት ጥሩ አጋጣሚ ቢያገኙም የወልቂጤ ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተውት ጨዋታው በአቻ ውጤት ተፈፅሟል።
© ሶከር ኢትዮጵያ