አሰልጣኝ ፍስሀ ጥዑመልሳን ወደ ክስ አምርተዋል

ድሬዳዋ ከተማን በዋና አሰልጣኝነት ሲያገለግሉ የቆዩት ፍስሐ ጥዑመልሳን ለፌዴሬሽኑ የክስ ደብዳቤ አስገብተዋል።

ፈገግታን በሚጭሩ አስተያየታቸው በብዙዎች የስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ትኩረትን ይስቡ የነበሩት አሰልጣኝ ፍስሐ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የጅማ ምዕራፍ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድሬዳዋ ከተማን በዋና አሰልጣኝነት ሲያገለግሉ ቆይተው በኃላም በስምምነት መለያየታቸው ይታወቃል። ሆኖም “ቀሪ ኮንትራት ጊዜ እያለኝ በስምምነት የተለያየሁ ቢሆንም በስምምነቴ መሠረት የውል ማፍረሻ ክፍያ እንደሚሰጠኝ ቃል ተገብቶልኝ ሳለ ክለቡ በምንም ጉዳይ ሊያናግረኝ አልቻለም።” ሲሉ ቅሬታቸውን በመያዝ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በደብዳቤ አስገብተዋል።

ፌዴሬሽኑንም ክለቡ በቀረበበት ቅሬታ ዙርያ ምላሽ እንዲሰጥ በደብዳቤ የጠየቀ ሲሆን ክለቡም ወደ ህግ ክፍል በመምራት እስከ ሐሙስ ድረስ ምላሽ እንደሚሰጥ አሳውቋል። በቀጣይ በዚህ ጉዳይ የሚኖሩ አዳዲስ ነገሮች ካሉም ተከታትለን እናቀርባለን።

© ሶከር ኢትዮጵያ