20ኛው የጨዋታ ሳምንቱ ላይ በደረሰው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሳምንቱ ስድስት ጨዋታዎች ላይ የታዘብናቸው ክለብ ነክ ጉዳዮች በዚህ ፅሁፍ ለመዳሰስ ሞክረናል።
👉 እጅግ ወሳኝ ሦስት ነጥብ ያሳኩት ድሬዎች
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከፍተኛ ግምት በተሰጠው እና ሁለቱን የወራጅነት ስጋት ያንዣበባቸው ድሬዳዋ ከተማ እና ሲዳማ ቡናን ያገናኘው ጨዋታ ሙኸዲን ሙሳ ከፍፁም ቅጣት ምት ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ድሬዳዋ ከተማዎች እጅግ ወሳኝ ሦስት ነጥብ አሳክተዋል።
የፕሪምየር ሊጉ ውድድር ወደ ድሬዳዋ ከተማ ካመራ ወዲህ በምስራቅ ኢትዮጵያ ብቸኛ ተሳታፊ ክለብ የሆነው ድሬዳዋ እስካሁን ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች እንደ ቡድን ያለው ህብረት እና ከፍተኛ መነሳሳት ብሎም በጨዋታዎች ወቅት ተጫዋቾቹ ላይ የሚነበበው ያላቸውን ሁሉ ሜዳ ላይ አውጥቶ የመስጠት ቁርጠኝነት የሚያስደንቅ ነው። በውጤት ደረጃም እስካሁን በድሬዳዋ ባደረጓቸው ጨዋታዎች ሁለት ሲያሸንፉ በአንዱ ተሸንፈው በአንዱ ደግሞ አቻ መውጣት ችለዋል።
እንደ ቡድን በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ በተደራጀ ሁኔታ እየተንቀሳቀሱ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ኳስን በላይኛው የሜዳ ክፍል ለማግኘት ከፍ ያለ ጫናን በማሳደር በመቀማትም ሆነ በቅብብል ከራሳቸው ሜዳ ይዘው በመውጣት ጥቃቶችን ሲሰነዝሩ ይታያሉ። ኳስ በሚያጡባቸው ቅፅበቶች ደግሞ ከፊት አጥቂው በስተቀር በህብረት ወደ ራሳቸው ሜዳ በበመመለስ እያደረጉ የሚገኙት እንቅስቃሴ በተለይ በመጨረሻዎቹ የባህርዳር ከተማ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ ላይ በስፋት ተስተውሏል። አሁንም ቢሆን ግን የተገኙ ዕድሎችን ወደ ግብነት የመቀየር ነገር ላይ ብዙ ሥራዎች ይጠብቁታል።
በእኩል 17 ነጥቦች ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር 11ኛ እና 10ኛ ደረጃ ላይ የነበሩት ድሬዳዋ እና ሲዳማ ባደረጉት በዚህ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማዎች ቀጥተኛ ተፎካካሪያቸው የሆነው ቡድን ላይ ይህን ድል ማስመዝገባቸው እንደ ሌሎች ሦስት ነጥቦች የሚታይ አልነበረም።
👉በቀናት ልዩነት የተዳከመው ቅዱስ ጊዮርጊስ
ከቀናት በፊት ተጠባቂ በነበረው የሸገር ደርቢ ኢትዮጵያ ቡናን በአስቻለው ታመነ ብቸኛ የግንባር ኳስ ማሸነፍ ችለው የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ20ኛው ሳምንት ጅማ አባ ጅፋርን ገጥመው ከደካማ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጋር አንድ አቻ ተለያይተው ወጥተዋል።
በሸገር ደርቢ ቡድኑ ድል ሲቀዳጅ ተጋጣሚያቸውን ከራሳቸው ሜዳ ኳሶችን መስርተው እንዳይወጡ ከፍ ያለ ጫናን አሳድረው ለመጫወት በቻሉት መጠን ጥረት ሲያደርጉ ነበር። በዚህም በሁለተኛው አጋማሽ የተወሰነ መቀዛቀዝ ተስተዋሎ እንጂ አጨዋወቱ ውጤታማ አድርጓቸው እንደነበር አይዘነጋም። አሰልጣኝ ፍራንክ ናታልም ቡድኑ ጅማ አባጅፋርን ሲገጥም ቡናን ከገጠመው ስብስብ ምንም የተጫዋች ለውጥ ሳያደርጉ ጨዋታውን ማድረጋቸው በቡድናቸው ደስተኛ መሆናቸውን የሚያሳይ ነበር።
በጨዋታውም በጊዮጊስ በኩል እንደ ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ሁሉ ገና በጊዜ ጌታነህ ከበደ ከማዕዘን ምት የተሻማለትን ኳስ በግንባር በመግጨት ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ከዚህች ግብ መቆጠር በኃላ ግን በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ የተመለከትነው ቅዱስ ጊዮርጊስ በበርካታ መመዘኛዎች እጅግ የተዳከመውን ነበር።
በሜዳው የላይኛው ክፍል ተጋጣሚን ጫና ውስጥ አስገብቶ ለመጫወት ተጫዋቾች ከአዕምሯዊ ዝግጁነት ባልተናነሰ ከፍተኛ አከላዊ ዝግጁነት እንደሚጠይቅ ይታወቃል። በዚህም የተጋጣሚ ተጫዋቾች ስህተት እንዲሰሩ በመጋበዝ ኳስን ዳግም በቁጥጥራቸው ስር ለማስገባት ፋታ ያለሽ ሩጫዎችን ለማድረግ ይገደዳሉ። ይህ በራሱ ለቀጣይ ጨዋታዎች በተጫዋቾች የአካል ብቃት ላይ የሚያሳድረው ጫና እንዳለ ሆኖ በሸገር ደርቢ ጨዋታ እንደተመለከትነው ዓይነት ደግሞ ምቹ ያልሆነ (ጭቃማ) የመጫወቻ ሜዳ ላይ መጫወት በራሱ ከመደበኛ የመጫወቻ ሜዳ በበለጠ ተጫዋቾች ተጨማሪ ጉልበት እንዲያወጡ የሚያስገድድ ነው። በዚህም ቅዱስ ጊዮርጊስ የሸገር ደርቢ ጨዋታ ሰለባ የሆነ ይመስላል።
በፕሪምየር ሊጋችን ከተሰረዘው የውድድር ዘመን አንስቶ በጨዋታ ሳምንታት መካከል ያለው የቀናት ልዩነት ጠባብ መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም ቡድኖች በጨዋታ ቀናት መካከል በሚኖሩ ዕለታት ለተጫዋቾች በቂ የማገገሚያ ጊዜ ባለመኖሩ የተለያዩ ፈጣን የማገገሚያ መንገዶችን ካልተጠቀሙ ብሎም በተጫዋቾች አጠቃቀም እና የጨዋታ ስልቶች ላይትኩረት የማያደርጉ ከሆነ ለወትሮውም ቢሆን የወጥነት ችግር መገለጫው በሆነው ሊጋችን ከጨዋታ ሳምንት ሳምንት ፍፁም የተለያዩ ቡድኖችን መመልከታችን የሚቀር አይመስልም።
👉 ወልቂጤ ከተማ አሁንም ማሸነፍ አልሆነለትም
በ20ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ወልቂጤ ከተማ ከሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት በኋላ ወደ ድል ለመመለስ እጅግ ቢቃረብም በጭማሪ ደቂቃ ላይ በተቆጠረች የቅጣት ምት ግብ ሳይሳካ ቀርቷል።
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የተዳከመ ቡድን እያሳዩ የቆዩት ወልቂጤ ከተማዎች ምስጋና በመጀመሪያው ዙር ለሰበሰቧቸው ነጥቦች እንጂ እንደ ሁለተኛ ዙር እንቅስቃሴያቸው በወራጅ ቀጠና ውስጥ በተዘፈቁ ነበር። ችግር ላይ የሚገኘው ቡድኑ ከባለፈው የሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ አንስቶ ከወትሮው አጨዋወቱ በተለየ መልኩ ጥንቃቄን ቀላቅሎ ቢጫወትም በሁለቱም ጨዋታዎች ነገሮች እንደታሰቡት ሊሄድላቸው አልቻሉም። በአንድ ወቅት ማጥቃት እና ማጥቃት መገለጫው የነበረው ቡድኑ አሁን ላይ የማጥቂያ አማራጮቹ በሙሉ ጠበው ግራ በተጋባ እንቅስቃሴ ውስጥ እየዳከረ ይገኛል። በተጨማሪም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ለመከተል ያሰበው ጥንቃቄ አዘል እንቅስቃሴ በዋነኝነት የሚፈልገውን የማያቋርጥ ትኩረት በሚያጣባቸው የተወሰኑ ቅፅበቶች ግቦችን እያስተናገደ ይገኛል።
በዚህኛው ሳምንት ከአዳማ ከተማ ጋር በተደረገው ጨዋታ ላይ ቡድኑ ጥንቃቄ መር አጨዋወት ቢጫወትም የማጥቃት እንቅስቃሴው በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ካለፉት ጊዜያት የተሻለ ነበር። በዚህም ግልፅ የሚባሉ ባይሆኑም የጎል ዕድሎችን ፈጥረው ነበር። ሆኖም ተጨማሪ ጎሎችን በማስቆጠር የጨዋታውን ውጤት በራሳቸው መወሰን ሳይችሉ ቀርተው በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተቆጠረባቸው ጎል ሁለት ነጥብ አሳልፈው ለመስጠት ተገደዋል። በተጨማሪም የቡድኑ የኋላ መስመር የትኩረት ደረጃ የላቀ እንዲሆን በሚጠበቅባቸው ቅፅበቶች የታየው ቸልተኝነት ዋጋ እንደሚያስከፍል የአዳማው ጨዋታ ማሳያ ሆኗል። በዚህም በመከላከሉ ወቅት በሳጥናቸው ጠርዝ የሰሩት አንድ ያልተገባ ጥፋት የቡድኑን የ90 ደቂቃ ጥረት መና ያስቀረ ሆኗል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ተጫዋቾች ላይ ይታይ የነበረው ስሜትም ይህንን እውነታ በደንብ የሚያሳይ ሆኗል።
👉 በሚገባ የተፋለመው ጅማ አባ ጅፋር
በዚህ ሳምንት ከነበሩ የሊጉ መርሐ ግብሮች መካከል ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጅማ አባ ጅፋር የተገናኙበት ጨዋታ አንዱ ነበር። ከጨዋታው በፊት ቅዱስ ጊዮርጊስ በሸገር ደርቢ ላይ ካሳየው አቋም እና መነሳሳት እንዲሁም ጅማ አባ ጅፋር በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ ግምቶች ለጊዮርጊስ ያደሉ ነበሩ። ነገር ግን በዘጠና ደቂቃው ፍልሚያ ነጥብ ተጋርተው መውጣታቸው ብቻ ሳይሆን ሜዳ ላይ የነበረው ፉክክራቸው ከግምቱ የተለየ ሆኗል።
ቀድሞ ግብ አስቆጥሮ ውጤት ማስጠበቅ እየተሳነው በተደጋጋሚ ነጥብ የተወሰደበት ጅማ አባ ጅፋር ጭራሽ በጌታነህ ከበደ አማካይነት ቶሎ ግብ ሲቆጠርበት መታየቱ ጨዋታው ለፈረሰኞቹ ይበልጥ ቀላል ሊሆን እንደሚችል ጠቁሞ ነበር። ነገር ግን ቀሪውን ደቂቃ በትጋት የተጫወቱት አባ ጅፋሮች አንድ ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል። ከዚህም በላይ አሸንፈው ለመውጣት የተቃረቡባቸው አጋጣሚዎች ታይተው ነበር።
ከፍተኛ የመውረድ ስጋት የተጋረጠበት ግን ደግሞ ሜዳ ላይ የሚቻለውን ሁሉ እያደረገ የሚገኘው የቡድኑ ስብስብ በዚህ ሳምንት ያሳየው ይህ ብቃት ትኩረት ሳቢ ነበር። ለወትሮው ከኋላ ስህተት የማያጣው የቡድኑ የተከላካይ ክፍል ራሱን ከስህተት ጠብቆ እና በአጠቃላዩ የቡድኑ መዋቅር ታግዞ ጨዋታውን አገባዷል። ቁምጭጭ ያለ መከላከልን ምርጫው ያላደረገው ጅማ በሰንጠረዡ አጋማሽ የሚገኝ ቡድን ባህሪን ተላብሶ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠርም ጥረት አድርጓል። አሸንፎ ለመውጣት ባይታደልም ተጋጣሚውን የተገዳደረበት መንገድ ግን በሳምንቱ ከታዩ መልካም የቡድን እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንዲጠቀስ የሚያደርገው ሆኖ አልፏል።
👉 በወሳኝ ሰዓት ነጥቦች እየጣለ የሚገኘው ባህር ዳር
ወጣ ገባ ከሆነ የውድድር ዘመን በኋላ በመቀመጫ ከተማው ላይ በተደረጉ ጨዋታዎች መነቃቃት የታየበት ባህር ዳር ከተማ ተከታታይ አራት ጨዋታዎችን በማሸነፍ ወደ ሁለተኛ ደረጃ በእጅጉ መቃረብ ችሏል። ከመሪዎቹ ተርታ ርቆ የነበረው ቡድንም የነጥብ ልዩነቱን በማጥበብ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ የሚያስገኘውን ቦታ ለመያዝ በሚደረገው ፉክክር ላይ ተዋናይ መሆን ችሏል።
ሆኖም ፉክክሩ ባየለበት በዚህ ወቅት ላይ ባደረጋቸው ያለፉት ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው ዘጠኝ ነጥብ ማሳካት የቻለው ሁለት ብቻ መሆኑ አስደናቂ ማንሰራራቱን አቀዝቅዞታል። ባለፉት ሳምንታት በፉክክሩ ውስጥ የሚገኙት ቡድኖች በተለይም የኢትዮጵያ ቡና ነጥቦች መጣል እንጂ በመካከላቸው የነበረው የነጥብ ልዩነት ከሁለት በላይም ሊሆን ይችል ነበር።
ቡድኑ በዚህ ሳምንት ከሀዋሳ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ በማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ በእጅጉ ተዳክሞ የታየ ሲሆን የጎል አጋጣሚ መፍጠር ቀርቶ በተጋጣሚ የጎል ክልል የተገኘባቸው አጋጣሚዎች በቁጥር ውስን ሆነው ታይተዋል። በተለይም 1-0 እየተመራ ሁለተኛው አጋማሽን እንደጀመረ ቡድን ያደረገው የማጥቃት እንቅስቃሴ አጥጋቢ ነበር ብሎ ለመናገር የማያስደፍር ነበር።
ባህር ዳር ባለፉት ሁለት ጨዋታዎቹ ላይ የዋና አሰልጣኙ ፋሲል ተካልኝን ግልጋሎት ባለማግኘቱ መጎዳቱ እንዳለ ሆኖ ከፍተኛ ፉክክር እንደሚያስተናግድ የሚጠበቀው የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎን ለማግኘት በቀጣዮቹ ጨዋታዎች ላይ ነጥቦችን መሰብሰብ ይጠበቅበታል።
© ሶከር ኢትዮጵያ